የአሰልጣኞች አስተያየት | ስሑል ሽረ 2-0 ፋሲል ከነማ

በኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ዘጠነኛ ሳምንት የመክፈቻ ጨዋታ ስሑል ሽረ ፋሲልን 2-0 ከረታ በኋላ የሁለቱ ቡድኖች አሰልጣኞች አስተያየታቸውን ሰጥተዋል።


👉 “ሦስትና አራት አግብተን ማሸነፍ እንችል ነበር” ሳምሶን አየለ (ስሑል ሽረ)

ስለ ጨዋታው

ጨዋታው ጥሩ ነበር። ሦስትና አራት አግብተን ማሸነፍ እንችል ነበር። ተጋጣሚያችን ይዞት የሚመጣውን አጨዋወት ቀድመን አውቀን ስለነበር ከኃላ የተጫዋቾች ቁጥር ቀንሰን በርካታ ተጫዋቾች በነሱ ሜዳ አድርገን ለማጥቃት ነው የገባነው። በሁለቱም አጋማሾች ጥሩ ተንቀሳቅሰን በርካታ ዕድሎች በመፍጠር ሁለት ለባዶ ማሸነፍ ችለናል። ቡድናችን ጥሩ ለውጦች አሉት፤ ይህን እያጠናከርን እንሄዳለን። የባለፈው የሜዳ ውጭ ድል ትልቅ የራስ መተማመን ነው የፈጠረብን። በአጠቃላይ ጨዋታው ጥሩ ነው።

ስለ ቡድኑ መንፈስ

ከሜዳ ውጭ የነበሩብን ችግሮች እየተፈቱ መጥተዋል። የቡድኑ ትኩረት ሙሉ በሙሉ በጨዋታው በማድረግ ላይ ነው። በቀጣይ ከዚህ የተሻለ ነገር እንፈጥራለን። ደጋፊያችንም የጀርባ አጥንታችን ሆኗል። እየሰጠን ላለው ደጋፍም ትልቅ ምስጋና አለን።

👉 “የሽረዎች ውሎ መልካም ነበር” ሥዩም ከበደ (ፋሲል ከነማ)

ስለ ጨዋታው

ሽረዎች የነበራቸው አቋም ጥሩ ነው። የነበራቸው ፍላጎትም ጥሩ ነበር። በኛ በኩል በሁለተኛው አጋማሽ አስተካክለን ለመምጣት ሞክረናል። ወደ ጨዋታችን ለመምጣት በነበርንበት ሰዓት ነው ጎሎቹ የገቡት። በተለይም በሁለተኛው አጋማሽ እኛ የተሻልን ነበርን የሚል ሀሳብ አለኝ። በተደጋጋሚ ያገኘናቸው የመዓዝን ምቶችም የማጥቃት ኃይላችንን የሚያሳዩ ናቸው።

የተቆጠረብን ግብ የግብ ጠባቂያችን መዘናጋት ነው፤ እሱም ችግር ነበር። ከዛ በኃላ በኛ የስሜት መውረድ ነበር። ምክንያቱም የመጀመርያው ግብ መጨረሻ ሰዓት ነው የተቆጠረው። በአጠቃላይ ግን የሽረዎች ውሎ መልካም ነበር።

ስለተደረገላቸው አቀባበል

የተደረገልን መስተንግዶ ጥሩ ነበር። ከትናንት ጀምሮ የክልሉ መስተዳደር ግብዣ አድርገውልናል። ቡድናቸውን የደገፉበት መንገድም ደስ ይላል። በአጠቃላይ የነበረው ሥነ ምግባር ደስ የሚል ነበር።


© ሶከር ኢትዮጵያ