ፕሪምየር ሊግ 12ኛ ሳምንት – ዐበይት ጉዳዮች (፫) | አሰልጣኞች ትኩረት

በ12ኛ ሳምንት በተካሄዱት 8 ጨዋታዎች ላይ የተመለከትናቸውን አሰልጣኝ ነክ ጉዳዮችና ትኩረት ሳቢ ድህረ ጨዋታ አስተያየቶችን በሚከተለው መንገድ አቅርበናቸዋል።

👉 ሰሚ ያጣው የድህረ ጨዋታ ቃለ ምልልስ ጉዳይ

በተደጋጋሚ በዚህ ዓመት የሳምንታዊ ዓበይት ጉዳዮች ዐምድ ላይ እንደምናነሳው አሰልጣኞች ከሽንፈቶች በኃላ በድህረ ቃለምልልስ ወቅት ደብዛቸውን የማጥፋት ሒደት በዚህኛው ሳምንት ተባብሶ ቀጥሏል። በዚህ ሳምንትም የሲዳማ ቡና፣ መቐለ 70 እንደርታ፣ ኢትዮጵያ ቡና እና ሀዲያ ሆሳዕና አሰልጣኝ ቡድን አባላት ተሰብስበው ለሚጠብቋቸው የሚዲያ አባላት ሀሳብ ሳይሰጡ ቀርተዋል።

ከሦስቱ ቡድን አሰልጣኞች የኢትዮጵያ ቡናው አሰልጣኝ ካሳዬ አራጌ ወደ መልበሻ ክፍል አካባቢ በቡድናቸው ደጋፊዎች በተፈጠረ ግርግር የተነሳ መስጠት ካልቻሉበት ሒደት በስተቀር ቀሪዎቹ አሰልጣኞች አስተያየት ላለመስጠት በቂ ምክንያት ማቅረብ በማይችሉበት ሁኔታ ከስፍራው ተሰውረዋል። በተለይ ደግሞ የሀዲያ ሆሳዕናው አሰልጣኝ ግርማ ታደሰ በተጫዋቻቸው ተከልለው ተሰብስቦ የሚጠብቃቸውን የሚዲያ ባለሙያዎችን በቆሙበት ሸውደው ለመሄድ የሞከሩበት መንገድ የሚያስተዛዝብ ነበር።

የተሸነፈ ቡድን አሰልጣኞች በውጪያዊ ጉዳዮች ማሳበብ በተለመደበት የሀገራችን ሊግ መሰል ድብብቆሽ ሰሞነኛ ጥሩ የማምለጫ መንገድ ተደርገው መወሰዳቸውን ቀጥለዋል።

👉 በሜንሳህ እና ጃኮ ላይ ደፋር ውሳኔ የወሰኑት የወልቂጤው አለቃ

በፕሪምየር ሊጉ በመጀመሪያ የማሰልጠን ሥራቸው ላይ የሚገኙት የወልቂጤ ከተማው አሰልጣኝ ደግአረግ ይግዛው በከፍተኛ ወጪ ቡድኑን የተቀላቀሉት ሁለቱን ቶጎዋዊዎች ሶሆሆ ሜንሳህ እና ጃኮ አረፋት ላይ የወሰዱት ድፍረት የተሞላበት ውሳኔያቸው ቡድኑን እየጠቀመ ይገኛል።

በሒደት ወደ ወራጅ ቀጠና ተንሸራቶ የነበረው ቡድኑ መሻሻሎችን በማሳየት ወደ 5ኛ ደረጃ ከፍ ማለት ችሏል። እንደቡድን መሻሻል ባሳየው ቡድኑ ውስጥ በተለይ ግብ ለማስቆጠር በጣም ሲቸገር በነበረው ደካማ የአጥቂ መስመራቸው ዋነኛ መሪ የነበረውንና ከአቅም በታች እንደሚጫወት በተደጋጋሚ ወቀሳ የሚሰነዘርበት ጃኮ አራፋት ከጉዳት ነፃ ቢሆንም ከስብስብ ውጭ ባለፉት ሦስት ጨዋታዎች ከስብስብ ውጪ ሲያደርጉት ተስተውሏል። በዚህም በ9 ቁጥርነት ሚና የነበረውን ክፍተት ለመሸፍን እድል የተሰጣቸው ሳዲቅ ሴቾ እና አህመድ ሁሴን አሰልጣኙ የጣለባቸውን እምነት በሚገባ እየተወጡ ነው ብሎ መናገር በሚያስችል መልኩ ሁለቱም ወሳኝ የሆኑ ሁለት ሁለት ግቦችን ማስቆጠር ችለዋል።

በተመሳሳይ ግብጠባቂ ሥፍራ ላይ ሶሆሆ ሜንሳህን በተመሳሳይ ሒደት (ቀደም ብሎ ቢሆንም) ከስብስብ ውጭ በማድረግ በምትኩ በሊጉ የካበተ ልምድ ባለቤቱ ይድነቃቸው ኪዳኔ በተከታታይ ጨዋታዎች በግቦቹ ቋሚዎች መሀል የቡድኑን ግብ እየጠበቀ ጥሩ አቋሙን እያሳየም ይገኛል።

አሰልጣኙ ወቅታዊ ብቃትን መሰረት በማድረግ ሁኔታ የወሰዱት ይህ ድፍረት የተሞላበት ውሳኔ ሌሎች በሊጉ የካበተ የማሰልጠን ልምድ ያላቸውና ደካማ ግልጋሎት እየሰጡ እንኳን ተጠባባቂ ለማይደረጉ የውጭ ሀገራት እንዲሁም ባለልምድ የሀገር ውስጥ ተጫዋቾችን ከልክ ያለፈ መለሳለስ ለሚያሳዩ አሰልጣኞች አስተማሪ ውሳኔ ነው።

👉 ተመልካቹ አሰልጣኝ ስምዖን ዓባይ

ባሳለፍነው እሁድ ድሬዳዋ ከተማ በወላይታ ድቻ 3-0 ሽንፈትን አስተናግዷል። በዚሁ ጨዋታ ላይ ለወትሮ በሜዳው ጠርዝ ሲቁነጠነጡ የሚታዩት ድሬዳዋው አሰልጣኝ ስምዖን ዓባይ ያለወትሯቸው ለሙሉ 90 ደቂቃው ከወንበራቸው ሳይነሱ ጨዋታቸውን ጨርሰዋል። (ክለቡ ዛሬ በወሰነው ውሳኔ አሰልጣኙ ከኃላፊነታቸው ተነስተዋል።)

👉 ዐበይት አስተያየቶች

* ውበቱ አባተ በእስካሁኑ የሰበታ የውጤት ጉዞ ላይ ሰራሁት ብለው ስሚያስቡት ስህተት

“ምን አልባት አሁንም ለምንገኝበት ደረጃ የእኔ ስህተት ነው ብዬ አስባለሁ። ምክንያቱም ሁሌም የምንጫወተው ከሜዳችን ውጭ ቢሆንም ሁልጊዜም አቀራረባችን ለማሸነፍ ነው። ይህም በራሱ በቀላሉ ነጥቦችን እንዳናስመዘግብ እያደረገን ይገኛል። በቀጣይ ይህን ማስተካከል ከቻልን የተሻለ ከስጋት ነፃ የምንሆንበትን እድል መፍጠር እንችላለን። ”

* የአዳማው ም/አሰልጣኝ የቡድኑን ውጤት ለማስቀጠል መሰራት ስላለበት ሥራ

“ይህ የሚወሰነው በዋነኝነት በአስተዳደሩ የሚወሰን ነው ፤ አስተዳደሩ አፋጣኝ ምላሽ የሚሰጥ ከሆነ በተሻለ ወደ መስመር ተመልሰን ጥሩ ነገር መስራት እንችላለን። እንደምታዩት አሁን ላይ ችግር ላይ ነን ይፈታል ቢባልም ያየነው ነገር የለም። አስተዳደሩ ይህን ጉዳይ በጊዜ ቢፈታልን ትልቅ ውጤት ይዘን እንወጣለን ብዬ አስባለሁ።”

* ሥዩም ከበደ ቡድናቸው ላይ ስለነበረው ተቃውሞ

“ሀብታሙ ተከስተ እና ኦሲ ማውሊ ለመቐለ ጨዋታ ይደርሳሉ በአንፃሩ ጅብሪል አህመድ ለቅዱስ ጊዮርጊስ ጨዋታ ይደርሳል ያለውን ክፍተት ሞልተን እንደርሳልን። ብዙ ተጫዋቾች ከህመም እየወጡ እንደዚህ እየጠጋገንን ከዚህ ደረጃ መድረሱ ሊመሰገን ይገባ ነበር። እና በአንዳንድ ደጋፊዎች ላይ የምንሰማው ነገር ሁላችንንም ቅር ያሰኘ ነገር ነው። ተጫዋቾችን በራስ መተማመናቸውን የሚያሳጣ ተግባር ነው። እና ይህ ቢስተካከል እና ለቡድኑ እድገት በጋራ ብንሰራ ጥሩ ነው ።”

* ደለለኝ ደቻሳ ስለተለዋዋጭ የጨዋታ እቅዳቸው

“መጀመሪያ አጋማሽ ላይ ሶስት ጎል አግብተናል፡፡ ሁለተኛ አጋማሽ ላይ ጥንቃቄ ላይ አተኩረን ነው የገባነው ሜዳችንን ዘግተን ማጥቃት ባለብን ዕድል ልክ ለማጥቃት ነው ሁለተኛ አጋማሽ ላይ የገባነው ቢሆንም ተሳክቶልናል ብዬ አስባለሁ፡፡

* ስምኦን ዓባይ ስለደካማው የተከላካይ መስመራቸውና ተጫዋቾች ድካም

“ልክ ነው እንግዲህ እግር ኳስ ይሄ ነው፡፡ በ45 ደቂቃው ነው ተሸንፌ የወጣውት፡፡ ፈፅሞ የኛ ቡድን በመጀመሪያ 45 እንዳያችሁት ምንም ዝግጁ አልነበረም በተለይ ከወገብ በታች በጣም የተበታተነ እና ያልተቀናጀ ቡድን ነበር፡፡ ያንን ነገር በመጠቀም ደግሞ እነሱ ሶስት ጎል በተከታታይ ሊያገቡብም ችለዋል፡፡ ስለዚህ ከእረፍት በፊት እንደነበራቸው ብልጫ እና እንቅስቃሴ ሶስት ጎል ማስቆጠራቸው የሚያንስ ነው፡፡ በመጀመሪያው አጋማሽ በነበረው ነገር ሙሉ ለሙሉ ብልጫ ተወስዶብኝ መሸነፍ ችያለሁ።

“ተጫዋቾቹ ከፍተኛ የሆነ ድካም ይታያል። ባለን ተጫዋቾች ነው የምንጫወተው። ተከታታይ እየተጫወቱ ያሉ ልጆች ስለሚጫወቱ የምንቀይረው እንኳን ብዙም የለም፡፡ አድካሚ ጉዞ እያደረግን ነው፤ እንደምክንያት ባይቆጠርም። በ45 ደቂቃ ጥሩ እንቅስቃሴ አድርገው ሶስት ጎል አግብተው አሸንፈውናል፡፡ እግር ኳስ ይሄ ነው መስተካከል ያለብንን ለማስተካከል ጥረት ማድረግ ነው ለሚቀጥለው፡፡

* የወልዋሎው ም/አሰልጣኝ የዋና አሰልጣኛቸው በቅጣት ስላለመኖሩ

“ተፅዕኖ አድርጎብናል። በተለይ ባለፈው ሳምንት (11ኛ ሳምንት) የሲዳማ ጨዋታ
የተነገረን ለጨዋታው 9 ሰአት ልንገባ 5 ሰአት ላይ ነበር። ስለዚህ ይህ የራሱ የሆነ ተፅዕኖ ቡድናችን ላይ አሳድሮብናል።”

*ሰርዳን ዝቪጅኖቨ ስለእሁዱ አስደናቂ ድል

እንደማስበው ዛሬ ጨዋታውን ለመታደም የመጣ ተመልካቾች ተዝናንቷል፤ ስድስት ጎሎችን በማስቆጠራችን። ስለፍፁም ቅጣት ምቱ እርግጠኛ ባልሆንም በሰራናቸው ስህተቶች ነው ሁለት ጎሎች የተቆጠሩብን። በአጠቃላይ ግን ቅዱስ ጊዮርጊስ ምን ዓይነት እግር ኳስ መጫወት እንዳለበት ያሳየንበት ጨዋታ ነበር። በማጥቃት ላይ የተመሰረተ እና በርካታ ግቦችን ለማስቆጠር ጥረት የታየበት ነበር። በርካታ ግቦችን ለማስቆጠር ጥረት የታየበት ነበር።


© ሶከር ኢትዮጵያ