የፕሪምየር ሊግ 17ኛ ሳምንት ዓበይት ጉዳዮች (፪) – ተጫዋች ትኩረት

በ17ኛው ሳምንት በተከናከኑ ጨዋታዎች የተመለከትናቸው ተጫዋች ነክ ጉዳዮችን እንደሚከተለው አቅርበናል።

👉አሰልጣኙን የሚመለከተው ወጣቱ ግብጠባቂ

በትላትናው ዕለት ሰበታ ከተማ ቅዱስ ጊዮርጊስን በረታበት ጨዋታ ሁለተኛ የሊግ ጨዋታውን በቋሚነት ያደረገው ወጣቱ ግብጠባቂ ፋሲል ገ/ማርያም ተስፋ ሰጪን እንቅስቃሴ አሳይቷል። የቀድሞው የኢትዮጵያ ታዳጊ ብሔራዊ ቡድን ግብ ጠባቂ በጨዋታው የተወሰኑ የውሳኔ ስህተቶች ቢሰራም ጥሩ ጥሩ ኳሶችን ማዳን ችሏል።

ሌላኛው በትላንቱ ጨዋታ ትኩረት የሚስበው ጉዳይ ግብ ጠባቂው ኳስን ከተቆጣጠረ በኃላ በፍጥነት በረጅሙ ማስጀመር የሚገባውን ኳስ በማዘገየቱ በተደጋጋሚ ብስጭታቸውን ሲያሳዩ የነበሩት አሰልጣኝ ውበቱ አባተ ድርጊት ተከትሎ ግብጠባቂው በተለይ በሁለተኛው አጋማሽ የመጨረሻ 20 ደቂቃ ኳሶችን ሲቆጣጠር ውሳኔዎችን ለመወሰን የአሰልጣኙን ትዕዛዝ ይጠባበቅ የነበረበት መንገድ ያልተለመደ አጋጣሚ ነበር።

መሰል ወጣት ግብ ጠባቂዎች ራሳቸውን እንዲያሻሽሉ እና በሒደቱ የበቁ ተጫዋቾች እንዲሆኑ አሰልጣኞች በቅርብ ሆነው ሊያግዟቸው ቢገባም የራስ መተማመናቸውን እንዲያሳድጉ ግን ውሳኔዎችን በራሳቸው እንዲወስኑ ነፃነቱን ሊሰጧቸው እንደሚገባ ይታመናል።

👉ያልተጠበቀው የሰልሀዲን ሰዒድ ድርጊት እና መስመር የሳተው የደጋፊዎች ድርጊት

ሰበታ ከተማ ከቅዱስ ጊዮርጊስ ባደረጉት ጨዋታ በ62ኛው ደቂቃ ከመሀል ዳኛው ኃይለየሱስ ባዘዘው ጋር በፈጠረው አለመግባባት በሁለት ቢጫ ከጨዋታው የተሰናበተው ሰልሀዲን ሰዒድ ወደ መልበሻ ክፍል በሚያመራበት ወቅት በብስጭት ስሜት መለያውን ከወደ ደረቱ አካባቢ በመቅደዱ እና ማልያውን አውልቆ በመውጣቱ ጨዋታውን የታደሙ የክለቡ ደጋፊዎች ቅር ተሰኝተው መመልከት ችለናል።

ከጨዋታው መጠናቀቅ በኋላም ተጫዋቾቹ ከመልበሻ ክፍል ወደ ቡድኑ አውቶብስ እያመራ በሚገኝበት ወቅት ጥቂት በጉዳዩ ቅር የተሰኙ የክለቡ ደጋፊዎች ከተጫዋቹ ጋር ለፀብ የተጋበዙበት እንዲሁም በተፈጠረው ሁኔታ ተጫዋቹ እጁ ላይ ጉዳት ያስተናገደበትን አጋጣሚ ተመልክተናል።

ምንም እንኳን ድርጊቱ እንደ ሰልሀዲን ካለ ለብዙ የሀገራችን ተጫዋቾች አርዓያ ከሆነ ተጫዋች የማይጠበቅ ቢሆንም ተጫዋቾች እንደ ሁላችንም ሰዎች መሆናቸውን ስናስብ እና ከዕለታት በአንዱ የጨዋታ ቀን የስሜት ከፍታዎች መከሰታቸው አይቀሬ ስለመሆኑ መገመት አያዳግትም። ሲቀጥልም ተጫዋቹ በድርጊቱ ተፀፅቶ በአፋጣኝ ይቅርታ መጠየቁ የሚያስመሰግነው ተግባር ነው።

በተመሳሳይ አንድ ክለቡን የሚወድ ደጋፊም በክለቡ ዙርያ ችግሮችን ቢያስተውል ወይ በድርጊቶች ቅር ቢሰኝ እንኳን ነገሩን ክለቡን በማይጎዳ መልኩ በስክነት ለመፍታት መሞከር ሲገባ በዚህ ደረጃ ነገ የቡድኑን መለያ ለብሰው ለሚጫወቱ እና የክለቡ ባለውለታ ለሆነ ተጫዋች የማይመጥን ድርጊቶች መፈፀም እንዳለባቸው አይታመንም።

👉ድንቅ ብቃቱን ያሳየው ሀሪስተን ሄሱ

ከሳምንቱ ተጠባቂ ጨዋታዎች አንዱ በነበረው እና መቐለ 70 እንደርታን ከባህር ዳር ከተማ ያገናኘው ጨዋታ ያለ ግብ በአቻ ውጤት መጠናቀቁ ይታወሳል። በጨዋታውም ባለሜዳዎቹ መቐለ 70 እንደርታዎች በደጋፊዎቻቸው ታግዘው ባህርዳር ከተማ ላይ ፍፁም የበላይነት ማሳየት ቢችሉም የባህርዳር ከተማው ግብጠባቂ ሀሪሰን ሄሱ ግን የሚቀመስ አልነበረም።

ከጨዋታው ባህር ዳር ከተማዎች አንድ ነጥብ ይዘው እንዲወጡ ምክንያት የነበረው ሀሪስተ ሄሱ እጅግ በርካታ የግብ አጋጣሚዎችን የፈጠሩት መቐለዎች ውጤታማ እንዳይሆኑ ሳንካ ሆኖባቸዋል። በተለይ ከአማኑኤል ገ/ሚካኤል፣ ኦኪኪ አፎላቢ እና አልሀሰን ካሉሻ የተሰነዘሩበትን ተደጋጋሚ ሙከራዎች ያመከነባቸው መንገዶች እጅግ አስገራሚ ነበሩ።

ለወትሮም ቢሆን የብቃት ጥያቄ የማይነሳበት ተጫዋቹ ከልክ ያለፈ የራስ መተማመን ስሜቱ የመነጨ የሚሰራቸው ስህተቶችን ማሻሻል ቢችል ከዚህ በላይም ቡድኑን መጥቀም እንደሚችል ብዙዎች ይስማሙበታል።

👉እጅግ ቀርፋፋው ዐወል ከድር እና ለጨዋታ ዝግጁ ያልሆነው እዮኤል ሳሙኤል

የተከላካይ መስመር ተሰላፊዎቻቸውን በተለያዩ ምከንያቶች ያጡት ወልቂጤ ከተማዎች በዚህኛው ሳምንት ደግሞ በአዳማ ከተማ በተረቱበት ጨዋታ በሁለቱ አጋማሾች የተለያዩ የመሐል ተከላካዮች ጥምረት አስመልክተውናል።

በተለይ በመጀመሪያ አጋማሽ ከመሐመድ ሻፊ ጋር ተጣምሮ የነበረው ዐወል ከድር ከጨዋታው ጅማሮ አንስቶ ተክለ ሰውነቱ መግዘፍ ጋር ተያይዞ ጨዋታው ሊከብደው እንደሚችል እንደተገመተው ሜዳ ላይ በቆየባቸው ደቂቃዎች በእጅጉ ተቸግሮ ተስተውሏል። በሀገራችን እግርኳስ የአንድን ቡድን ደካማ ወገን ደጋግሞ በማጥቃት ረገድ ችግሮች ይስተዋላል እንጂ ከዐወል ጀርባ ተደጋጋሚ ኳሶችን ቢጥሉ ምን ይህል አደጋ መፍጠር ይችሉ እንደነበር በተወሰኑ የጨዋታ አጋጣሚዎች መመልከት ችለናል።

በተመሳሳይ ሌላኛው ከቀናት በፊት ሀዲያ ሆሳዕናን ለቆ ወልቂጤ ከተማን የተቀላቀለው የመስመር አጥቂው እዩኤል ሳሙኤል በሐሙሱ ጨዋታ ከጨዋታው ጅማሮ አንስቶ የመሰለፍ እድል ቢያገኝም በሀዲያ ሆሳዕና በነበረው የግማሽ የውድድር ዘመን ቆይታ በቂ የመሰለፍ እድል አለማግኘቱ ምንም ያህል ተፅዕኖ እንዳሳደረበት መመልከት ይቻላል።

አሰልጣኝ ደግአረግ ይግዛው ትልቅ ኃላፊነት በመውሰድ የጨዋታ ዝግጅነቱ ረገድ ብቁ ያልነበረውን እዮኤል ሳሙኤል በመጀመሪያ አሰላለፍ የተጠቀሙ ቢሆንም የሚጠብቁትን ያህል ግልጋሎት ሳይሰጥ ተቀይሮ ከሜዳ ወጥቷል።

👉የተረሳው ቴዎድሮስ ጌትነት ጥሩ መንቀሳቀሱን ቀጥሏል

ያለፉትን ዓመታት በፋሲል ከነማ ሦስተኛ ተመራጭ ግብ ጠባቂ የሆነው ቴዎድሮስ ጌትነት ከረጅም ጊዜያት በኋላ ያገኘውን ዕድል በአግባቡ እየተጠቀመ ይገኛል። የሚኬል ሳማኬን ዘግይቶ ወደ ቡድኑ መቀላቀል ተከትሎ በአዳማው ጨዋታ የመጀመሪያ ተሰላፊ የነበረው ቴዎድሮስ በባህር ዳሩ ጨዋታ ያሳየውን መልካም እንቅስቃሴ በትላንቱ ጨዋታም ላይ መድገም ችሏል። ቁመተ መለሎው ግብ ጠባቂ እያሳየ ከሚገኘው ጥሩ ብቃት አንፃር ለማሊያዊው ግብ ጠባቂ ነገሮችን የሚያከብድበት ይመስላል።

👉ያልተገባው የተስፋዬ መላኩ ድርጊት

እጅግ አሰልቺ መልክ በነበረው እና ሀዋሳ ከተማ ከ ሀዲያ ሆሳዕና ያለ ግብ አቻ ከተለያዩበት ጨዋታ መጠናቀቅ በኋላ በሀዋሳ ከተማዎች በኩል በተጠባባቂ ወንበር የነበረው ተስፋዬ መላኩ የፈጠረው ያልተገባ ድርጊት እጅግ አነጋጋሪ ነበር።

ጨዋታው ከተጠናቀቀ በኋላ በተጠባባቂ ቦታ ላይ ተቀምጦ የነበረው የሀዋሳ ከተማው ተጫዋች ወደ መልበሻ ክፍል ከሌሎች የቡድን አጋሮቹ ጋር እያመራ በነበረበት ወቅት ተጫዋቹ ከደጋፊዎች ጋር በፈጠረው አለመግባባት መነሾ ለደጋፊዎች ያሳየው ያልተገባ የእጅ ምልክት ከደጋፊዎች ባስተናገደው አፀፋዊ የፕላስቲክ ጠርሙሶች ውርወራን የፀጥታ አካላት ፈጥነው ደርሰው ነገሮችን ማርገብ ቻሉ እንጂ ወዳልተገባ ነገር ሊያመራ የሚችል ክስተት ነበር።

በከፍተኛ ደረጃ እየተጫወቱ የሚገኙ ተጫዋቾች በሚፈጠሩ አሉታዊ ሁነቶች ወቅት ስሜታቸውን በመቆጣጠር ተስፋ ሰጪ ነገር እየታየበት የሚገኘው የስታዲየሞች ፀጥታ ጉዳይ መስመር እንዳይስት ኃላፊነታቸውን መወጣት ይኖርባቸዋል።


© ሶከር ኢትዮጵያ