ሦስት የከፍተኛ ሊግ ክለቦች ድጋፍ አድርገዋል

በከፍተኛ ሊግ እየተሳተፉ የሚገኙት ገላን ከተማ ሀምበሪቾ እና ጋሞ ጨንቻ የገንዘብ ድጋፍ አድርገዋል።

የምድብ ሀ ተሳታፊው ገላን ከተማ በከተማው አካባቢ ስርጭቱን ለመከላከል ለሚደረጉ ተግባራት እንዲረዳ ለተቋቋመው ግብረ ሀይል ከተጫዋቾች፣ ከአሰልጣኝ እና የፅህፈት ቤት ሰራተኞች ከደመወዛቸው 50% እንዲሁም የተስፋ በድን አባላት ከደሞዛቸው 25% በድምሩ 152,173 (አንድ መቶ ሃምሳ ሁለት ሺ አንድ መቶ ሰባ ሶስት ብር) የገንዘብ ድጋፍ አድርገዋል፡፡

በከምባታ ዞን በዱራሜ ከተማ የሚገኘው የሀምበሪቾ ቡድን ከቦርድ አመራሩ ጀምሮ የቡድኑ የአሰልጣኝ አባላት እና ከሁሉም ተጫዋቾች ከወር ደመወዛቸው ላይ የሚቆረጥ በአጠቃላይ 91 ሺህ ብር ለዞን አስረክቧል፡፡ ክለቡም አሁን ካደረገው ድጋፍ በተጠናከረ መልኩ በቀጣይም አጠናክሮ እንደሚቀጥል የተገለፀ ሲሆን የትውልድ ስፍራቸው ከምባታ ዞን የሆኑ እውቅ ተጫዋቾችን በመያዝ በአራቱ ከተማ አስተዳደር እና በስምንት ወረዳዎች የግንዛቤ ማስጨበጫ ፕሮግራም አዘጋጅተዋል። በዚህም ፕሮግራም ላይ ከሚሳታፉ አካላት መካከል በሴቶች እግርኳስ ከሀገር ውስጥ አልፋ በአውሮፓ ያንፃባረቀችው ሎዛ አበራ፣ በሆሳዕና እየተጫወተ የሚገኘው ትግስቱ አበራ፣ በሲዳማ ቡና የሚጫወተው ሚሊዮን ሰለሞን፣ የሀምበሪቾ አምበል እንዳለ ዮሐንስ እንዲሁም የሞተር ሳይክል ስፖርተኛ ማስተር አብነት ከበደ በግንዛቤ ማስጨበጫው ላይ ተሳታፊ ላይ ተሳታፊ ከሆኑት መካከል ናቸው።

ሌላው የምድብ ለ የሚገኘው ጋሞ ጨንቻ ደግሞ ከ20 ሺህ ብር በላይ የመጀመሪያ ዙር ድጋፍ አበርክቷል። የጋሞ ጨንቻ ተጫዋቾች፣ አሰልጣኞች እና የደጋፊዎች ማኅበር ከቅዱስ ጊዮርጊሱ ተጫዋች ሙሉዓለም መስፍን ጋር በመተባበር ያሰባሰቡትን ገንዘብ በመጠቀም የንፅህና መጠበቂያ ቁሳቁስ ለጨንቻ ከተማ አስተዳደር እና ለጨንቻ ዙሪያ ወረዳ የኮቪድ 19 ድጋፍ አሰባሳቢ ኮሚቴ የመጀመሪያ ዙር ድጋፍ አስረክበዋል።

👉እጅዎን በተደጋጋሚ በሳሙና በአግባቡ በመታጠብ አልያም አልኮል እና ሳኒታይዘር በመጠቀም

👉ከሰዎች ጋር ንክኪ በማስወገድ

👉ከአላስፈላጊ እንቅስቃሴ በመገደብ፣ አካላዊ ርቀት በመጠበቅ እና በቤት በመቆየት ራሳችንን ከኮሮና ቫይረስ እንጠብቅ!


© ሶከር ኢትዮጵያ

error: