አስተያየት | የታዳጊዎች ሥልጠና ጉዳይ

በዚህ ዘመን እግርኳሳችን ለሚገኝበት ደረጃ በተለያዩ የሥልጠና መንገዶች ከታች የሚመጡ ታዳጊዎች በቂ እንደሆኑ ይሰማኛል፡፡ በአዲስ አበባ ብሎም በተለያዩ የክልል ከተሞች በርካታ ችግሮችን እየተጋፈጡ ታዳጊዎችን የሚያሰለጥኑ ብዙ አሰልጣኞች ይገኛሉ፡፡ በእነዚህ አሰልጣኞች  ስር ባሉ ፕሮጀክቶች አልፈው ለተለያዩ ክለቦች ከሚቀርቡት በጣት የሚቆጠሩ ታዳጊ ተጫዋቾች መካከል ባለፉት ዓመታት እድለኛ የሆኑትና በለስ የቀናቸው ለአንጋፋዎቹ ተተኪ ሆነው የመታየት ዕድል አግኝተዋል፡፡ እንዲያም ሆኖ እግርኳሳችን አዳዲስና ወጣት ተጫዋቾችን በትልቅ ደረጃ በማሳተፍ ረገድ አሁንም የኋሊት ጉዞውን እንደቀጠለ ነው ፡፡ እነዚህ ፕሮጀክቶች ጥራት ያላቸው ታዳጊ ተጫዋቾችን እያፈሩ አለመሆኑ ለዚህ ችግር በመንስኤነት ሊጠቀስ ይችላል፡፡

በታክቲክ አረዳድና አተገባበር፣ በቴክኒካዊ ክህሎት፣ በአካል ብቃት ዝግጅት እና ስነ-ልቦናዊ ጥንካሬ አይነተኛ ድክመት ለሚታይበትና ዝቅተኛ ግምት ለሚቸረው እግርኳሳችን ከየፕሮጀክቶቹ የሚወጡት ተጫዋቾች ከበቂ በላይ እንደሆኑ ይሰማኛል፡፡ ለመሆኑ ጥራት ያላቸው ወጣት ተጫዋቾችን በብዛት ማፍራት ዳገት የሆነብን ለምንድን ነው? በሃገራችን እግርኳስ ብሄራዊ ቡድናችን አልያም ክለቦቻችን በአህጉር አቀፍ ደረጃ የተሻለ ውጤት ባጡ ቁጥር ” ታዳጊዎች ላይ መስራት!” የሚለው አርዕስት ይነሳል፡፡ ” ከታች መጀመር አለብን!” የሚል ተደጋጋሚ ዲስኩርም ይደመጣል፡፡ በእግርኳሱ ዙሪያ በሚሰሩ በርካታ ባለሞያዎች እና ደጋፊዎች ሳይቀር ሃሳቡ እንደ አማራጭ መፍትሄ ሲቀርብ ይስተዋላል፡፡

በእግርኳስ እድገታቸው ከፍታ ላይ ከሚገኙ የተለያዩ አገራት ተመክሮ እንደምንማረው በጨዋታው ስኬታማ ለመሆን እና ውጤትን በዘላቂነት ጠብቆ ለመቆየት ታዳጊዎች ላይ መስራት የማያከራክር ሐቅ ነው፡፡ በኢትዮጵያ ባልተደራጀ መዋቅርና ባልተሟላ ሁኔታም ቢሆን በተለያዩ አሰልጣኞች የግል ተነሳሽነትና ፍላጎት ላይ ተመስርተው የሚሰሩ የታዳጊ ፕሮጀክቶች አሉ፡፡ እነዚህ የማሰልጠኛ ማዕከላት ውስጥ የሚታትሩ የበጎ ፈቃድ አሰልጣኞች ባላቸው እውቀትና ልምድ ልክ ለታዳጊዎች ስልጠና በመስጠት ለተለያዩ ክለቦች ወጣት ተጫዋቾችን ያበረክታሉ፡፡ለምሳሌ፦ እኔ የምሰራበት <የአስኮ እግርኳስ ፕሮጀክት> እንኳን ባለፉት አስራ ስምንት ዓመታት ውስጥ ከአንድ መቶ ሰላሣ በላይ የሚሆኑ ታዳጊ ተጫዋቾችን ለተለያዩ ክለቦች ማበርከት ችሏል፡፡ እነዚህ እና ከሌሎች ፕሮጀክቶች ተሳክቶላቸው  ወደ ተለያዩ የሃገሪቱ እግርኳስ የክለቦች የሄዱ ታዳጊዎች ግን በደካማው የታዳጊና ወጣት ቡድን የሥልጠና ሥርዓት አልፈው ከፍ ካለ ደረጃ  ሲደርሱ እየተሠለከትን አይደለም፡፡ አብዛኞቹ ከእግርኳስ ውጪ የመሆን ዕጣ ሲገጥማቸው የቀሩት ደግሞ በዚህ ጊዜ ካለን ደካማ የእግርኳስ ደረጃችን እንኳ ነጥሮ የመውጣት ተስኗቸው እዚያው-ለ-ዚያው ሲዳክሩ ይታያሉ፡፡

በእርግጥም  የእግርኳሳችን ደረጃ እንዲያድግ፣ ጥራቱን የጠበቀ ጠንካራ ሊግ እንዲኖረን፣ በዓለም አቀፍ መድረኮች ተወዳዳሪ ቡድኖች ለመገንባት ታዳጊዎችና ወጣቶች ላይ መስራት ግድ ነው፡፡ ይህ ማለት ግን በእግርኳሱ ውጤት ባጣን ቁጥር እየተነሳን ታዴጊዎች ላይ ስለመሥራት ማላዘን ያለብን አይመስለኝም፡፡ አሁን ባሉን የጥራት ደረጃቸው “እዚህ ግባ” የማይባሉ ሜዳዎች፣ በዘርፉ የሚገኙ የበቁ አሰልጣኞች እጥረት፣ ያለምንም እቅድ የመሥራት ልማድ፣ መዋቅራዊ አደረጃጀቱ የተሳለጠ የሥልጠና ሥርዓት ሳይኖር ታዳጊዎችና ወጣቶች ላይ ስለመሥራት ማሰብ አስቸጋሪ ነው፡፡ የታዳጊዎች ሥልጠና ራሱን የቻለ አንድ ትልቅ ሥራ ነው፡፡ በተቋም ደረጃ መመራት ይኖርበታል፡፡ በከፍተኛ ዝግጅትና ቀጣይነት ባለው መንገድ እንዲከናወን ዕቅድ፣ ራዕይና ተልዕኮን ይሻል፡፡

በእኔ እምነት “ከታች” የታዳጊዎች ስልጠና ከመጀመሩ በፊት “ከላይ” መስተካከል የሚኖርባቸው ጉዳዮች አሉ፡፡ እነዚህም በሚከተለው መልኩ በዝርዝር ቀርበዋል፡፡

1) እውቀትና ራዕይ ያላቸው አመራሮችና ባለሞያዎችን መፍጠር፦

በእግርኳሳችን አስተዳደራዊ መዋቅሮች በተለይም  በፌዴሬሽን፣ በስፓርት ኮሚሽን፣ በክፍለ ከተማና በወረዳ ስፓርት ቢሮዎች ያሉ አመራሮችና ባለሞያዎች ከጥቂቶቹ በስተቀር ጊዜያዊ ውድድሮችን ከማድረግ የዘለለ ለዘርፉ የሚመጥን እውቀት የላቸውም ፡፡ ከእውቀት ማነስ ችግር ባለፈ እግርኳሰችንን የማሳደግ ራዕይም አላነገቡም፡፡ የእግርኳስ ማሰልጠኛ ማዕከላትን በመክፈት ውጤታማ ከሆኑ አገራት ጀርባ ስለ ወደፊቱ በመተለም እቅድ የነደፉትና ለተግባራዊነቱ የተጉት ጥቂት ግለሰቦች መሆናቸው ይታወቃል፡፡ ስለዚህም የአገራችን እግርኳስ ተስፋ እንዲኖረው ከተፈለገ የሩቁን የሚመለከቱና ለሥራው የሚያስፈልገውን ዕውቀት የያዙ ግለሰቦች መፈጠር ወይም ካሉበት ቦታ በማሰስ  እንዲሳተፉ ማድረግ ያስፈልጋል፡፡

2)የረጅም ጊዜ ስልታዊ እቅድ መንደፍ፦

ባለፉት አሥር ዓመታት በኢትዮጵያ ያለውን የታዳጊዎች ስልጠና በቅርበት ተከታትያለሁ፡፡ በግለሰብ ባለቤትነት ሥር በሚተዳደሩ ማሰልጠኛዎችም ይሁን በአገር ዓቀፍ ወይም በክለቦች ደረጃ እኔ እስከማስታውሰው ድረስ በእቅድ የሚመራ ምንም ዓይነት ሥልጠና አላስተዋልኩም፡፡ “ከየት ተነስተን የት መድረስ አለብን?” ለሚለው ጥያቄ ተገቢ መልስ ማስቀመጥ ካልቻልን፣ ጠንካራውን እና ደካማውን ጎን፣ እድሎችንና ተግዳሮቶችን መለየት ካልቻልን በስራው ላይ ለመቆየት እንቸገራለን፡፡ በተለያዩ የእድሜ እርከኖች የሚገኙ ብሔራዊ ቡድኖች፣ በክለቦች ሥር የታዳጊዎች ስልጠና እና ውድድር የሚያካሂዱ አካላት ዝርዝር እቅዶች ያስፈልጋቸዋል፡፡ ስለ እነዚህ መሰረታዊ ግብዓቶች ደግሞ አስቀድሞ ማወቅ ያሻል፡፡

3) የታዳጊዎች ስልጠና ማዕከላት ካፈሯቸው ተጫዋቾች ዝውውር ተጠቃሚ የሚሆኑበትን አሰራር መዘርጋት፦

በሃገራችን እግርኳስ ብዙ ገንዘብ ይንቀሳቀሳል፡፡ችግሩ የዚህ ሁሉ ገንዘብ ተቀራማች አካል ያለመጠን መብዛቱ ነው፡፡ ለእግርኳሱ ምንም የማይፈይዱ ግለሰቦች ይህን የህዝብ ገንዘብ ይዘውሩታል፤ የተጠያቂነት ደረጃው እንዲያው ለይስሙላ በመሆኑ ያለ አግባብ ከሚወጣው ወጪ ኪሳቸውን እንዲሞሉ ሁኔታዎች ተመቻችተውላቸዋል፡፡ ለበርካታ ክለቦች መፍረስ ይህ ብልሹ አሰራር አንዱ ምክንያት ሆኗል፡፡ ምንም እንኳ በሃገራችን የተጫዋቾች ዝውውር አካሄድ ዙሪያ ግልጽና ተዓማኒ መረጃ ማግኘት አዳጋች ቢሆንም በሁሉም ዘንድ ቅቡል የሆነ አሰራር እንዳልተዘረጋ እሙን ነው፡፡ ወጣት ተጫዋቾችን በማፍራት ረገድ የሚጠቀሱ ክለቦችን እንዲሁም የታዳጊ ማሰልጠኛ ማዕከላትን ተጠቃሚ የማድረግ አደረጃጀት አለመፈጠሩ ብዙዎችን ጎድቷል፡፡ ክለቦችም ተጫዋቾችን የረጅም ጊዜ ኮንትራት በማስፈረምና በሌሎች ክለቦች ሲፈለጉ ኮንትራታቸውን በመሸጥ የጥቅሙ ተቋዳሽ እንዲሆኑ ማስቻል ችግሩን በመጠኑ ይቀርፈዋል፡፡ በሃገራችን ክለቦች ይህንን ከማድረግ ይልቅ በነባር ተጫዋቾች ዝውውር ላይ ሲጠመዱ ይስተዋላል፡፡ ክለቦቻችን ለተተኪዎች ትኩረት የመስጠትና ፍሬያቸውን የማየት ትዕግስት አጥተዋል፡፡ እነርሱ በዚህ ጉዳይ ላይ አጽዕኖት ሰጥተው ቢሰሩ የታዳጊ ማዕከላት የገንዘብ አቅም ከፍ ይላል፤ ክህሎት የማሰስ (Talent Scouting) ሒደቱ ይደረጃል፤ ትርፍ የማግኘት ጥረት ይጨምርና ማዕከላቱ ለዘላቂ ህልውና እንዲሰሩ ይገፋፋቸዋል፡፡ በሌላ በኩል ታዳጊዎች ከአስራ ሁለት ዓመታቸው ጀምሮ በተያዙበት የማሰልጠኛ ማዕከል በፌዴሬሽኑ ዕውቅና ያለው ምዝገባ እንዲያደርጉና ከተጫዋቾቻው ሽያጭ ተጠቃሚ የሚሆኑበትን አሰራር መዘርጋት ያስፈልጋል፡፡ በግልም ይሁን በመንግስት ስር ያሉ ማሰልጠኛ ማዕከላት ላሰለጠኑዋቸው ታዳጊዎች የማካካሻ ክፍያ ካገኙ ሌላ የተሻለ ተጫዋች ለማሳደግ ውድድር ውስጥ ይገባሉ፡፡

4. ደረጃውን የጠበቀ የእግርኳስ መሰረተ ልማት፦

በታዳጊዎች ስልጠናም ይሁን በአጠቃላይ በእግርኳስ የመሰረተ ልማት በተለይም የመለማመጃና የመጫወቻ ሜዳ አስፈላጊነት የማያጠያይቅ ነው፡፡የአገራችን ታዳጊ ተጫዋቾች በቂ የመለማመጃም ይሁን የመወዳደሪያ ሜዳ የላቸውም ፡፡ አብዛኞቹ ታዳጊዎች ሳር በለበሰ ሜዳ ላይ ለመጫወት ሃያ ዓመት እስኪሞላቸው ይጠብቃሉ – ይህም እድለኛ ከሆኑ ነው፡፡ ለዚህ ማሳያ እንዲሆነን በከተማችን ያሉ ሜዳዎችን መቃኘቱ በቂ ይሆናል፡፡ ለብዙ ዓመታት ምንም ለውጥ ያልተደረገበትን የጃን ሜዳ ማየት በራሱ ታዳጊዎቻችን ክህሎታቸውን ሊያዳብሩ የሚያስችላቸውን ሜዳዎች በአግባቡ እንደማንንከባከብ ያረጋግጥልናል፡፡ የተሻለ ጥራት ያላቸውና በዓለም አቀፍ መድረክ ተወዳዳሪ ሊያደርጉን የሚችሉ ተጫዋቾችን ማፍራት ከፈለግን በርከት ያሉ ደረጃቸውን የጠበቁ ሜዳዎችን ማዘጋጀት ያስፈልጋል፡፡

5. ብቃት ያላቸው አሰልጣኞችን ማፍራት፦

የአንድ አገር እግርኳስ እንዲያድግ ከተፈለገ በመጀመሪያ ጥራት ያላቸው አሰልጣኞች እንዲኖሩ ያስፈልጋል፡፡በ2008 ዓ.ም የወጣ አንድ ፅሑፍ ላይ እንዳነበብኩት በስፔን <Pro License> ያላቸው አሰልጣኞች ብቻ ከአስራ አምስት ሺህ በላይ ናቸው፡፡ የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን በተለያዩ ጊዜያት ለአሰልጣኞች ስልጠና  ቢያመቻችም የሚዘጋጁት ስልጠናዎች ግን በቂ አይደሉም፡፡ አብዛኞቹ ስልጠናዎች የአጭር ጊዜ (ከአስራ አምስት ቀናት ያልበለጡ) እንደመሆናቸው የይድረስ ይድረስ አዝማሚያ ይታይባቸዋል፡፡ በእኔ እምነት በተለይ ታዳጊ ላይ ለሚሰሩ አሰልጣኞች የሚሰጡ ስልጠናዎች የረጅም ጊዜ መሆን አለባቸው-ቢያንስ ለሥድስት ወራት፡፡ በረጅም ጊዜ ሥልጠና በንድፈ ሃሳብና በተግባር ላይ ያተኮሩ ትምህርቶችን በመስጠት የአሰልጣኞችን አዕምሯዊ እድገት ማዳበር ያስችላል፡፡

6. ክለቦች ላይ መተግበር ያለባቸው አስገዳጅ ህግጋትን ማውጣት፦

ታዳጊዎቻችን በክለቦች ውስጥ የማደግ እድል እንዲያገኙ፣ ክለቦቻችንንም ከኪሳራና ከመፍረስ ለመታደግ የሚያስችሉ አስገዳጅ ህጎችና ደንቦችን ማውጣት ያስፈልጋል፡፡ ለምሳሌ፡-ክለቦች በውድድር ዓመቱ ማስመዝገብ ከሚፈቀድላቸው ተጫዋቾች ውስጥ የሚበዙቱ በክለቡ ያደጉ (በታዳጊና ወጣት ቡድን ውስጥ ያለፉ) እንዲሆኑ፣ ጨዋታ በሚካሄድበት ዕለት ከሚመዘገቡ አስራ ስምንት ተጫዋቾች ውስጥ ከግማሽ በላይ የሚሆኑት በክለብ ውስጥ ያደጉ እንዲሆኑ ማስገደድ፣ በመጀመሪያ ተሰላፊነት ወደ ሜዳ ከሚገቡ ተጫዋቾች ውስጥ አምስት ያህሉ በክለቡ ያደጉ እንዲሆኑ ማድረግ ለችግሩ መጠነኛ መፍትሄ ለማበጀት ይረዳል፡፡ ከሌሎች ሃገራት የሚመጡ ግብ ጠባቂዎችን የማስፈረም ልማድ ማገድ እና የመሳሰሉትን የሚመለከቱ አስፈላጊ ህጎችን ማውጣትም ወሳኝ ነው፡፡ይህም ክለቦች አዳዲስ ተስጥኦዎችን ከታዳጊ ማሰልጠኛ ማዕከላት እንዲፈልጉ እንዲሁም እነርሱ የታዳጊና ወጣት ቡድን ስልጠናዎቻቸውን እና የተጫዋች አያያዛቸውን እንዲያሻሽሉ ያስችላቸዋል፡፡

ከላይ የተዘረዘሩት ስድስት ነጥቦች የታዳጊዎች ማሰልጠኛ ማዕከላት ላይ መስራት ስንፈልግ በጣም አስፈላጊ ናቸው ብዬ አምናለሁ፡፡ እነዚህ መሰረታዊ ሁኔታዎች ላይ ከሰራን በኋላ ደግሞ ሌሎች ስርዓተ ስልጠና (curriculm) ማዘጋጀት፣ ምልመላ፣ የጨዋታ ዘይቤ እና የመሳሰሉት ጉዳዮች ላይ መስራትና ዝርዝር እቅዶችን ማዘጋጀት በመጨረሻም ለተግባራዊነቱ መትጋት ያስፈልጋል፡፡

 


ስለ ፀሐፊው


የአስተያየቱ ፀሐፊ አሰልጣኝ ደስታ ታደሰ ነው፡፡ አሰልጣኙ ባለፉት አስር ዓመታት በበጎ ፍቃድ  ታዳጊዎችን በማሰልጠንና ለበርካታ ክለቦች በማበርከት እውቅና ባተረፈው የአስኮ እግር ኳስ ፕሮጀክት ሲያሰለጥን ቆይቷል ፡፡ከ2011 ዓ.ም ጀምሮ ደግሞ በአፍሮ-ፅዮን እግር ኳስ ክለብ ከ17 ዓመት በታች ቡድኑ አሰልጣኝ ሆኖ በመስራት ላይ ይገኛል፡፡


👉እጅዎን በተደጋጋሚ በሳሙና በአግባቡ በመታጠብ አልያም አልኮል እና ሳኒታይዘር በመጠቀም

👉ከሰዎች ጋር ንክኪ በማስወገድ

👉ከአላስፈላጊ እንቅስቃሴ በመገደብ፣ አካላዊ ርቀት በመጠበቅ እና በቤት በመቆየት ራሳችንን ከኮሮና ቫይረስ እንጠብቅ!


© ሶከር ኢትዮጵያ