የ1991 ፕሪምየር ሊግ ከፍተኛ ጎል አስቆጣሪ ሲታወስ…

በኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ስማቸውን ከተከሉ ተጫዋቾች መካከል በ1991 የፕሪምየር ሊጉ ከፍተኛ ግብ አስቆጣሪ እና አሁን በህይወት የሌለው በረከት ሀጎስ (ሮጀር) እንዲህ ዘክረነዋል።

በረከት ሀጎስ ወይንም በጓደኞቹ ዘንድ ሮጀር እየተባለ ይጠራል። ትውልድ እና ዕድገቱ በይርጋለም ከተማ ነው፡፡ በ1980ወቹ መጀመሪያ ላይ በትምህርት ቤት በመጫወት ነበር የስፖርቱን ዓለም የተቀላቀለው። ለእግርኳስ በነበረው ጥልቅ ፍቅር የተነሳ ከትምህርቱ ይልቅ ለወደደው እግርኳስ ራሱን የሰጠው የፊት መስመሩ ተጫዋች የትውልድ ከተማውን በመልቀቅም ወደ ወላይታ ተጉዞ ኑሮውን ለማድረግ ቢገደድም አልጋ በአልጋ ነገሮች ሊሆኑለት ባለመቻሉ በድጋሚ እትብቱ ወደ ተቀበረችበት ይርጋለም ዳግም ሊመለስ ችሏል፡፡ ከተመለሰ በኃላ ግን ለእግር ኳስ ይበልጥ ራሱን ሰጥቶ ስለነበረ 1985 ለደቡብ ክልል ምርጥ ተመርጦ ባሳየው አስደናቂ ብቃት የተነሳ በቀጥታ ወደ ሀዋሳ ከተማ 1987 ላይ በይፋ ለመቀላቀል ችሏል፡፡ ተጫዋቹ ወደ ሀዋሳ ከተማ ክለብ ካመራ በኃላ ሀዋሳ ከተማ እና ሀዋሳ ጨርቃጨርቅ ወደ ሱፐር ሊጉ ለማደግ ከደቡብ ክልል ተመርጠው ድሬዳዋ ላይ ለሚደረገው ውድድር ከሌሎች የሀገሪቱ ክለቦች ጋር ተወዳድረው ለማደግ በተደረገው ፉክክር ላይ ለሀዋሳ ከተማ ተሰልፎ በመጫወት አዲስ አበባን ከወከለው አየር መንገድ ጋር ተያይዘው ሲያድጉ ተጫዋቹ በቡድኑ ውስጥ ድርሻው ላቅ ያለ ነበር፡፡

በርካታ የክልል ክለቦችን ባሳተፈው በዚህ የድሬዳዋው ውድድር ላይ ሀዋሳ ከተማ ወደ ሱፐር ሊጉ ካሳደጉት ተጫዋቾች መካከል የአሁኑ አሰልጣኝ በወቅቱ የክለቡ አጥቂዎች ዘነበ ፍሰሀ እና ራሱ በረከት ሀጎስ በኢትዮጵያ ቡና ተፈለጉ። በድሬዳዋ ካሳዩት እንቅስቃሴ ባሻገር በአዲስ አበባ ስታዲየም ሀዋሳ ንግድ ባንክን በጥሎ ማለፉ በሚገጥምበትም ወቅት በተጨማሪ ያሳዩት ብቃት 1988 ላይ ኢትዮጵያ ቡና በአዲስ መልክ ሲቋቋም ለክለቡ ሁለቱም ፊርማቸውን አኑረዋል፡፡ ይሁን እና ሁለቱም ተጫዋቾች ወደ ኢትዮጵያ ቡና አምርተው ከክለቡ ጋር ደብረዘይት ላይ ዝግጅት ቢጀምሩም ከወራት ቆይታ በኃላ በረከት ከክለቡ ሲቀነስ ዘነበ ፍሰሀ ግን እዛው ቀርቷል፡፡ ዘነበ ፍሰሀም በወቅቱ በረከት ሀጎስ አቅም ቢኖረውም በቡድኑ ውስጥ የነበሩት ትልልቅ አጥቂዎች ስለነበሩ ሊሰናበት እንደቻለ አውግቶናል። “ያኔ በኢትዮጵያ ቡና ውስጥ ለመጫወት ስሄድ ከበረከት ሀጎስ ጋር ነበር የተጠራነው። እሱ ግን በቡድኑ ጋር ትንሽ ጊዜን ነው የቆየው። እኔን ግን ክለቡ ስለፈለገኝ እዛው ቀረው። የክለቡ አሰልጣኝ እኔን ጠራኝና ‘ዘነበ.. አንተ ለቡድኑ ታስፈልጋለህ። በቡድኑ ውስጥ ከነ አሰግድ ተስፋዬ፣ ካሳዬ አራጌ እና ዮሴፍ ተስፋዬ ጋር ጥሩ ነገርን ታሳያለህ። እሱን ግን ከአሁን በኃላ አንፈልገውም ንገረው።’ ተባልኩኝ። እኔም ለሱ ለመንገር ከበደኝ፤ እኔ ከሱ ሌላ ጓደኛ አልነበረኝም። አዲስ አበባንም አላውቃትም፤ ግድ ስለሆነብኝ ግን ነገርኩት። እሱም ወደ ሀዋሳ ተመለሰ።” ሲል ወቅቱን የኃሊት መልሶ አስታውሶናል፡፡

በረከት ሀጎስ ከኢትዮጵያ ቡና መልስ 1989 ላይ ወደ መጀመሪያ ክለቡ ሀዋሳ ተመልሶ መጫወት ጀምሯል፡፡ ተጫዋቹም ከገባበት ዓመት አንስቶ እስከ 1992 በሀዋሳ ከተማ አንፀባርቋል። በተለይ 1991 ላይ ተጫዋቹ ከኢትዮጵያ እግርኳስ ጋር በሚገባ የተግባባበት ዓመት ነበር። አስር ክለቦችን በወቅቱ አቅፎ ሲያወዳድር በነበረው የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ላይ ቅዱስ ጊዮርጊስ ከክልል ክለቦች ሻምፒዮና ወደ ሊጉ ባደገበት ዓመት የመጀመሪያ የፕሪምየር ሊግ ዋንጫውን መብራት ኃይልን በማስከተል ሲያነሳ በሀዋሳ ከተማ መለያ ከፊት ተሰልፎ ግቦችን ሲያስቆጥር የነበረው በረከት ሀጎስ (ሮጀር) በስምንት ግቦች የሊጉን ኮከብ ግብ አግቢነት ክብርን ለመቀናጀት በቅቷል። ተጫዋቹ ስምንት ግቦችን አገባ ተብሎ ይሸለም እንጂ አስራ አንድ ጎሎችን አስቆጥሯል፤ በስህተት ነው ቁጥሩ የቀነሰው ሲል ጋዜጠኛ ገነነ መኩሪያ (ሊብሮ) አውስቶናል “1991 አጨቃጫቂ ጉዳይ ተፈጥሮ ነበር። በረከት ሀጎስ እና አሸናፊ ሲሳይ እኩል ግቦችን ነበር ያስቆጠሩት። ነገር ግን ፌዴሬሽኑ አመዘጋገብ ላይ በነበረበት ስህተት የተነሳ አሸናፊ ሲሳይ ቀርቶ በረከት ከፍተኛ ግብ አስቆጣሪ ተብሏል።” ሲል አስታውሶናል፡፡

ከግብ ጋር የነበረው ቁርኝት እና የአጨራረስ አቅሙን እንዲሁም በግንባር የሚያስቆጥራቸው ግቦች ብዙዎች አሁንም የሚመሰክሩለት ይህ አጥቂ 1991 ላይ ሀዋሳ ከተማን ጠንካራ ተፎካካሪ በማድረግ ለዋንጫ ቅርብ እንዲሆን ከጓደኞቹ ጋር ማድረግ ቢችልም ክለቡ በቅዱስ ጊዮርጊስ ዋንጫውን ተነጥቆ የሊጉን ኮከብ ግብ አግቢነት ግን በግሉ ማሳካት ችሏል፡፡ ሀዋሳ የፕሪምየር ሊጉን ዋንጫ ሀዋሳ ከተማ ቢያጣም በዛኑ ዓመት መጨረሻ ባህርዳር ላይ በነበረው የአማራ ዋንጫ ላይ አሸናፊ ሲሆን ተጫዋቹ የማሸነፊያዋን ግብ ከመረብ አዋህዶ የዋንጫ አሸናፊ ማድረግ አስችሏል፡፡ በሀዋሳ ከተማ ቤት ከነ ያሬድ አበጀ እና ሰብስቤ ደፋር ጋር ጥሩ ጥምረትን እስከ 1992 መጨረሻ ድረስ በክለቡ ቆይታው ያሳየ ሲሆን ለኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ቢጠራም 1991 ላይ በሊጉ ያሳየውን አቅም ግን መድገም ሳይችል ቀርቷል። ተጫዋቹ 1993 ላይ በገጠመው ህመም የተነሳ ከእግር ኳሱ ከዓመት በላይ በህመም ከራቀ በኃላ ብዙ ተስፋ እየተጣለበት የተጠበቀውን ያህል ረጅም አመታት መጫወት ሳይችል ታህሳስ 28 ቀን 1994 ላይ ህይወቱ አልፏል፡፡

👉እጅዎን በተደጋጋሚ በሳሙና በአግባቡ በመታጠብ አልያም አልኮል እና ሳኒታይዘር በመጠቀም

👉ከሰዎች ጋር ንክኪ በማስወገድ

👉ከአላስፈላጊ እንቅስቃሴ በመገደብ፣ አካላዊ ርቀት በመጠበቅ እና በቤት በመቆየት ራሳችንን ከኮሮና ቫይረስ እንጠብቅ!


© ሶከር ኢትዮጵያ

error: