ይህን ያውቁ ኖሯል? | ስለ አዲስ አበባ ስታዲየም…

በዛሬው ይህንን ያውቁ ኖሯል አምዳችን ስለ አዲስ አበባ ስታዲየም ምናልባትም የማያውቋቸው እና ሊያውቋቸው የሚገቡ ዕውነታዎችን እንደሚከተለው አሰናድተናል።

እድሜ ጠገቡ የአዲስ አበባ ስታዲየም የሃገር ውስጥ እና ዓለማቀፍ ውድድሮችን ለዓመታት ያስተናገደ ሲሆን ከውድድሮቹ ጎን ለጎን የተለያዩ ሁነቶችም በቋሚነትና በጊዜያዊነት ሲከወኑበት ቆይቷል። ይህ አንጋፋ ስታዲየም አሁን “ጊዜ ጥሎት” እንደ ከዚህ ቀደሞቹ ወቅቶች የውድድሮች ብቸኛ መደረጊያ ስፍራ ባይሆንም ያሳለፋቸው በርካታ ታሪኮች እየተነሱ ሲወደስ ይኖራል። ሶከር ኢትዮጵያም ዛሬ በምትጀምረው በይህን ያውቁ ኖሯል አምዷ ስለ ስታዲየሙ ሊታወቁ ስለሚገባቸው ነጥቦችን ታነሳለች።

ከተለያዩ ምንጮች ባሻገር በአሻም ቲቪ ገነነ መኩርያ ስለ ስታዲየሙ ያዘጋጀው ፕሮግራምን እንደ ዋነኛ የመረጃ ምንጭ ተጠቅመናል።

1 – የአዲስ አበባ ስታዲየም ስፖርታዊ ክንውኖችን ከማስተናገዱና ታጥሮ የስፖርት ማዘውተሪያ ቦታ ተብሎ ከመሰየሙ በፊት “ሰንጋ ተራ” የሚባል የከብቶች መሸጫ ነበር። በተለይ ከ1930ዎቹ በፊት ጥቅጥቅ ያለ ጫካ የነበረው የአሁኑ የመዲናዋ ስታዲየም የራስ ብሩ ከብቶች ውሃ ማጠጫ ሆኖ ሲያገለግል እንደነበረ ይነገራል። ከዚህ በተጨማሪም ጫካው የእንስሳት (ውሻ) ማስወገጃ እና ቆሻሻ መጣያ ቦታ እንደነበረ ይሰማል።

2 – የአዲስ አበባ ስታዲየም ለስፖርታዊ ክንውኖች እንዲሆን የተደረገውና የስታዲም መልክ ኖሮት እንዲገነባ መሰረተ ድንጋይ የተጣለው ጥቅምት 23 ቀን 1940 ዓ/ም ነው። ከ1940 በፊት በነበሩት ጥቂት ዓመታትም ቦታው በእሾህ፣ ጥድ እና መሰል አጥሮች ታጥሮ የእግርኳስ ጨዋታዎች የሚከወኑበት ሜዳ ነበር። በእግርኳስ ታሪካችን ውስጥ ጉልህ ስም የነበራቸው ይድነቃቸው ተሰማ ግርማዊ ቀዳማዊ ኃይለሥላሴን አስፈቅደው በ1939 የስታዲየሙ ካርታ እንዲወጣ አድርገዋል። በዛን ጊዜ የመዲናዋ የመሐል ከተማ ፒያሳ ስለነበረና የአሁኑ ስታዲየም አካባቢ የነበረው ቦታ የከተማ ጫፍ ተደርጎ ስለሚታሰብ ይድነቃቸው ፍቃድ ለማግኘት እንዳልተቸገሩ ይነገራል።

3 – የአዲስ አበባ ስታዲየም ሲገነባ 200 ቅርጫት እንቁላል ፈጅቷል። እንቁላሉ እንደ ሲሚንቶ እንዲያገለግልና የሚገነባው ስታዲየም ጥንካሬ እንዲኖረው በማሰብ ይህንን ያክል እንቁላል ለግንባታው እንዳገለገለ ይነገራል።

4 – ስታዲየሙ ደረጃውን ጠብቆ ገንብቶ ለማጠናቀቅ በመዘግየቱ ምክንያት በ1953 ሊደረግ የነበረው የአፍሪካ ዋንጫ በአንድ ዓመት መራዘሙ ይነገራል። በ1953 የተደረገውና በተለምዶ “የታኅሣሥ ግርግር” በሚል የሚራው የመፈንቅለ መንግሥት ሙከራም ለአፍሪካ ዋንጫው መስተጓጎል እንደምክንያት የሚነሳ ሌላው የታሪክ አጋጣሚ ነው።

5 – በ1953 ዓም የኢትዮጵያ እግርኳስ ፌደሬሽን ፕሬዝዳንት የነበሩት ሌተናል ኮሎኔል ታምራት ይገዙ ስታዲየሙን በተሻለ መልኩ እንዲሰራ አድርገዋል። ፌደሬሽኑን ለ16 ዓመታት በፕሬዝዳንትነት ያገለገሉት አቶ ታምራት በተለይ ስታዲየሙ በተሻለ መልኩ እንዲታጠርና መብራት እንዲኖረው እንዳደረጉ ታሪክ ይናገራል።

6 – የአዲስ አበባ ስታዲየም የተገነባው በወንዝ ላይ ነው። በአካባቢው ያለ ወንዝ አሁንም ድረስ ስታዲየሙን በስር አቋርጦ እንደሚያልፍ ይነገራል።

7 – የመጫወቻ ሜዳውን እና ትሪቡን አካባቢ የነበረውን የስታዲየሙ ክፍል በ1953 ዓ/ም ያደሰው መሀንዲስ ሶሌል ቦኒህ ይባላል። ይህ መሀንዲስ እስራኤላዊ ነው።

8 – አዲስ አበባ ስታዲየም ከ1953 ጀምሮ እስከ 1967 ድረስ ይፋዊ ሥያሜው ቀ/ኃ/ሥ ስታዲየም የነበረ ሲሆን ከደርግ መንግሥት መምጣት በኋላ ወደ አዲስ አበባ ስታዲየም ተቀይሯል። ስታዲየሙ ከሁለቱ ሥያሜዎች በፊት በተለምዶ ካምቦሎጆ ይባል እንደነበረም ይነገራል።

9 – ኢትዮጵያ ለመጀመርያ ጊዜ ባስተናገደችው 3ኛው የአፍሪካ ዋንጫ (1954) ስታዲየሙ ያለ መብራት የአህጉሪቱን ትልቁን የፍፃሜ ጨዋታ ተከናውኖበታል። በጊዜው ቀ/ኃ/ሥላሴ አርፍደው ወደ ስታዲየም በመምጣታቸው የሚጀመርበት ሰዓት እንደተገፋ እና ጨዋታው በመደበኛ ክፍለ ጊዜ አቻ ተጠናቆ ወደ ተጨማሪ ደቂቃ በመሸጋገሩ ጨዋታው ሲጠናቀቅ ለዓይን ያዝ እንዳደረገ (እንደመሸ) ይነገራል።

10 – የአዲስ አበባ ስታዲየም ፓውዛ (የመብራት ምሰሶ) የተተከለው 1959 ዓ/ም ነው። በተለይ ፓውዛው ለ6ኛው የአፍሪካ ዋንጫ (1960) እንዲደርስ ተፈልጎ እንደተተከለ ታሪክ ያስረዳል። ከጀርመን ሃገር በመጡ ባለሙያዎች የተተከለው ይህ የመብራት ማማ እስካሁን እንዳልተቀየረ ይነገራል።

11 – የስታዲየም ክፍሎች (Stand) ሥያሜዎች ከይፋዊ ይልቅ በተለምዶ በወጡ ስያሜዎች ሲጠሩ ይስተዋላል። ክቡር ትሪቡን፣ ጥላ ፎቅ፣ ከማን አንሼ፣ ፋሲካ በር፣ ዳፍ ትራክ፣ ሚስማር ተራ፣ ካታንጋ የሚሉ መጠርያዎች በስፖርት አፍቃሪያን ዘንድ የተለመዱና በሌሎች ስታዲየሞችም ለመጠርያነት ሲያገለግሉ የሚስተዋሉ ናቸው። ከመጠርያዎቹ ጀርባ ያሉ መነሻ ምክንያቶች ፡-

– “ሚስማር ተራ” የሚባለው የስታዲየም ክፍል የተሰየመው የጭንቅላት መከላከያ ቆብ (ሄልሜት) የሚያደርጉ ወታደሮች በዚህ ቦታ ስለሚገቡ እና ጭንቅላታቸው ላይ የሚያደርጉት ሄልሜት እንደ ሚስማር ቆብ ስለሚታይ ነው ቦታው ሚስማር ተራ የተባለው ተብሎ ይነገራል።

– ካታንጋ የተባለው የስታዲየም ክፍል በተመሳሳይ የተሰየመው ከወታደሮች ጋር በተያያዘ ነው። ኮንጎ ዲ/ሪ በሚገኘው ካታንጋ ግዛት ሠላም ለማስከበር ዘምተው የነበሩት የሃገራችን ወታደሮች ከግዳጃቸው መልስ ስታዲየም ሲገቡ ይቀመጡ የነበረው በአሁኑ አጠራር ካታንጋ በተባለው የስታዲየሙ ክፍል ነበር። ከዚህ መነሻነት ይህ የስታዲየሙ ክፍል ካታንጋ ተብሎ እንደተሰየመ የታሪክ አዋቂዎች ያነሳሉ።

– ፋሲካ በር የተባለው የስታዲየም ክፍል ደግሞ ስያሜውን ያገኘው በአንድ የቅዱስ ጊዮርጊስ እና የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን ቀንደኛ ደጋፊ እንደሆነ ይወሳል። ፋሲካ ዳቢያን የተባለው ይህ ደጋፊ በዋናነት መምህር የነበረ ሲሆን ጨዋታዎች ሲኖሩ ግን ወደ ስታዲየም በመግባት የሚደግፈውን ቡድን በንቃት ሲያነቃቃ እንደነበረ ይነገራል። ይህንን ደጋፊ ለማየትና የእርሱን የተለየ የድጋፍ አሰጣጥ ለመመልከት ከተለያዩ የስታዲየሙ ክፍሎች “ፋሲካን እንይ” በማለት ወደ እርሱ ስለሚጓዙ ቦታው በስሙ ፀንቶ እንደቀረ ይነገራል።

12 – የአዲስ አበባ ስታዲየም የመሮጫ መም (ትራክ) ተገንብቶ የተመረቀው ግንቦት 16 ቀን 1983 ዓ/ም ነው።

13 – የአዲስ አበባ ስታዲየም መቀመጫ ወንበሮች የተገጠሙት የካቲት 1993 ዓ/ም ነበር። እርግጥ በ1986 አግዳሚ ወንበር ትሪቡን በሚባለው የስታዲየም ክፍል እንደገባ ይነገራል። ነገር ግን በጊዜው የነበሩ ደጋፊዎች ደስታቸውን ለመግለፅ ስላልተመቻቸው ይህንን አግዳሚ ወንበር አንስተው እንደወረወሩት ይገለፃል።

14 – የአዲስ አበባ ስታዲየም በአሁኑ ወቅት 12 የተመልካቾች መግቢያ በሮች አሉት።

15 – ስታዲየም ዙሪያ ያሉት የንግድ ሱቆች የተሰሩት ለ10ኛው የአፍሪካ ዋንጫ ነው። ከዛ በፊት ቦታው የቆሻሻ መጣያ እንደነበር ታሪክ ያወሳል።

16 – አዲስ አበባ ስታዲየም ከኢትዮጵያ እግርኳስ ጋር የተቆራኙ ታሪካዊ ጨዋታዎች እንዲሁም በርካታ ኃይማኖታዊ እና ፖቲካዊ ሁነቶች ተስተናግደውበታል። ስታዲየሙ ሦስት የአፍሪካ ዋንጫዎች ከማስተናገዱ ባሻገር አራት የሴካፋ ዋንጫ እና የወጣቶች የአፍሪካ ዋንጫን አስተናግዷል። የአፍሪካ አትሌቲክስ ሻምፒዮናን የመሳሰሉ ሌሎች የስፖርት ክንውኖችም በተጨማሪነት አስተናግዷል።

17 – ኢትዮጵያ ባስተናገደቻቸው ሦስት የአፍሪካ ዋንጫዎች 44 ጨዋታዎች ሲካሄዱ አዲስ አበባ ስታዲየም ሦስት የፍፃሜ ጨዋታ ጨምሮ 31 ጨዋታዎችን በማስተናገድ ከፍተኛውን ሚና ተጫውቷል። የአስመራው ንግስተ ሳባ ስታዲየም እና የድሬዳዋው አስፋወሰን ስታዲየም (የወቅቱ መጠርያዎች) እያንዳንዳቸው 7 እና 6 ጨዋታ አስተናግደዋል።

18 – እስከ 2005 ድረስ በአዲስ አበባ አበበ ቢቂላ እና ድሬዳዋ ስታዲየሞች ከሚደረጉ ጥቂት ጨዋታዎች ውጪ ያለ እረፍት የብሔራዊ ቡድኖችን ጨዋታ ያስተናገደው የአዲስ አበባ ስታዲየም ባለፉት ስምንት ዓመታት የተሻለ ጥራት ያላቸው ስታዲየሞች በሀገሪቱ እየተገነቡ መሆናቸውን ተከትሎ ጫናው እየቀነሰለት መጥቷል። በወንዶች ብሔራዊ ቡድን ደረጃ ከተደረጉ ያለፉት 10 ጨዋታዎች እንኳ በዚህ ስታዲየም የተስተናገደው 1 ጨዋታ ብቻ ነው።

19 – የኢንተርናሽናል ብቻ ሳይሆን በሀገር ውስጥ ጨዋታዎችም ለ70 ዓመታት የሀገሪቱ እግርኳስ ማዕከል የነበረው አዲስ አበባ ስታዲየም አሁን አሁን ከአዲስ አበባ ክለቦች ቁጥር መመናመን ጋር በተያያዘ የሚያስተናግደው ቁጥር በእጅጉ ቀንሷል። ለአብነትም በ1995 በፕሪምየር ሊጉ በአጠቃላይ ከተደረጉ 156 ጨዋታዎች 91 ጨዋታዎች በአዲስ አበበ ስታዲየም ሲደረጉ በዘንድሮ ግማሽ ዓመት ከተደረጉ 120 ጨዋታዎች አአ ላይ የተከናወኑት ከ25 አይዘሉም።

20 – በአሁኑ ሰዓት ስታዲየሙ አህጉራዊ እና ዓለማቀፋዊ ጨዋታዎችን እንዳያከናውን በካፍ እግድ ተጥሎበታል። በተለይ ስታዲየሙ ከመጠን በላይ ማርጀቱ እና የጥገና ስራዎች በአግባቡ አለመከናወናቸው እግዱን እንዳመጣውና ለዓለማቀፍ ጨዋታዎች ብቁ እንዳይሆን እንዳደረገው ይታወቃል።

👉እጅዎን በተደጋጋሚ በሳሙና በአግባቡ በመታጠብ አልያም አልኮል እና ሳኒታይዘር በመጠቀም

👉ከሰዎች ጋር ንክኪ በማስወገድ

👉ከአላስፈላጊ እንቅስቃሴ በመገደብ፣ አካላዊ ርቀት በመጠበቅ እና በቤት በመቆየት ራሳችንን ከኮሮና ቫይረስ እንጠብቅ!


© ሶከር ኢትዮጵያ