ቆይታ ከፋሲል ከነማው ተስፈኛ ተጫዋች ኪሩቤል ኃይሉ ጋር

በዛሬው የተስፋኞች አምዳችን ከሁለገብ የተከላካይ እና የተከላካይ አማካኝይ ስፍራ ተጫዋቹ ኪሩቤል ኃይሉ ጋር አጠር ያለ ቆይታ አድርገናል።

የኢትዮጵያ ወጣቶች ስፖርት አካዳሚ ካፈራቸው እና በጉልህ ስማቸው ከሚጠቀሱ ተጫዋቾች መካከል አንዱ የሆነው በጎንደር ከተማ ተወልዶ ያደገው ኪሩቤል ኃይሉ እግር ኳስን በሚማርበት ትምህርት ቤት በደብረ ሠላም ካቶሊክ ትምህርት ቤት ፕሮጀክት ነው የጀመረው። በመቀጠል ወደ ኢትዮጵያ ወጣቶች ስፖርት አካዳሚ በማቅናት አራት ዓመትን ካሳለፈ በኋላ ለኢኮስኮ እና ደሴ ከተማ የመጫወት ዕድል ያገኘ ሲሆን በድሬድዋ ከተማው የዮሃንስ ሳህሌ ስብስብ ውስጥ ለመካተት ከጫፍ ደርሶ ከደሴ ጋር የነበረው ውል ባለማብቃቱ መልቀቂያውን ሳያገኝ የ2011 ወድድር ዓመትን እዛው ደሴ ከተማ ሊቀጥል ችሏል። ኪሩቤል ዓመቱ መጨረሻ ላይም ወደ ደደቢት አምርቶ ለተወሰነ ጊዜ ከቡድኑ ጋር ልምምድ ሲሳራ የቆየ ቢሆንም በተመሳሳይ መልቀቂያውን ባለማግኘቱ ሳይሳካ ቀርቷል። ዓመቱ ሲጠናቀቅ በወጣት ተጫዋቾች ዕምነት ባለው አሰልጣኝ ውበቱ አባተ የተፈለገው ተጫዋቹ ከደሴዎች ጋር በድርድር በመለያየት ወደ ትውልድ ከተማው ጎንደር ተመልሶ ፋሲል ከነማን መቀላቀል ችሏል። ፋሲል ለኮንፌደሬሽን ዋንጫ ዝግጅት ላይ በነበረበት ወቅት ክለቡን የተቀላቀለው ኪሩቤል በወራት ቆይታው ብቻ በዚህ ኢንተርናሽናል ወድድር ላይ የተሳተፈው የመጨረሻ 18 ቡድን ውስጥ ገብቶ የነበረ መሆኑም ይታወሳል። ኪሩቤል ኃይሉ በአካዳሚ እና በሦስቱ ክለቦች ስላሳለፈው ጊዜ ፣ ስለወደፊት ህልሙ እና ስለሚያደንቀው ተጫዋች ይህንን ብሎናል።

” እግር ኳስን የጀመርኩት ትምህርት ቤት ውስጥ በፕሮጀክት ነበር። ከዚያም በህርዳር ውድድር ላይ ከተማው ላይ ያሉት አሰልጣኞች አዩኝ። ከዚያ ከተማው ላይ ያለ ፕሮጀክት ለአጭር ጊዜ ሰርቼ ነበር 2005 ዓ.ም ላይ ሻሸመኔ ለውድድር በሄድኩበት ወቅት ለአካዳሚ የተመረጥኩት። ያው የመጀመሪያ ስለነበርን ብዙ ፈተናዎች ነበሩ። እንዲሁም ጥሩ የሚባሉ አጋጣሚዎችም ነበሩ። በመጀመሪያ ወደዛ ለመሄድ ቤት ሳስፈቅድ ቤተሰቤቼ ደስተኛ አልነበሩም። ለእናቴ ነበር የነገርኳት ፤ አባቴን ትንሽ ስለምፈራው ኳስም ስጫዎት ደስተኛ ስላልሆነ መናገር ከብዶኝ ነበር። ኳስ ስጫወትም የሚደግፉኝ እህቶቼ ናቸው ፤ በትጥቅም ያግዙኝ ነበር። እነሱ እናቴ ላይ ጫና አድርገው እኔም ፍላጎቴ እንደሆነ በግልጽ ነግሬው ‘ፍላጎትህ ከሆነ አልጫንህም’ ተባልኩ። ወደ አካዳሚ ከሄድኩ በኋላ በጣም የሚደግፉኝ ብዙ ሰዎች አግኝቻለው። እንደ ትንሳኤ ካሳ (ቡቹ) እንዲሁም አሰልጣኝ ተገኘ ዕቁባይ ያሉ ባለሙያዎች በርካታ ነገሮች አድርገውልኛል። በእርግጥ በጣም ብዙ ሰዎች አሉ ድጋፍ ያደረጉልኝ በስም መዘርዘር ስለሚበዙ እንጂ።


” አካዳሚ የነበረኝ ቆይታ ሲጠናቀቅ ብዙ የክለብ ጥያቄዎች ነበሩ። ንግድ ባንክ ፣ ደደቢት እና አዳማ ከተማ ጥያቄ አቅርበውልኝ አዳማ ስሄድ የጠበኩት ዋናው ቡድን ላይ በቢጫ መጫወት ነበር። ግን ተስፋ ወርጄ እንድጫወት ሲጠይቁኝ አዳማን ትቼ ኢኮስኮ ሙከራ አለ ሲባል ወደዛ ሄድኩ ፤ ዱከም ነበር ሙከራው። እሱን አልፌም በቢጫ ሁለት ዓመት ፈረምኩ። ከአሰልጣኝ ደግአረገ ይግዛው ጋር ስድስት ወር በኋላ ደሴ ከነማ ጥያቄ ሲያቀርብልኝ 2010 ግማሽ ላይ ወደዛ አመራሁ። እዛም ከፈረምኩ በኋላ ነገሮች የተለዩ ነበሩ ፤ የቡድኑ ቁልፍ ተጫዋች መሆንም ቻልኩ። እስከለቀኩበት ጊዜ በርካታ ጨዋታዎችን ያለማቆረጥ አድርጊያለሁ ፤ ከጨዋታ ጨዋታ በጣም ራሴን አሻሽያለሁ። ውድድር ዓመቱ ሲያልቅ ባህርዳር ላይ ዝግጅት ላይ የነበረው ድሬድዋ ከነማ ጋር ሙከራ አደረኩ። አራት ቀን እንደሞከረኝ አሰልጣኝ ዮሃንስ ሣህሌ ‘አስፈርምሀለሁ መልቀቂያ አምጣ’ አለኝ። ሆኖም የደሴ ደጋፊዎች ደስተኛ አልነበሩም ፤ ውልም ስለነበረኝ ቀጣይ ዓመት እዛው ለመቆየት ተገደደኩ። ከደደቢትም ጋርም የተወሰነ ጊዜ አብሬ መስራት ችዬ በድጋሜ በመልቀቂያ ችግር ነበር የተበላሸብኝ። ሆኖም ዓመቱ ሲጠናቀቅ ፋሲል ከነማ ጥያቄ ሲያቀርብ ደሴዎች እንቢ ማለት ስለከበዳቸው ለቀቁኝ። ፋሲል ስመጣ ጥሩ ነገር ጠብቄ ነው የመጣሁ ፤ የመጫዎት ጉጉት ስነበረኝ። በደሴ ከተማ ከምለው በላይ ደስተኛ ነበርኩ። ደጋፊዎቹም ክለቡም ለኔ ጥሩ ነገር ነበራቸው። ግን ፕሪምየር ሊግ ለመጫወት የነበረኝ ጉጉት ከክለቡ ጋር እንድለያይ አድርጎኛል።
“በፕሪምየር ሊጉ ላይ አዲስ እንደ መሆኔ የመጀመሪያ እና ሁለተኛ ጨዋታዎቼን ከጅማ አባ ጅፋር እና ወልዋሎ ዓዲግራት ዩኒቨርስቲ ጋር ሳደርግ ጨዋታው በጣም አሪፍ ነበር። ፕሪምየር ሊጉ ከከፍተኛ ሊግ ይልቅ ደስ ይላል። አቅሜን አውጥቼ በመሰራት የተሻለ ተጫዋች ለመሆንም እፈልጋለሁ። ለወደፊት በኢንተናሽናል ደረጃ መጫወት እና ሀገሬን ማገልገል ነው።

” የባርሴሎናው ሰርጂዮ ቡስኬት አድናቂ ነኝ። የመሀል ተከላካይ እና የተከላካይ አማካይ ስፍራ ላይ መጫዎት እችላለሁ። አሰልጣኝ ውበቱ አባተም በሁለቱ ቦታ እያጫውተኝ ነበር። እኔ የተከላካይ አማካይ ስፍራ ላይ መጫወት ይበልጥ ያስደስተኛል። ”

👉እጅዎን በተደጋጋሚ በሳሙና በአግባቡ በመታጠብ አልያም አልኮል እና ሳኒታይዘር በመጠቀም

👉ከሰዎች ጋር ንክኪ በማስወገድ

👉ከአላስፈላጊ እንቅስቃሴ በመገደብ፣ አካላዊ ርቀት በመጠበቅ እና በቤት በመቆየት ራሳችንን ከኮሮና ቫይረስ እንጠብቅ!


© ሶከር ኢትዮጵያ

error: