ይህንን ያውቁ ኖሯል? (፪) | ስለኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ እና ክለቦች

በዛሬው ይህንን ያውቁ ኖሯል? አምዳችን ሁለተኛ ክፍል የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ 10 ዕውነታዎችን የምናነሳ ይሆናል።

የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ በአዲስ መልክ 1990 ዓ/ም ላይ ከተጀመረ በኋላ የተለያዩ ታሪኮች እና እውነታዎች ተመዝግበዋል። ሶከር ኢትዮጵያም ሀሙስ በምታስነብበው ይህንን ያውቁ ኖሯል? አምዷ ሊጉ እና ክለቦችን የተመለከቱ ዕውነታዎችን ከሳምንት ጀምሮ እያቀረበች ትገኛለች። ለዛሬም ከሳምንት የቀጠለውን ክፍል ታቀርባለች።

1 – በአንድ ጨዋታ 2 ክለቦች በድምሩ ብዙ ጎል ያስቆጠሩበት ጨዋታ በ1994 ዓ/ም የተደረገ ነው። በዚህ የውድድር ዘመን በተደረገ የመጨረሻ ሳምንት ጨዋታ የተገናኙት ቅዱስ ጊዮርጊስ እና መብራት ኃይል በድምሩ 13 ጎሎችን አስቆጥረዋል። ጨዋታውም በቅዱስ ጊዮርጊስ 8-5 አሸናፊነት ተጠናቋል።

2 – በሊጉ የ22 ዓመት ታሪክ በአንድ የውድድር ዘመን አነስተኛ ክለቦች የተሳተፉበት ዓመት በ1990 ሆኖ ተመዝግቧል። በዚህም 8 ክለቦች (መብራት ኃይል፣ ኢትዮጵያ መድን፣ ኢትዮጵያ ቡና፣ ሃዋሳ ከተማ፣ ድሬዳዋ ጨርቃጨርቅ፣ ጉና ንግድ፣ ኮምቦልቻ፣ ፐልፕና ወረቀት) ብቻ በሊጉ ውድድር አከናውነዋል።

3 – በተቃራኒው በአንድ የውድድር ዘመን በርካታ ክለቦች የተሳተፉበት ዓመት 2000 ላይ ነው። በዚህ ዓመት በሊጉ 25 ክለቦች ተሳትፈዋል።

4 – በአንድ የውድድር ዘመን በርካታ ጎሎችን ያስተናገደው ክለብ ሀረር ከተማ ነው። ሀረር ከተማ በ1993 ዓ/ም በተደረገው የሊጉ ውድድር ላይ 61 ጎሎችን በ26 ጨዋታ አስተናግዷል። ይህም ቁጥር ሀረር ከተማን በጨዋታ ብዙ ጎሎችን (2.34) የሚያስተናግድ የሊጉ ክለብ አድርጎታል።

5 – በአንድ የውድድር ዓመት ብዙ ጎሎችን ተጋጣሚ ላይ ያስቆጠረው ክለብ ደደቢት ነው። ቡድኑ በ2005 በታሪኩ ብቸኛ የሊግ ዋንጫ ባነሳበት ዓመት 64 ግቦችን በ26 ጨዋታ ተጋጣሚ ላይ አስቆጥሯል። ከዚህ በተጨማሪም ደደቢቶች በዚህ የውድድር ዓመት ያስቆጠሩት 64 ጎሎች በጨዋታ ከፍተኛ ግብ የማስቆጠር ነፃሬ (2.46) እንዲኖራቸው በማድረግ በሊጉ ጥሩ ግብ የማስቆጠር ንፃሬ ያለው ቀዳሚ ክለብ አድርጓቸዋል።

6 – በአንድ የውድድር ዓመት ብዙ ጨዋታዎችን የተሸነፈው ክለብ ሜታ ቢራ ነው። ክለቡ ለመጨረሻ ጊዜ በሊጉ በተሳተፈበት 2002 ዓ/ም ባደረጋቸው 34 ጨዋታዎች 24ቱን በሽንፈት አገባዷል። ከአጠቃላይ የ1 ዓመት የጨዋታ ብዛት አንፃር ግን በርካታ ጨዋታዎችን የተረታው ክለብ አርባምንጭ ጨርቃጨርቅ ነው። ቡድኑ በ1997 ካደረጋቸው 26 ጨዋታዎች 80.7% (21) በሽንፈት አጠናቋል።

7 – በአንድ የውድድር ዓመት ምንም ጨዋታ ሳይሸነፍ ዋንጫ ያነሳው ክለብ ቅዱስ ጊዮርጊስ ነው። ቡድኑ በ2000 ሰባተኛ የፕሪምየር ሊግ ዋንጫውን ወደ ካዝናው ሲያስገባ በ24ቱም ጨዋታዎች እጅ ሳይሰጥ ነው። ይህም እውነታ ቅዱስ ጊዮርጊሶችን ብቸኛ ያደርጋቸዋል።

8 – በአንድ የውድድር ዘመን አነስተኛ ግብ ያስተናገደው ክለብ ቅዱስ ጊዮርጊስ ነው። ቡድኑ በኢትዮጵያ ሚሌኒየም 24 ጨዋታዎችን አከናውኖ 7 ጎሎችን ብቻ ነበር ያስተናገደው። በተጨማሪም ጊዮርጊሶች በ1991 ዓም በተደረጉ 18 የሊጉ ጨዋታዎች 10 ጎሎችን ብቻ በማስተናገድ ሁለተኛውንም ስፍራ ይዘዋል።

9 – በአንድ የውድድር ዓመት ምንም ጨዋታ ያላሸነፈው ብቸኛ ክለብ ፊንጫ ስኳር ነው። ቡድኑ በ2003 ዓ/ም ባደረጋቸው 30 የሊግ ጨዋታዎች አንዱንም ሳያሸንፍ ከሊጉ ተሰናብቷል።

10 – በአንድ የውድድር ዘመን ብዙ አቻ ውጤቶችን ያስመዘገበው ክለብ አዳማ ከተማ ነው። አዳማ በ2001 ዓ/ም ባደረጋቸው 30 የሊግ ጨዋታዎች 18ቱን በአቻ ውጤት አገባዷል። ከ18ቱ የአቻ ውጤቶች ገሚሶቹ ደግሞ ያለ ግብ 0-0 የተጠናቀቁ ናቸው። ከአዳማ በመቀጠል ብዙ የአቻ ውጤቶችን በአንድ የውድድር ዘመን ያስመዘገበው ክለብ ሀረር ቢራ ነው። ሀረር በ2002 ዓ/ም 17 አቻዎች በ34 የሊጉ መርሃ ግብር አስመዝግቧል።

👉እጅዎን በተደጋጋሚ በሳሙና በአግባቡ በመታጠብ አልያም አልኮል እና ሳኒታይዘር በመጠቀም

👉ከሰዎች ጋር ንክኪ በማስወገድ

👉ከአላስፈላጊ እንቅስቃሴ በመገደብ፣ አካላዊ ርቀት በመጠበቅ እና በቤት በመቆየት ራሳችንን ከኮሮና ቫይረስ እንጠብቅ!


© ሶከር ኢትዮጵያ