ስለ አንዱዓለም ነጋ (ቢጣ) ሊያውቋቸው የሚገቡ እውነታዎች

በ1990ዎቹ የኢትዮጵያ እግርኳስ ከታዩ ድንቅ የተከላካይ ስፍራ ተጫዋቾች መካከል ነው። ተክለ ቁመናው በተለምዶ “ተከላካዮች ግዙፍ መሆን ይገባቸዋል” ከሚለው አባባል በተቃራኒ ቢሆንም ብልህ እና ታጋይ ነው። ለሀዋሳ ከተማ ወርቃማ ዘመናት ተጠቃሽ ከሆኑት ተጫዋቾች አንዱ የሆነው የቀድሞው የሀዋሳ ከነማ፣ ሰበታ ከነማ እና ሲዳማ ቡና ተከላካይ አንዱዓለም ነጋ (ቢጣ) ማነው ?

ከ1990ዎቹ አጋማሽ ጀምሮ በሀዋሳ አብሮት የተጫወተው የአሁኑ አሰልጣኝ ሙሉጌታ ምህረት ስለ አንዱዓለም ነጋ እንዲህ ሲል ይናገራል “በምን ዓይነት ቃል ልግለፀው ? ጎበዝ ተጫዋች ነው ፤ ሙያውን አክባሪ ፣ ፈጣን ፣ ጠንካራ እና ፍሌክሰብል፣ መሸነፍን የማይወድ እና ከሰው ጋር በደንብ ተነጋግሮ የሚሰራ ነው። ለእኔ በእግርኳስ ህይወቴ ካየኋቸው የተሟሉ ተከላካዮች መካከል የመጀመሪያው ነው፡፡ በማኅበራዊ ህይወቱም ከስፖርተኛውም ከሁሉም ጋር ተግባብቶ ተጫውቶ የሚያሳልፍ ሰው ነው፡፡ ጥሩ ተጫዋችነትን ከምርጥ ስብዕና ጋር አካቶ የያዘ ነው። ቁመቱ አጭር ቢሆንም ሁሉም ኳሊቲዎች አሉት። ኳስ ይዞ ነው የሚጫወተው ፤ አሁን በዘመናዊ እግርኳስ ተከላካዮች የሚጫወቱትን ያህል እሱም ይጫወት ነበር፡፡ ብዙዎችም ቅፅል ስም ይሰጡት ነበር። የኢትዮጵያ ቡናው ተከላካይ ሳሙኤል ደምሴ (ኩኩሻ) ይሉታል። እኛ ኩኩሻን በደንብ አላየነውም ግን ስንሰማም የዚያን ያህል ስም ከወጣለት ምን ዓይነት ተጫዋች እንደሆነ መገመት ይቻላል። ኩኩሻ ከተባለ ኩኩሻን የሚያውቅ ቢጣ ምን ዓይነት ነው የሚለውን ይረዳዋል። ሙሉ ተጫዋች ነው ፤ መሸነፍ የሚባል ነገርን በልምምድም ሆነ በጨዋታ የማይፈልግም ጭምር ነው። በሄደበት ክለብ ሁሉ ተጫዋቾችም ሆኑ አሰልጣኞች ይወዱታል።”

አንዱዓለም ትውልዱ በባሌ-ጎባ ከተማ ቢሆንም ወታደር አባቱ በዝውውር ምክንያት ሀዋሳ በመመደባቸው የሦስት ወር ልጅ ሆኖ ከቤተሰቡ ጋር ወደ ሀዋሳ አመራ። ዕድሜው እየገፋ የታዳጊነት ደረጃ ላይ ሲደርስ እግርኳስን በሰፈር እና በፕሮጀክት ውስጥ ተጫውቶ አሳልፎ ነው በትልቅ ደረጃ ወደነገሰበት ሀዋሳ ከተማ ያመራው፡፡ 1991 ላይ ጥቂት ወራትን በአሰልጣኝ ከማል አህመድ የፕሮጀክት ቡድን ውስጥ ሲሰለጥን ቆይቶ በወቅቱ አሰልጣኙ ሀዋሳ ከነማንም ያሰለጥኑ የነበረ በመሆኑ ሊመቻቸው ስላልቻለ ወደቀድሞው የሀዋሳ ከነማ እና የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ረዳት አሰልጣኝ ታመነ ይርዳው ፕሮጀክት ተዘዋውሮ ለሦስት ዓመት ከግማሽ ቆይቶ ራሱን በደንብ ማዳበር ችሏል፡፡ ሰውነቱ ደቃቃ ይምሰል እንጂ ገና በልጅነቱ ጠንካራ አቅሙን ማሳየት የጀመረው “ቢጣ” በሀዋሳ ከተማ ውስጥ ከሚዘጋጁ የውስጥ ውድድሮች ተንስቶ ክልሉንም ወክሎ መጫወት ችሏል፡፡ በዚሁ ፕሮጀክት ውስጥም እያለ ለመጀመሪያ ጊዜ ሚዛን ተፈሪ ላይ በነበረው የ17 ዓመት በታች ውድድር ላይ ተመርጦ በመጫወት በሀገርዓቀፍ ውድድር ላይም መካፈል ችሏል።

በፕሮጀክት ስልጠና የዘለቀው ቢጣ ኢትዮጵያን ወክሎ ከሌሎች የወቅቱ ድንቅ ተጫዋቾች ጋር ወደ ስዊድን ለማምራት አጋጣሚውን አግኝቶ የነበረ ቢሆንም መሳካት ባለመቻሉ የተስፋ መቁረጥ ስሜት ውስጥ ገብቶ ነበር። በአሰልጣኝ ታመነ ይርዳው ይሰለጥኑ የነበሩት እሱና ጓደኞቹ የመጨረሻው የስልጠና ዕድሜ ላይ በመድረሳቸው ‘ከቡድኑ ከወጣን ወደየት እንሄዳለን ?’ የሚል ስጋት ቢፈጠርባቸውም በሰዓቱ የነበረው የፖሊስ ዓመታዊ ውድድር ተስፋን ይዞላቸው መጣ፡፡ በውድድሩ ላይ የማሰልጠን ኃላፊነት የተሰጠው ደግሞ በፕሮጀክት ያሰለጠናቸው ታመነ መሆኑ ይበልጡኑ አጋጣሚውን መልካም አደረገው። አሰልጣኝ ታመነ ለ15 ቀኑ ውድድር አሰልጣኝ ሆኖ ቢመደብም ሀዋሳ ከነማንም በአሰልጣኝነት አጣምሮ መያዙ የታዳጊውን ተከላካይ ተስፋ አሰፋው። በዚሁም ደቡብ ፖሊስን ወክሎ አዲስ አበባ ላይ በነበረው የ1994ቱ ዓመታዊ ውድድር ላይ እየተካፈለ ሳለ በሀዋሳ ከነማ ሊፈለግ ቻለ። የአዲስ አበባ ክለቦችም ተነሳሳይ ፍላጎት ቢያሳዩም አሰልጣኝ ታመነ ” ከዚህ ውድድር ከተመለስን በኃላ የሀዋሳ ከነማ ተጫዋች ነህ ፤ ከማንም ጋር እንዳትነጋገር ከእኔ ጋር ትጣላለህ። ህይወትህ እንዳይበላሽ ከዚህ ሰዓት ጀምሮ የሀዋሳ ከነማ ተጫዋች ነህ።” በማለት ሲያግባባው ለጊዜው እውነት ባይመስለውም ቤተሰቦቹ ድረስ አማላጅ የሚልኩ ክለቦችን ትቶ የልጅነት አሰልጣኙን ቃል በማክበር ሀዋሳ ከነማን ተቀላቀለ።

ቡድኑን በተቀላቀለበት 1995 አሰልጣኝ ታመነ በበርካታ ታዳጊዎች የገነቡት የሀዋሳ ቡድን በፕሪምየር ሊጉ ብዙ ልምድ ስለልነበረው ጥሩ ዓመት አላሳለፈም። አንዱዓለምም ቋሚ ሆኖ ለመሰለፍ የተቸገረ ቢሆንም ጥሩ ልምድ በቀሰመበት በዚሁ ዓመት ቡድኑ ላለመውረድ እየዳከረ ቢቆይም በመጨረሻዎቹ ጨዋታዎች የመጀመሪያ አሰላለፍ ውስጥ የመካተት ዕድልን ማግኘት ጀመረ። በሚያሳየው ድንቅ የመከላከል ብቃቱም ‘እስከ ዛሬ የት ተደብቆ ነው ? እንዴት ሊቀመጥ ቻለ ?’ የሚሉ ጥያቄዎች በደጋፊው እንዲነሱ አድርጓል። አስገራሚው ነገር ደግሞ ከሊጉ ለመሰናበት ቁልቁል በመንደርደር ላይ የነበረው ሀዋሳ ከነማ የእሱን ቋሚ መሆን ተከትሎ ወደ መልካም ቁመናው በመምጣት በሊጉ መቆየት ቻለ። አንዱዓለም በመጀመሪያው ዓመት አብዛኛዎቹን ጨዋታዎች ከተሰላፊነት ይልቅ በተመልካችነት ያሳለፈ ቢሆንም ሀዋሳ የሊጉን ዋንጫ 1996 ላይ ሲያነሳ የቡድኑ ቁልፍ ከነበሩት ተጫዋቾች መካከል በግንባር ቀደምትነት በመጠቀስ ዛሬም ድረስ በክለቡ ደጋፊዎች ልብ ውስጥ መቀመጥ ችሏል፡፡ 1997 ላይም ክለቡ ጥሎ ማለፉን ሲያሳካ የእሱ ድርሻ የማይዘነጋ ነበር። ከሀዋሳ ጋር ሁለት ዋንጫዎችን ያነሳው የመሀል እና የመስመር ተከላካዩ 1999 ላይም በነጭ እና ሰማያዊ ለባሾቹ ቤት የፕሪምየር ሊጉን ዋንጫ መድገም ችሏል።

አንዱዓለም በሀዋሳ ከነማ በዋንጫ ያሸበረቁ ዓመታትን ባሳለፈባቸው ዓመታት በኢትዮጵያ ቡና ደጋፊዎች በጥብቅ ይወደድ ነበር። ሀዋሳ ከነማ በአዲስ አበባ ስታድየም ጨዋታውን ሲያደርግ አንዱዓለም በሜዳ ላይ በሚያሳየው በብልጠት የተሞላ አጨዋወቱ እና በደቃቃ ሰውነቱ ከቀድሞው ተከላካያቸው ሳሙኤል ደምሴ (ኩኩሻ) ጋር እያመሳሰሉት ለቡና ፈርሞ የኩኩሻን ቦታ እንዲረከብ ቢወተውቱትም እሱ ግን እስከ 2003 ድረስ በሀዋሳ መቆየትን ምርጫው አደረገ። ቀጣይ ማረፊያውም በአሰልጣኝ ሰብስቤ ይባስ የሚሰለጥነው ሠበታ ከነማ ሆኗል። በቀጣይም ለሲዳማ ቡና ተጫውቶ በ2005 ላይ ወደ ቀድሞ ክለቡ ሀዋሳ ተመልሷል። ሀዋሳ ከተማ በአዲስ አበባ ስታድየም ከመከላከያ ጋር ያደረገው ጨዋታ ግን ለተከላካዩ መጥፎ አጋጣሚን ይዞ መጣ። ሀዋሳ ከኃላ ተነስቶ ጨዋታውን ሲያሸንፍ ግቦቹን ላስቆጠሩት ሽመክት ጉግሳ እና አብዱልከሪም መሀመድ ሦስት ኳሶችን አመቻችቶ በማቀበል ድንቅ እንቅስቃሴ ቢያደርግም ጨዋታው ሊጠናቀቅ ሁለት ደቂቃዎች ሲቀሩት በገጠመው ጉዳት ጉልበቱ መናጋቱ ለእግር ኳስ ህይወቱ መቋጫ ምክንያት ሆነ። በክለብ ህይወቱ ደስተኛ ቢሆንም ለብሔራዊ ቡድን አለመጫወቱ የሚቆጨው አንዱዓለም ነጋ ከእግርኳሱ ከወጣ በኃላ በግል ስራዎች በመሰማራት በሀዋሳ እየኖረ ሲሆን በዛሬው የ90ዎቹ ኮከቦች አምዳችን ከድረገፃችን ጋር ቆይታ አድርጓል።

“ሀዋሳ ከነማ ስገባ አሰልጣኝ ታመነ ይርዳው ነበር፡፡ እሱ ህይወቱ ሲያልፍ ደግሞ ጋሽ ከማል ቀጠሉ። በጋሽ ከማል ጊዜም የቻምፒዮንነት ህይወቴ ጀመረ፡፡ እኛ ዋንጫ ስንበላ የነበረው ቤተሰባዊ ግንኙነታችን እና ስራችን ላይ ያለን ጥንካሬ የራስን ድርጅት የመምራት ያህል ነበር፡፡ ሁሉም ሰው የየግሉን አቅም አሟጦ ነበር የሚጠቀመው። ተጠባባቂ ተጫዋችን ጨምሮ ሁሉም ለውጤቱ ግብዓር ነበር። ያ ህብረት ባለመኖሩ ነው ሀዋሳ አሁን ላይ እየተቸገረ ያለው። በነገራችን ላይ ለዚህ ትልቁን ድርሻ የሚወስዱት ጋሽ ከማል ናቸው። ምክንያቱም አሰልጣኝ ሳይሆኑ አባት ናቸው። ማንም ሰው ጣልቃ አይገባባቸውም። አንድ ተጫዋቾች የዲሲፕሊን ችግር ቢያሳይ እንኳን በራሳቸው መንገድ ነው የሚፈቱት። አመራር ላይ ካሉት ጋር ሁሉ መገናኘት አይፈልጉም፡፡ እንዲህ በማድረጋቸው ደግሞ የእሳቸው በሳል አመራር ቡድኑን ለውጤት አብቅቶታል።

“2003 ወደ ሰበታ ሄድኩኝ። አሰልጣኝ ሰብስቤ ከፕሬዝዳንቱ ጋር ሆነው ሀዋሳ ድረስ መጡና ‘የእኛ ቡድን አባል እንድትሆን እንፈልጋለን’ ብለው አስጨነቁኝ። እኔም ‘ሀዋሳ ያሳደገኝ ክለብ ነው። እነሱ ጋር ጥያቄዎች አሉኝ። ጥያቄዎቼን የማይመልሱልኝ ከሆነ ወደ እናንተ እመጣለሁ።’ አልኳቸው። ሆኖም ሀዋሳም ጋር የምፈልገውን ነገር ማግኘት ስላልቻልኩ የኳስ ህይወትም ደግሞ አጭር በመሆኑ እና በምታሳልፋቸው ጣፋጭ ጊዜያቶች መጠቀም ያለብህን መጠቀም ስላለብህ ወደ ሰበታ ሄድኩ። በሰበታ ጥሩ ጊዜ ነበር ያሳለፍኩት። ሆኖም አንድ ክለብ ላይ ለውጦች ይኖራሉ። ለውጦች ሲመጡ ከአሰልጣኞች ጋር ያለመግባባቶች ይፈጠራሉ። ለሁለት ዓመት ነበር የፈረምኩት ግን ከመጣው አሰልጣኝ ጋር መግባባት ስላልቻልኩኝ ደስ በሚል ሁኔታ ተነጋግረን ሰበታን ለቀኩኝ እና ወደ ሲዳማ ቡና ሄድኩ። ሲዳማ ቡና መጥቼ የሚገርም ጊዜን አሳለፍኩኝ። እንደውም የቡድኑ ምርጥ እና ኮከብ ተከላካይ ተብዬ ሀያ ሺህ ብር ተሸልሜያለው። ይህ ሲደረግልኝ ደግሞ በዓመቱ ውስጥ ትንሽ ጎል (አስራ ሁለት አስራ ሦስት ጎል) ብቻ ነበር የገባብን። የዋንጫ ፉክክር ውስጥ ሁሉ ገብተን ነበር። ያው ጥሩ ቆይታ ቢኖረኝም ሀዋሳ ቤተሰብ ስላለኝ ወደ ቤተሰቤ ለመምጣት ብዬ አሰልጣኝ ዘላለም ሽፈራው ወደ ሀዋሳ ወሰደኝ። እስከ 2005 ሀዋሳ በመጫወት ካሳለፍኩ በኃላም በጉዳት አቆምኩ፡፡

“በሀዋሳ ከነማ ቤት ወርቃማ ጊዜን አሳልፌያለሁ። አንድ ሁለቴ ገባ ወጣ ከማለቴ ውጪ አንድም ቀን የአቋም መውረድ ችግር ገጥሞኝ አያውቅም። እስከ አሁንም መጫወት የምችልበት ዕድሉ ነበረኝ። የእኛ ሀገር የህክምና ችግር ነው ወደ ኳሱ ድጋሜ እንዳልመለስ ያደረገኝ። አብዛኞቹ ተጫዋቾች እየጠፉ ያሉትም በጉዳት ነው፡፡ እኛ ሀገር ላይ ድኖ መመለስ የሚችል ተጫዋች የለም። በራሱ ጥረት በራሱ ህክምና አድርጎ እንጂ ሀገር ውስጥ ዘመናዊ ህክምና ተሰጥቶት በትክክል ወደ ጤንነቱ የተመለሰ ተጫዋች የለም። ያ ችግር እኔንም አንዱ ተጠቂ አድርጎኛል። ወደምፈልገውም ወደምወደውም ኳስ እንዳልመለስ አድርጎኛል። ነገር ግን ሀዋሳ ቤት በቆየውባቸው ጊዜያት ይሄ ነው የከፋኝ ብዬ የማስታውሰው ነገር የለም። ለእኔ ሀዋሳ ከነማን ከተቀላቀልኩበት ቀን ጀምሮ እስካቆምኩበት ድረስ የከፋኝ በዛች ጉዳት ባገኘኝ ቀን ብቻ ነው። ከዛ ውጪ ደስተኛ ሆኜ ነው ያሳለፍኩት። ወደ እግር ኳሱ ለመመለስ አስቤ ነበር። ኳስ በዕድሜ የሚቆም ነገር ነው። ከኳሱ መውጣት ይከብዳል። ከልጅነትህ ጀምሮ ስትጫወት አሳልፈህ ከዛም በላይ ደግሞ ስራህ ሆኖ ለመመለስ ያጓጓል። እናም የተወሰኑ ሙከራዎችን አደረኩኝ። ‘ውጪ ሄደህ መታከም አለብህ’ ተባልኩኝ። በወቅቱ የግንዛቤ ችግርም ነበረብኝ። ግንኙነት ልፈጠር የምችልባቸው ሰዎችም አልነበሩም። ከዚያም ለመመለስ እየጣርኩ አንድ ዓመት ከቆየው በኃላ ግን በዛው ተስፋ እየቆረጥኩ መጣሁ። ኳስን አቁሜም ወደ ሌላ ህይወት ውስጥ ገባሁ፡፡

“በጣም ደስ የሚለኝ አዲስ አበባ ስታድየም ስጫወት ነው፡፡ ከቡና እና ከጊዮርጊስ ጋር ስጫወት ደስ ይለኛል። ምክንያቱም የስታድየሙ ድባብ ነው። አንዳንዴ ታዝበህ ሊሆን ይችላል ፤ ስታድየሙ ውስጥ ጨዋታ እያደረኩ ደጋፊ የማይበት ጊዜ አለ። የደጋፊው ድባብ ፣ ድጋፍ አሰጣጣቸው እና ዝማሬያቸው ደስ ይላል። እዚህ ቦታ ላይ ለመድረሴ የኢትዮጵያ ቡና አስተዋጽኦ አለው ብዬም አስባለሁ። ምክንያቱም በምጫወትበት ሰዓት ላይ ከሚወዱት የቀድሞው ተጫዋቻቸው ከሳሙኤል (ኩኩሻ) ጋር ያነፃፅሩኛል። እና የኩኩሻ ምትክም ይሉኛል። ሁሌም በየዓመቱ ሊያስፈርሙኝ ይፈልጋሉ። እየሰደብኳቸው የሚወዱኝ ደጋፊዎች ናቸው። ይሄን ስል በመጥፎ አይደለም። ለምሳሌ ለቡድንህ ውጤት ይዞ ለመውጣት ስትል ሰዓት ትገላለህ። ስትገል ደግሞ በተቃራኒ ቡድን መጥፎ ኢሜጅ ያመጣል። ያ ነገር ደግሞ አንተን ወዳልሆነ ነገር ውስጥ እንድትገባ ያደርግሀል። እኔ ደግሞ በዛን ሰዓት ደጋፊዎቹ ሲናገሩኝ እጅግ በጣም በጣም አቅሜን እንዳወጣ ነው የሚያደርጉኝ። በዚሁ አጋጣሚ የእውነቴን ነው የኢትዮጵያ ቡናን መለያ ሳልለብስ ኳስ በማቆሜ እጅግ በጣም ይፀፅተኛል። እኔ ከምጫወተው አጨዋወት ጋር የሚያያዝ ቡድን ነው። እንደገና ደግሞ የኩኩሻ እና የእኔ መለያ ቁጥር አንድ ነው። ብቻ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን እና የኢትዮጵያ ቡናን መለያ ሳላደርግ ኳስ በማቆሜ ውስጤን ዛሬም ድረስ ይሰማኛል፡፡

“በኳስ ህይወቴ ያላሳካውት ነገር የለም። ከሀዋሳ ጋር ሁለት የፕሪምየር ዋንጫ እና አንድ የጥሎ ማለፍ ዋንጫን አግኝቻለሁ። በካርድ እና በተወሰነች ጉዳት ጥቂት ጨዋታ ነው ያመለጠኝ። ሽንፈት አልወድም ፤ የተፈጥሮ እልህ አለብኝ። እንዲህ ዓይነት ባህሪ ውጪ የለብኝም ሜዳ ላይ ግን ቀልድ አላውቅም። ፊሽካ እስኪነፋ ድረስ ያለኝን አውጥቼ ነው የምጫወተው። ትልቅ ተጫዋችም ቢሆን ከተሳሳተ መናገሬ አይቀርም። ደግሞም ማንም ኔጌቲቭ መልስ መልሶልኝ አያውቅም። ብሔራዊ ቡድን ባለመጫወቴ ግን ይቆጨኛል ። ዛሬም ድረስ ብሔራዊ ቡድኑን ሳይ ይከፋኛል። ምክንያቱም የብቃት ችግር አልነበረብኝም። ከታዳጊ እስከ ዋናው ብሔራዊ ቡድን ተጠርቼ ከቡድኑ ጋር ልምምድ ስሰራ ቆይቼ መጨረሻ ላይ የሚቀርብልኝ ምክንያት ግን አሳማኝ አይደለም ፤ ከሰውነቴ ጋር ያያይዙታል። አንድም ቀን ግን ይሄ ነው ብለው ነግረውኝ አያውቁም። በአካሌ ብቁ ነኝ ፣ ልምምዴን በአግባቡ እሰራለው ፣ የመጀመሪያ አሰላለፍ ውስጥ ገብቼ እጫወታለው። መጨረሻ ላይ ግን ወር ሁለት ወር ተዘጋጅቼ ወደ ቤቴ እሄዳለሁ። አንድ ጊዜ ብቻ አሰልጣኝ አብረሀም መብራቱ አምበል አድርጎኝ ለሦስት ወር ያህል ለኦሊምፒክ ውድድር ስንዘጋጅ ቆይተን ፓስፖርቴ ሁለት ወር አልፎበት ውድድሩ እስኪጀምር መጫወት አትችልም ተብዬ ተመልሻለው። በመጠራት ደረጃ ግን የቀረሁበት የለም። ነገር ግን ብሔራዊ ቡድን የመጫወት አቅም ሳይኖረኝ ተመልሻለሁ ብዬ አንድም ቀን በህይወቴ አምኜ አላውቅም።

“በእግርኳስ ከማልረሳው አጋጣሚ 1997 ጥሎማለፍ ከሙገር ጋር ያደረግነው የዋንጫ ጨዋታ ነው። ዘጠና ደቂቃ 1-0 እየመራን 88ኛው ደቂቃ ላይ ሙገሮች አገቡብን። 90ኛው ደቂቃ ላይ ደግሞ ደገሙብን እና 2-1 ሆንን። የቡና ደጋፊዎች እኛን የጊዮርጊስ ደጋፊዎች ደግሞ ሙገርን እየደገፉ በጣም ከፍተኛ ውጥረት ነበር። በቃ እያለቀስኩ ነበር የምጫወተው። ዋንጫውን ወስደናል ብለን እርግጠኛ ሆነን ፊሽካ ብቻ እየጠበቅን መመራት ማለት የማይጠበቅ እና የማይታመን ነገር ነው። ድራሚዊ የሆነ ነገር ነው። ከዛም ሦስት ደቂቃ ተጨመረ። ሁለቱ ደቂቃዎች አልቀው አንድ ሲቀር ሁላችንም ወደ ሙገር ጎል መጥተናል። የማዕዘን ምት አገኘን እና ያቺ ኳስ ክሮስ ተደርጋ ተጨርፋ መጥታ እግሬ ላይ አረፈች። ወደ አራት ሰኮንድ ምናምን ኳሷን ይዤ ደነገጥኩ። ብመታው ከተበላሸ ፊሽካ ይነፋል ፤ የሆነ ነገር ቢፈጠርስ ብዬ አሰብኩ። አጋጣሚ ቀና ስል በኃይሉ ደመቀ ይለምነኛል። በጥንቃቄ ለበሀይሉ ደመቀ ሰጠውት እና አገባ። እዚህ ጋር ጥፋት ሰርቻለሁ ፤ እያበድኩኝ መለያዬን አውልቄ የጊዮርጊስ ደጋፊ ጋር ሄድኩኝ። የተረጋጋው ሙሴ ዩሴፍ ነብሱን ይማረው እና ከቤንች እየሮጠ መጥቶ መለያ አለበሰኝ። ጨዋታው ሊጀመር ሲል እኔ እና አዳነ ግርማ በሁለት ቢጫ በቀይ ወጣን። የአዳነን መውጣት አላየሁም። እኔ እያለቀስኩኝ መልበሻ ክፍል ገባሁ። አዳነም በቡና ደጋፊዎች በኩል ወደኔ ጋር መጣ። ማልቀስ ጀመርን። ሁለታችንም ‘ምን ሆነህ ነው ?’ መባባል ጀመርን። ‘እኔኮ ቢጫ አይቼ ወጣሁ እኔም እንደዛው’ ምናምን ተባባልን። በቃ ሁለታችንም ‘ቡድኑን ገደልን’ አልን። ‘ያገኘነውን ዕድል ድጋሜ አሳጣነው’ እያልን ማልቀስ ቀጠልን። መሀመድ የሚባል የኛ በረኛ አለ ‘አይዞህ ሠላሳ ደቂቃ ተጨመረ ፤ ፀልይ’ ብሎ ጭንቅላቴን አሻሽቶኝ ሄደ። ደቂቃውም አለቀ። እሱ ሲያልቅ በፔናሊቲ ዋንጫውን በላን። በ90 ደቂቃ ውስጥ ሁለት ዓለምን ያየሁበት በህይወቴ ልረሳሁ የማልችለው ጨዋታ ነው ፤ ቪዲዮ ቢኖረው ደስ ይለኝ የነበረ አጋጣሚ።

” ወደምወደው እግርኳስ በአሰልጣኝነት እመለሳለው ብዬ ከጓደኞቼ ጋር አወራለሁ። የአሰልጣኝነት ኮርስ ወስጃለው። ታዳጊዎችን በማሰልጠን ከምወደውን ስፖርት ሳልርቅ ደስተኛ ሆኜ መኖር እፈልጋለሁ። ከእግርኳሱ ከራኩኝ በኃላ እንደማንኛውም ሰው የራሴ የሆነ ነገር እየሰራው እገኛለው። ይሄን ደግሞ የፈጠረልኝ ያሳለፍኩት የእግርኳስ ህይወቴ ነው። በኳሱ ባገኘዋቸው ነገሮች የራሴን ቢዝነስ በራሴ ደረጃ እያንቀሳቀስኩ ነው።”

“ቤተሰቦቼን አመሰግናቸዋለሁ። ሌላው አሰልጣኝ ታመነ ይርዳው እና ጋሽ ከማልን በሚገባ ማመስገን እፈልጋለሁ። እግዚአብሔር የሰጡኝ ሰዎች ናቸው። በእግርኳስ ዘመኔ ሁሉ አንዳችም ነገር በራሴ ያመጣሁት የለም። ባጠፋ እንደ አባት ገስፀውኝ መልካም ነገር ስሰራም አበረታተውኝ ተደስተውብኝ እዚህ ደረጃ እንድቆምም በኳሱም እዚህ እንድደርስ ያደረጉት ታመነ እና ጋሽ ከማል ናቸው። ታመነ አልፏል ጋሽ ከማል አሉ። ላደረጉልኝ ሁሉ አምላክ ይክፈላቸው።

“አንድ ልጅ አለኝ ፤ የሚኖረው አሜሪካ ነው። እንደውም የኢትዮጵያን ብሔራዊ ቡድንን በእሱ ውስጥ አየዋለው ብዬ ተስፋ አደርጋለሁ። አሁን አስር ዓመት ሆኖታል። አካዳሚ ውስጥ ፕሮሰስ ላይ ነው ያለው። ስለሀገሬ ብዙ እየነገርኩት ነው። የስታድየሞችን ፎቶዎች እልክለታለሁ። እዛ ነው የተወለደው። በእርግጥ በመጣም ሰዓት እኔ በምጫወትበት ሰዓት ልጅ ቢሆንም ትንንሽ ቪዲዮችን ያያል። ከኳስ ውጪ አይወድም። ኢንጅነር እና ፕሮፌሽናል ኳስ ተጫዋች መሆን ይፈልጋል። የአርሰናል ቀንደኛ ደጋፊ ነው። የሜሲ እና የኦዚል አድናቂም ነው። ኳስ ተጫዋች ሆኖልኝ ለኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ቢጫወትልኝ ደስ ይለኛል ፤ ጊዜው ስላልረፈደ እንደሚሳካም ተስፋ አለኝ፡፡”

👉እጅዎን በተደጋጋሚ በሳሙና በአግባቡ በመታጠብ አልያም አልኮል እና ሳኒታይዘር በመጠቀም

👉ከሰዎች ጋር ንክኪ በማስወገድ

👉ከአላስፈላጊ እንቅስቃሴ በመገደብ፣ አካላዊ ርቀት በመጠበቅ እና በቤት በመቆየት ራሳችንን ከኮሮና ቫይረስ እንጠብቅ!


© ሶከር ኢትዮጵያ