ለአሰልጣኞች ስለ ባርሴሎና አካዳሚ ገለፃ እና አካል ብቃት ላይ ያተኮረ ስልጠና ተሰጥቷል

ለአሰልጣኞች ከዚህ ወር ጀምሮ የተለያዩ የስልጠና መርሐ ግብሮች እየተሰጡ ሲሆን በትላንትናው ዕለት ደግሞ በባርሴሎ አካዳሚ አሰልጣኝ እንዲሁም በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ መምህር የአካል ብቃት ስልጠና ተሰጥቷል፡፡

በአሰልጣኝ አብርሀም መብራቱ አነሳሽነት ለአሰልጣኞች በተለያዩ ቀናት ስልጠና እና የመማሪያ ውይይቶች በመሰጠት ላይ ይገኛሉ፡፡ በዋናነት በሀገራችን ያሉ የፕሪምየር ሊግ እንዲሁም ደግሞ በሴቶች እግር ኳስ ላይ ለሚሰሩት ትኩረቱን አድርጎ መስራት ከጀመረ ወራት ተቆጥረዋል፡፡ ቅዳሜ ቀን ለአሰልጣኞቹ ስለ ቤልጅየም የእግር ኳስ መሠረት እና ዕድገቷ አሁን እስከ ደረሰችበት ጊዜ ድረስ ላይ ያተኮረ ሰፊ ውይይት እና ስልጠና በማብራሪያ መልክ የተሰጠ ሲሆን ቅዳሜ ምሽት ደግሞ አካል ብቃት ላይ ያተኮረ ስልጠና ለሁለት ሰአታት ያህል ተሰጥቷል፡፡

ስልጠናውን የሰጡት የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የስፖርት ሳይንስ መምህር ዶክተር ዘሩ በቀለ ሲሆን መምህሩ ለአሰልጣኞቹ ፊትስ ላይ ያተኮረ ሰፊ ገለፃን አድርገዋል በተለይ በገለፃቸው ላይ ኢትዮጵያውያን አሰልጣኞች በአሁኑ ሰአት ውድድሮች ባለመኖራቸው በምን አይነት መልኩ በቴክኖሎጂ ታግዘው የፊትነስ ስራን ማሰራት አለባቸው የሚሉ ሲገኙበት ለሰልጣኞችም የአውሮፓ ሀገራትን ተሞክሮም በምሳሌነት በግብአትነት አቅርበዋል፡፡


ሌላው ትላንት ምሽት የታዳጊዎች ስልጠና እና ዕድገት ላይ ያተኮረ የውይይት መርሀግብር ተከናውኗል፡፡ይህን ስልጠና የሰጡት የባርሴሎና አካዳሚ ከ20 አመት በታች አሰልጣኝ ፍሬድ ሞርጋን ሲሆን ሰፊ የሆነ ጥልቅ ሀሳብን ለሀገራችን አሰልጣኞች አቅርበዋል፡፡ አሰልጣኝ በውይይቱ ላይ በዋናነት የባርሴሎና አካዳሚ ከታዳጊ ልጆች ጋር በተያያዘ የሚሰራቸውን አመርቂ ስራዎች ያብራሩ ሲሆን በተለይ አሰራሩን ኢትዮጵያ ተግባራዊ በምታደርግበት ሂደት ላይ ትኩረታቸውን አድርገው ስለ ማዕከሉ ገለፃ እና የአሰለጣጠን መንገድ ገልፀዋል፡፡ ከባርሴሎና ባሻገር ስለ ስፔን የስኬት ቁልፍ ዙሪያም እኚህ ተጋባዥ አሰልጣኝ ገለፃን አድርገዋል፡፡

በጎ ጅምርን ያመጣው የዙም የቪዲዮ ውይይት ለሀገራችን አሰልጣኞች ጥቅሙ እያየለ የመጣ ሲሆን በቀጣይ ቀናትም ተመሳሳይ መርሀግብሮች እንደሚቀጥሉ ሶከር ኢትዮጵያ ያገኘችሁ መረጃ ይጠቁማል፡፡ይህን ስልጠና በኢትዮጵያ ውስጥ ላሉ የከፍተኛ ሊግ እና ብሔራዊ ሊግ አሰልጣኞች በተዋረድ ለመስጠት መዘጋጀታቸውን ከአሰልጣኝ አብረሀም መብራቱ ጋር ይህን ስልጠና በበላይነት የሚመራው የአሜሪካው ሳክርሜንቶ አካዳሚ የሴቶች ዳሬክተር አሰልጣኝ አምሳሉ ፋንታሁን ነግሮናል፡፡

👉እጅዎን በተደጋጋሚ በሳሙና በአግባቡ በመታጠብ አልያም አልኮል እና ሳኒታይዘር በመጠቀም

👉ከሰዎች ጋር ንክኪ በማስወገድ

👉ከአላስፈላጊ እንቅስቃሴ በመገደብ፣ አካላዊ ርቀት በመጠበቅ እና በቤት በመቆየት ራሳችንን ከኮሮና ቫይረስ እንጠብቅ!


© ሶከር ኢትዮጵያ