ይህንን ያውቁ ኖሯል? (፯) | የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ እና አሰልጣኞች…

ሶከር ኢትዮጵያ ዘወትር ሀሙስ በምታስነብበው ይህንን ያውቁ ኖሯል? አምዷ የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ እና ክለቦችን የተመለከቱ እውነታዎችን ስታቀርብ ሰንብታለች። ዛሬ ደግሞ ሊጉን እና አሰልጣኞችን የሚመለከቱ እውነታዎችን አጠናክራ ቀርባለች።

1- የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ በአዲስ መልክ እና መዋቅር ከ1990 አንስቶ መደረግ እንደጀመረ ይታወቃል። በዚህም ዓመት የተዘጋጀውን የመጀመሪያ የሊግ ዋንጫን ከክለባቸው መብራት ኃይል ጋር ያነሱት አሰልጣኝ ሐጎስ ደስታ ናቸው።

2- በኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ታሪክ ስኬታማው አሰልጣኝ ሰርዲዮቪች ሚሉቲን “ሚቾ” ናቸው። ሰርቢያዊው አሰልጣኝ በቅዱስ ጊዮርጊስ ጋር 5 የፕሪምየር ሊግ ዋንጫ በማንሳት ቀዳሚው ናቸው።

3- አሁን በሊጉ ላይ እያሰለጠኑ ከሚገኙ 16 አሰልጣኞች ረጅም ጊዜ አሁን በሚገኝበት ክለብ ውስጥ የቆየው አሰልጣኝ የሲዳማ ቡናው ዘርዓይ ሙሉ ነው። ዘርዓይ ከ2010 የግማሽ ዓመት ጀምሮ እስካሁን ቡድኑን እያሰለጠነ ይገኛል።

4- የሃገሪቱ ከፍተኛ የሊግ እርከን የኢትዮጵያ ሻምፒዮና በሚባለበት ጊዜ እና በአዲስ መልክ የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ በተባለበት ጊዜ ዋንጫዎችን ከተለያዩ ክለቦች ጋር ያገኙ ብቸኛ አሰልጣኝ አሥራት ኃይሌ ናቸው። አሥራት የኢትዮጵያ ሻምፒዮናን ሦስት (1986፣ 1987፣ 1988) እንዲሁም የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ደግሞ ሁለት (1991፣1992) ዋንጫዎችን አንስተው ነው ብቸኛ አሰልጣኝ የሆኑት።

5- የመጀመሪያው የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ የውጪ ዜጋ አሰልጣኝ ጁሴፔ ፔትሬሊ ናቸው። ፔትሬሊ በ1995 የመብራት ኃይል አሰልጣኝ ሆነው በመሾማቸው ነው የሊጉ የመጀመሪያ የውጪ ዜጋ አሰልጣኝ ሆነው የታሪክ መዝገብ ላይ የተፃፉት።

6- በመጀመሪያ ዓመት “የዋና አሰልጣኝነት” ቆይታ በሊጉ ዋንጫ ያነሱ አሰልጣኞች 9 ናቸው። እነሱም ጉልላት ፍርዴ (1993 ከመብራት ኃይል ጋር)፣ ሥዩም ከበደ (1994 ከቅዱስ ጊዮርጊስ ጋር)፣ ሰርዲዮቪን ሚሉቲን ሚቾ (1997 ከቅዱስ ጊዮርጊስ ጋር)፣ ውበቱ አባተ (2003 ከኢትዮጵያ ቡና ጋር)፣ ዳኔሎ ፔርሉጂ (2004 ከቅዱስ ጊዮርጊስ ጋር)፣ ንጉሴ ደስታ (2005 ከደደቢት ጋር)፣ ሬኒ ፌለር (2006 ከቅዱስ ጊዮርጊስ ጋር)፣ ፋሲል ተካልኝ (2007 ከቅዱስ ጊዮርጊስ ጋር) እና ገብረመድህን ኃይሌ (2010 ከጅማ አባጅፋር እና 2011 ከመቐለ ጋር) ናቸው።

7- በ1990 እንደ አዲስ በተጀመረው የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ አራት ክለቦች የውጪ ሃገር ዜጎችን በዋና አሰልጣኝነት ቀጥረዋል። እነሱም መብራት ኃይል፣ ቅዱስ ጊዮርጊስ፣ ደደቢት እና ኢትዮጵያ ቡና ናቸው።

8- በሊጉ ላይ አሁን እያሰለጠኑ ከሚገኙ አሰልጣኞች መካከል ከተለያዩ ክለቦች ጋር ዋንጫ ያነሳው አሰልጣኝ ገብረመድህን ኃይሌ ነው። ገብረመድን አሁን ከሚገኝበት መቐለ 70 እንድርታ ጋር በ2011 ዋንጫ ከማንሳቱ በፊት ከጅማ አባጅፋር ጋር የሊጉን የበላይነት አግኝቶ ነበር። ከዚህ መነሻነት ገብረመድህን አሁን በሊጉ እያሰለጠኑ ከሚገኙ አሰልጣኞች መካከል ከ2 ክለቦች ጋር ዋንጫ ያነሳ ብቸኛው አሰልጣኝ ሆኗል።

9- የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ በ1990 ከተጀመረበት ዓመት አንስቶ በሁሉም የውድድር ዘመናት ያሰለጠነ አሰልጣኝ የለም።

10- የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ክለብ እና የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድንን ይዘው ዋንጫ ያገኙ ብቸኛው አሰልጣኝ አሥራት ኃይሌ ናቸው። አሥራት ቅዱስ ጊዮርጊስን ይዘው የሊግ ዋንጫን (1991 እና 1992) እንዲሁም የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድንን እየመሩ የሴካፋ ዋንጫን (1994 እና 97) ማግኘታቸውን ተከትሎ ነው ስማቸው የታሪክ መዝገብ ላይ የተፃፈው።

👉እጅዎን በተደጋጋሚ በሳሙና በአግባቡ በመታጠብ አልያም አልኮል እና ሳኒታይዘር በመጠቀም

👉ከሰዎች ጋር ንክኪ በማስወገድ

👉ከአላስፈላጊ እንቅስቃሴ በመገደብ፣ አካላዊ ርቀት በመጠበቅ እና በቤት በመቆየት ራሳችንን ከኮሮና ቫይረስ እንጠብቅ!


© ሶከር ኢትዮጵያ