”የዘመናችን ክዋክብት ገፅ” ከሀብታሙ ተከስተ ጋር…

የፋሲል ከነማው የተከላካይ አማካይ ሀብታሙ ተከስተ የዘመናችን ክዋክብት ገፅ እንግዳችን ነው። ወቅቱን በምን አይነት ሁኔታ እያሳለፈ እንደሆነ ከአዝናኝ ጥያቄዎች ጋር ይዘን ቀርበናል።

በዚህ ወቅት ጥሩ ከሚባሉ የተከላካይ አማካዮች መካከል ሀብታሙ ተከስተ ይገኝበታል። ጎንደር ከተማ ተወልዶ ያደገው ሀብታሙ በትውልድ ስፍራው ጎንደር ከተማ ዳሽን ቢራ እግርኳስ ክለብ ተስፋ ቡድን እግርኳስን የጀመረ ሲሆን በ2007 በቢጫ ቴሴራ ዋናው ቡድንን ሲያገለግል ከቆየ በኋላ በውሰት ወደ ሰሜን ሸዋ ደብረብርሃን በ2008 መጨረሻ አካባቢ አምርቶ ለ 3ወራት ያህል ስኬታማ ቆይታ ማድረጉን ተከትሎ በ2009 ወደ መቐለ 70 እንደርታ አምርቶ መቐለን ፕሪምየር ሊግ በማስገባት እና በቀጣይ ዓመት በሊጉ ድንቅ ጊዜ እንዲያሳልፍ አስተዋፅኦ አድርጓል። ከሁለት ዓመት የመቐለ ቆይታ በኋላ በ2011 ወደ ጎንደር በመመለስ ፋሲል ከነማን ተቀላቅሎ ስኬታማ ጊዜ እያሳለፈ የሚገኘው ሀብታሙ የኢትዮጵያ ዋንጫ እና የአሸናፊዎች አሸናፊ ዋንጫን ከቡድኑ ጋር ማሳካት ችሏል። በአሰልጣኝ ሥዩም ከበደ ስብስብ ውስጥ ጉልህ ሚና ያለው ሀብታሙ ተከስተ ከሶከር ኢትዮጵያ ጋር አጠር ያለ ቆይታ አድርጓል ።

ጊዜህን እንዴት ታሳልፋለህ ?

በመጀመሪያ አክብራችሁ እንግዳ ስላደረጋችሁኝ በጣም አመስግናለሁ። ያው ጊዜው አስከፊ ስለሆነ ጠዋት ጠዋት ሰው በሌለበት አካባቢ የአካል ብቃት እንቅስቃሴዎች አደርጋለሁ። ቤት ከተመለስኩ በኋላ የተወሰነ ሰዓት እረፍት አድርጋለሁ። ከዛ መፅሃፎች አነባለሁ፣ ጌም እጫወታለሁ፣ ከቤተሰቦቸ ጋር በመሆን የቀረኝን ጊዜ አሳልፋለሁ። ሌሎችም ስፖርተኞች ራሳቸውን ጠብቀው እንቅስቀሴ በማድረግ ወድድር ሲጀምር አቋማቸው እንዳይወርድ በተቻላቸው አቅም እንዲሰሩ እመክራለሁ ።

እግርኳስ ተጫዋች ባትሆን ምን እሆናለሁ ብለህ ታስባለህ?

(እየሳቀ …) ይሄ በጣም ከባድ ጥያቄ ነው። ልጅ እያለሁ ጀምሬ ራዕዬ ኳስ ተጫዋች መሆን ነበር። ሌላ ነገር አስቤ አላውቅም፤ ያደኩት እግርኳስን ስጫወት ነው። እና ሌላ ነገር እሰብ ብትለኝ ይከብደኛል ።

ካስቆጠርከው የማትረሳው ግብ ?

መቐለ እንደፋረምኩ ትግራይ ስታድየም እየተሰራ ስለነበር ዓዲግራት ላይ ነበር የመጀመሪያ ጨዋታችንን ከሰበታ ጋር ያደረግነው። በመጀመርያ ጨዋታዬ ገና ጨዋታው በተጀመረ ሁለተኛው ደቂቃ ላይ ነበር ያስቆጠርኩት የማልረሳው ግብ ነው ።

ከተቆጠሩባችሁ ድንቅ ግብ የማትረሳው ?

መቐለ 70 እንደርታ እያለሁ ትግራይ ስታድየም ከቅዱስ ጊዮርጊስ ስንጫወት አብዱልከሪም መሐመድ 88ኛ ደቂቃ አካባቢ ያስቆጠረብን ግብ በጣም ድንቅ ግብ ነበረች፤ እሱን አልረሳውም ።

በተቃራኒ ስትገጥመው የሚከብድህ ተጫዋች ?

እግርኳስ ሜዳውስጥ ስገባ ማሸነፍን አስቤ ነው የምገባው። ተጫዋችን አክብጄም አቅልዬም አላይም። ሁሉም ተጫዋች ሜዳ ላይ ለኔ አንድ ነው። ለማሸነፍ እስከገባሁ ድረስ አክብጄም አቅልዬም አላይም።

አብረህው መጫወት የምትፈልገው የፕሪምየር ሊግ ተጫዋች ?

አብሬው መጫወት የምፈልገው ተጫዋች ሳይሆን ድጋሜ ባገኛቸው ደስ የሚለኝ ተጫዋቾች አሉ። አማኑኤል ገብረሚካኤል እና ያሬድ ከበደን እንዲሁም ዳሽን ቤት እያለን ቢጫ ታሴራ በነበርንበት ወቅት አስራት መገርሳ ሲጫወት ደስ ይለኝ ስለነበር ከሱ ጋር ብጫወት ብዬ አስብ ነበር።

በእግርኳስ ቅርብ ጓደኛህ ማነው ?

ለኔ ቅርብ ጓደኞቼ አማኑኤል ገብረሚካኤል እና ሰለሞን ሀብቴ ናቸው አማኑኤል ገና ከተስፋ ጀምሮ አብሮኝ ቢጫ ታሴራ ደብረብርሃን እና መቐለ ድረስ ወደ አምስት አመት አብረን ያሳለፍን ጓደኛዬ ነው። ሰለሞን ፋሲል ከመጣሁ በኋላ ያገኘሁት መልካም ሰው ነው።

በእግርኳስ ያዘንክበት እና የተደሰትክበት ቀን ?

በጣም ያዘንኩበት ቀን በ2011 ዓመቱን ሙሉ በወጥ አቋም አሳልፈን በመጨረሻ ዋንጫውን ያጣንበት መንገድ በጣም አሳዝኖኛል። በጣም ነበር የተሰማኝ። ጥሩ ውድድር ዓመት አሳልፈን ነበር፤ ዋንጫ ይገባን ነበር። በጣም ደስ የተደሰትኩበት ቀን ደግሞ መቐለን ፕሪምየር ሊግ ያስገባነው ጊዜ የነበረው ድባብ በልፋታችን ይዘነው ከገባነው ክለብ ጋር ፕሪምየር ሊግ እንደምንጫወት ስታውቅ በጣም ተደስቼ ነበር ።

ሜዳ ላይ ካጋጠመህ ገጠመኝ ያስገረመህ ?

መቐለ እያለሁ ሜዳ ላይ ጥፋት ተሰራብን፤ ዳኛው ሳይነፋልን ግብ ከመቆጠር ዳንን ከዛ እንዴት አልነፋህም ብሎ አንድ ተጫዋቾች ዳኛውን ሄዶ ሰደበው። ዳኛ የመለለት ስድብ በጣም ያስቃል። እሱን አልረሳውም፤ ከዳኛ ያልጠበኩት በጣም ከባድ ስድብ ነበር፤ ያነን አልረሳውም።

ከዚህ በኋላ በእግርኳስ ማሳካት የምትፈልገው ስኬት ?

ኳስ ተጫዋች ስትሆን ብዙ ነገር ታስባለህ። ሀገር ውስጥ ብቻ ሳይሆን ከሀገር ወጥቶ መጫወት ታስባለህ። ሀገርህን ወክለህ ማገልገል ትፈልጋለህ እና ያለብኝን ችግር ቀርፌ የተሻለ ሰርቼ እነዚህን ነገሮች ማሳካት እፈልጋለሁ። እንዲሁም በ2011 ያጣነውን የፕሪምየር ሊግ ዋንጫ ከፋሲል ከነማ ጋር ማንሳት እፈልጋለሁ ።

ታዳጊ እያለህ ያጋጠሙህ ችግሮች አሉ ?

በዳሽን ቢራ እግርኳስ ቡድን ተስፋ ውስጥ ነበርን ያደግነው። በጣም የሚገርምህ ክለቦች ያሳድጉሃል እንጅ እንክብካቤ አያደርጉልህም። አይዟችሁ በርቱ አይሉህም፤ በቃ ትኩረታቸው ዋናው ብድን ላይ ነው። ስታሸንፍ ደስተኛ ናቸው፤ ስትሸነፍ ለምን ይላሉ። ዋናው ብድን ላይ ለታዳጊዎች ስለሚሰጥ እድል ግድ የላቸውም። አሁን ለምሳሌ እኛ ጋር ዳሽን ቢራ ተስፋ ብዙ ተስፋ የተጣለባቸው ታዳጊዎች ነበሩ። እንክብካቤ እና ድጋፍ ያደረገላቸው ስለሌለ አሁን የሉም። ያለፈው አልፏል፤ እኔ አሁን የሚያሳስበኝ በፋሲል ከነማ ላደጉት ልጆች የነዛን ዕጣ ፈንታ እንዳይገጥማቸው እፈራለሁ። እንክብካቤ እየተደረገላቸው አይደለም። በዚህ አጋጣሚ ክለቦች ለሚያድጉ ልጆች ትኩረት ቢሰጡ ጥሩ ነው እላለሁ። ተንከባክበህ የምታሳድገው ልጅ የማልያ ፍቅር ይኖረዋል። ክለብን በሚገባ ያገለግላል እና ክለቦች በሚገባ ትኩረት መስጠት አለባቸው ። በቃ እኔ በነበርኩበት ዳሽንም፣ መቐለም ይሄው ፋሲልም ተመሳሳይ ነው ትኩረት አይሰጡም። ትኩረት የሚሰጡ ክለቦች አሉ፤ እነሱን ተሞክሮ በመውሰድ ምን ይጎላል ምን ያስፈልጋል በማለት እድል በመስጠት ልጆቹን ቢሞክሯቸው ጥሩ ነው።

እግርኳሱ ላይ ባለውለታዬ ነው የምትለው ሰው አለ ?

እኔ ሁሌም ባለውለታዬ የጌታዬ እናት ድንግል ማርያም ነች የ፤ ማመስገን የምፈልገው እሷን ነው። ከአሰልጣኝ ጥራ ካልከኝ ግን ታዳጊ እያለሁ ጀምሩ አይዞህ በርታ በማለት በማሰራትም ትልቅ አስተዋጽኦ ያደርግልኝ የነበረው ተገኘ ዕቁባይ ነው

በጎንደር የሚገኙ የቱሪስት መስህቦችን ጎብኝተሀል ?

(እየሳቀ… ) ፋሲል ግንብ ካየሁት ቆይቻለሁ። ራስ ግንብ ግን አይቸው አላውቅም። እስቲ ለወደፊት አየዋለሁ። በደምብ ጎብኝቼ ሌሎች ተጫዋቾች ሲመጡ አስጎበኛለሁ።  

👉እጅዎን በተደጋጋሚ በሳሙና በአግባቡ በመታጠብ አልያም አልኮል እና ሳኒታይዘር በመጠቀም

👉ከሰዎች ጋር ንክኪ በማስወገድ

👉ከአላስፈላጊ እንቅስቃሴ በመገደብ፣ አካላዊ ርቀት በመጠበቅ እና በቤት በመቆየት ራሳችንን ከኮሮና ቫይረስ እንጠብቅ!


© ሶከር ኢትዮጵያ