ሀዋሳ ከተማ ከወራቶች ቆይታ በኋላ ድሬደዋ ከተማን 1-0 በማሸነፍ ከወራጅ ቀጠናው የወጡበትን ውጤት አስመዝግበዋል።
ድሬደዋ ከተማ ከሽንፈት መልስ ከባለፈው ስብስባቸው የአራት ተጫዋቾች ለውጥ በማድረግ አህመድ ረሺድ፣ አቡበከር ሻሚል፣ አስራት ቱንጁ እና ዮሐንስ ደረጄን አሳርፈው ቴውድሮስ ሃሙ፣ሄኖክ ሀሰን፣ ሙኹዲን ሙሳ እና ሐቢብ ከማል ለውጠው ሲገቡ በሀዋሳ ከተማ በኩል ነጥብ ተጋርተው ከወጡበት ከባለፈው ጨዋታ የአምስት ተጫዋች ለውጥ አድርገዋል። በዚህም ሰለሞን ወዴሳ፣ ቢንያም በላይ፣ ያሬድ ብሩክ፣ ቸርነት አውሽ እና ብሩክ ኤልያስ ቀይረው ሲሳይ ጋቾ፣ ታፈሰ ሰለሞን፣ አብዱልባሲጥ ከማል፣ ተባረክ ሔፋሞ እና እስራኤል እሸቱ በመያዝ ወደ ሜዳ ገብተዋል
ዓለም አቀፍ ዋና ዳኛ ባዓምላክ ተሰማ በመራው በዚህ ተጠባቂ ጨዋታ ኳሱን ተቆጣጥረው የሜዳውን ክፍል በመጠቀም እንዲሁም ወደ ፊት በመሄድ እጅግ የተሻለ እንቅስቃሴ ያደርጉ የነበሩት ሀዋሳ ከተማዎች ምንም እንኳን እደወሰዱት ብልጫ ተደጋጋሚ ሙከራዎች ለማድረግ ቢቸገሩም እስራኤል እሸቱ በግንባሩ በመግጨት የግቡ ቋሚን ጨርፎ ከወጣበት ሙከራ በኋላ የጥረታቸውን ፍሬ በጎል ታጅቧል። 25ኛው ደቂቃ ላይ ማይክል ኦቱሉ የሰጠውን ታፈሰ ሰለሞን ተከላካይ በማለፍ ኳሱን ወደ ሳጥን ይዞ በመግባት በሚገርም ብቃት ቡድኑን ቀዳሚ ያደረገ ጎል አስቆጥሯል።
ድሬደዋዎች ሀዋሳዎች በቅብብሎሽ መሐል የሚሰሩትን ስህተቶች ኳሱን በመንጠቅ የግብ አጋጣሚዎችን ለመፍጠር ጥረት ያደርጋሉ በዙም ስኬታማ አልነበሩም። ይልቁንም በ28ኛው ደቂቃ ላይ የሀዋሳው አጥቂ እስራኤል እሸቱ የግል ጥረቱን ተጠቅሞ ከሳጥን ውጭ የመታውን ኳስ ሁለተኛ ጎል ሊቆጠርባቸው ተቃርበው የግቡ ቋሚ ታድጓቸዋል።
ሀዋሳ ከተማ ጨዋታወን ሙሉ ለሙሉ ተቆጣጥረው ብልጫ በወሰዱበት እንቅስቃሴ ወንድማገኝ ማዕረግ ላይ የተሰራውን ጥፋት ተከትሎ በግምት ከ25 ሜትር ርቀት የተሰጠውን ቅጣት ምት በረከት ሳሙኤል መቶት ግብጠባቂው አላዛር አምክኖበታል። የአጋማሹ የመጨረሻ አስር ደቂቃዎች ሀይቆቹ እየተቀዛቀዙ በአንናፃሩ ቡርትካናማዎቹ ተነሳሽነታቸው ከፍ እያለ ወደ ጨዋታው ለመግባት እንቅስቃሴ ማድረግ ችለው የነበረ ቢሆንም የጠሩ የጎል ዕድሎችን ሳይፈጥሩ ጨዋታው ለዕረፍት ወደ መልበሻ ክፍል አምርቷል።
በሁለተኛው አጋማሽ ጨዋታው በሁለቱም ቡድኖች በኩል ተመጣጣኝ የሆነ እንቅስቃሴ እያስመለከተን ቢቀጥልም በሙከራዎች ረገድ ብዙም ያልነበረበት አጋማሽ ነበር። ተጠቃሽ ሙከራዎችም በድሬደዋ በኩል በ68ኛው ደቂቃ ላይ አብዱልሰላም የሱፍ ከግራ መስመር ወደ ፊት በመሄድ ወደ ውስጥ የላከውን የሀዋሳው ተከላካይ ሲሳይ ኳሱን ለማውጣት ጥረት ሲያደርግ እራሱ ላይ ለጥቂት አስቆጥሮ የነበረው በሀዋሳ ከተማዎች በኩል ደግሞ በ72ኛው ደቂቃ ያሬድ ብሩክ መቶት ግብ ጠባቂው አላዛር አድኖበታል።
በመጨረሻዎቹ አስር ደቂቃዎች ድሬደዋዎች የአቻነት ጎል ፍለጋ ጥረት ያደረጉበት በአንፃሩ ሀዋሳዎች ውጤቱን ለማስጠበቅ በሙሉ አቅማቸው በመከለካል በመልሶ ማጥቃት አደጋ ለመፍጠር የሞከሩበት ሂደት ቢሆንም በሁለቱም በኩል ምንም ዒላማውን የጠበቀ ሙከራ ሳንመለከት ጨዋታው በሀዋሳ 1-0 አሸናፊነት ተጠናቋል።