ቅድመ ጨዋታ መረጃዎች | ሀዋሳ ከተማ ከ ፋሲል ከነማ

ቅድመ ጨዋታ መረጃዎች | ሀዋሳ ከተማ ከ ፋሲል ከነማ

የ31ኛው ሳምንት በአንድ ነጥብ ልዩነት ተከታትለው የተቀመጡት ሐይቆቹ እና ዐፄዎቹ በሚያደርጉት ጨዋታ ይቋጫል።

በሰላሣ ሰባት ነጥቦች 10ኛ ደረጃ ላይ የተቀመጡት ሀዋሳ ከተማዎች ከውጤታማው የከተማቸው ቆይታ በኋላ በያዙት የሽቅብ ጉዞ ለመቀጠል ዐፄዎቹን ይገጥማሉ።

አሰልጣኝ ሙሉጌታ ምሕረትን ከቀጠሩ በኋላ የሚያስደንቅ መሻሻል አስመዝግበው ከወራጅ ቀጠናው መውጣት የቻሉት ሐይቆቹ በሁለተኛው ዙር የሚታይ ለውጥ አምጥተዋል። ከውድድሩ ዓመቱ አጋማሽ በኋላ በተከናወኑ አስራ አንድ ጨዋታዎች ውስጥ በመሪው መድን ከገጠማቸው ሽንፈት ውጭ እጅ ያልሰጡት ሐይቆቹ በተጠቀሰው ወሳኝ የውድድር ወቅት ከሽንፈት ከመራቃቸው ባለፈ ተከታታይ ድሎች ማስመዝገባቸው ከወራጅ ቀጠናው ወጥተው በሰንጠረዡ አካፋይ እንዲደላደሉ አስችሏቸዋል። በመጨረሻዎቹ ስድስት ጨዋታዎች ማግኘት ከሚገባቸው አስራ ስምንት ነጥቦች ውስጥ ሁለት ብቻ ጥለው አስራ ስድስቱን ያፈሱት ሀዋሳ ከተማዎች በተለይም በመደዳ ድል ባደረጉባቸው የመጨረሻዎቹ ሦስት ጨዋታዎች ድንቅ እንቅስቃሴ አድርገዋል። በተጠቀሱት ጨዋታዎቹ አራት ግቦች በማስቆጠር አንድ ግብ ብቻ ማስተናገዳቸውም ቡድኑ ያለበትን ውጤታማ ወቅታዊ ብቃት ማሳያ ነው። የሽቅብ ጉዟቸውን ለማስቀጠልም በመከላከሉ እና በማጥቃቱ ረገድ ያላቸውን ጥንካሬ ማስቀጠል ይኖርባቸዋል።

በሰላሣ ስድስት ነጥቦች 11ኛ ደረጃ ላይ የተቀመጡት ፋሲል ከነማዎች በአንድ ነጥብ ከፍ ብሎ 10ኛ ደረጃ ላይ ከተቀመጠው የነገው ተጋጣሚያቸው በሚያደርጉት ጨዋታ ድል ማድረግ ከሚሰጣቸው የደረጃ መሻሻል በተጨማሪ ከስጋት ቀጠናው እንዲርቁ ስለሚያስችላቸው መርሐግብሩ እጅግ ወሳኝ ነው።

ወጥነት በጎደለው አካሄዳቸው እዚህ የደረሱት ዐፄዎቹ ድል ካደረጉ ስድስት የጨዋታ ሳምንታት አስቆጥረዋል። ቡድኑ ደረጃውን እንዲያሻሽል ከረዱት ሦስት ተከታታይ ድሎች በኋላ በተከናወኑ ስድስት መርሐ-ግብሮች ላይ ሦስት ሦስት የሽንፈት እና የአቻ ውጤቶች በእኩሌታ ማስመዝገቡን ተከትሎ ወደ ስጋት ቀጠናው ቀርቧል። በቅርብ ሳምንታት ቡድኑ ለገጠመው የውጤት መቀዛቀዝ እንደ አንድ ምክንያት የሚጠቀሰው ደግሞ የማጥቃት ክፍሉ ውጤታማነት መቀነስ ሲሆን ቡድኑ በሦስት ጨዋታዎች ስምንት ግቦች ካስቆጠረ በኋላ ባለፉት ስድስት ጨዋታዎች ሦስት ግቦች ብቻ ማስቆጠሩም በውጤቱ ላይ አሉታዊ አሳርፏል። ይህንን ተከትሎ የማጥቃት ክፍሉ  ዳግም ወደ ውጤታማነቱ የሚመልሱ ስራዎች መስራት ከአሰልጣኝ ውበቱ አባተ የሚጠበቅ ስራ ሲሆን የነገው ተጋጣሚያቸው የተከላካይ ክፍል በመጨረሻዎቹ ሦስት ጨዋታዎች አንድ ግብ ብቻ ያስተናገደ እንደመሆኑም ፈተናው ከባድ ያደርግባቸዋል።

በሀዋሳ ከተማ በኩል ፍቃደሥላሴ ደሳለኝ  በቅጣት ምክንያት ከነገው ጨዋታ ውጭ ሲሆን ሌሎች የቡድን አባላቶች ግን ለነገው ጨዋታ ዝግጁ ናቸው። በፋሲል በኩል አቤል እንዳለ በጉዳት ማርቲን ኪዛ ደግሞ በቅጣት ምክንያት አይሰለፉም። አማኑኤል ገብረሚካኤል ግን ከጉዳቱ አገግሞ ለጨዋታው ዝግጁ ሆኗል።

ሁለቱ ቡድኖቹ ከዚህ ቀደም በ16 ጨዋታዎች ተገናኝተዋል። ዐፄዎቹ በ5 ጨዋታዎች ድል በማድረግ ቀዳሚ ሲሆኑ ሐይቆቹ 4 ጊዜ አሸንፈዋል፤ ቀሪዎቹ 7 ጨዋታዎች ደግሞ በአቻ ውጤት ተጠናቀዋል በጨዋታዎቹ ፋሲል 19 ሲያስቆጥር ሀዋሳ 20 ግቦች ማስቆጠር ችለዋል።