ላለመውረድ በሚደረገው ፉክክር ተሳታፊ የሆነው የኢትዮጵያ ንግድ ባንክን እና ወላይታ ድቻን የሚያገናኘው ጨዋታ 12፡00 ላይ ይደረጋል።
በሰላሳ ስምንት ነጥብ ተከታትለው ከተቀመጡ ሦስት ክለቦች በሁለት ነጥብ ልቆ 12ኛ ደረጃ ላይ የተቀመጠው የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በሊጉ ለመትረፍ ያለው ዕድል ራሱን በራሱ ለመወሰን ድልና ድልን ብቻ እያለመ ወደ ሜዳ መግባት ይኖርበታል።
የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በ25ኛው ሳምንት ላይ ቅዱስ ጊዮርጊስን ካሸነፈ ወዲህ ላለፉት ዘጠኝ ጨዋታዎች ድል ማድረግ አልቻለም። ውጤቶቹን ተከትሎ ወደ ስጋት ቀጠናው የቀረበው ቡድኑ መልካም እንቅስቃሴውን በውጤት አለማጀብ ትልቁ ድክመቱ ነው። ሀምራዊ ለባሾቹ በሀድያ ሆሳዕና ሽንፈት ባስተናገዱበት ጨዋታ ጨምሮ በቅርብ ሳምንታት በተካሄዱ መርሐ-ግብሮች ላይ ብልጫ መውሰድ ቢችሉም ግብ ማስቆጠር ቀላል አልሆነላቸውም። በስድስት ጨዋታዎች ሁለት ጊዜ ብቻ ኳስ እና መረብን ያገናኙት ሀምራዊ ለባሾቹ በሀድያ ሆሳዕና ሽንፈት ባስተናገዱበት ጨዋታ የመጨረሻ የግብ ዕድሎችን በመፍጠር ረገድ መሻሻል ማሳየት ቢችሉም በተለይም በሦስተኛው የሜዳ ክፍል የነበራቸው ነገሮችን በእርጋታ የመከወን ችግር ግቦችን እንዳያስቆጥሩ አድርጓቸዋል። ቡድኑ በመጨረሻው ጨዋታ ከቆሙ ኳሶች ጥቂት የማይባሉ ዕድሎች መፍጠሩና ተጨማሪ የግብ ማግኛ መንገዶች ለመፍጠር ጥረት ማድረጉ እንደ አወንታ የሚነሳለት ነጥብ ቢሆንም በነገው ዕለትም ወደ ሳጥን የሚደርስባቸውን ሌሎች መንገዶች መዘየድ የግድ ይለዋል።
በጥቅሉ ሲታይ ቡድኑ ከእንቅስቅሴ በዘለለ ወደ ውጤታማነት ለመሸጋገር የማጥቃት አጨዋወቱም በብዙ ረገድ መሻሻል ይኖርበታል። በውድድር ዓመቱ በርከት ያሉ የአቻ ውጤቶች በማስመዝገብ 2ኛ ደረጃ ላይ የቀመጠው ቡድኑ በደረጃ ሰንጠረዡ ያለበት ቦታ በአቻ ውጤት እንዲረካ የሚያደርግ አይደለም፤ ይህንን ተከትሎ በተጫዋቾች የአሸናፊነት መንፈስ የማስረፅ ስራም ሌላው ቡድኑ መስራት የሚኖርበት ጉዳይ ነው።
በአርባ አምስት ነጥብ 8ኛ ደረጃ ላይ የተቀመጡት ወላይታ ድቻዎች በመጨረሻው ሳምንት በባህር ዳር ከተማ ከደረሰባቸው አስከፊ ሽንፈት በማገገም ደረጃቸውን ለማሻሻል ወደ ሜዳ ይገባሉ።
በባህርዳር ከተማ የአራት ለባዶ ሽንፈት ባስተናገዱበት ጨዋታ ላይ በሁሉም ረገድ የተዳከመ እንቅስቃሴ የነበራቸው የጦና ንቦቹ በተለይም ጉልህ የሆነ ግለሰባዊ እና መዋቅራዊ ድክመት የተስተዋለበት የመከላከል አደረጃጀታቸውን ማሻሻል ይኖርባቸዋል። በዕለቱ በተለመደው ቀጥተኛ አቀራረብ ወደ ጨዋታው የቀረበው ቡድኑ በማጥቃቱ በኩልም በተመሳሳይ ደካማ የሚባል ብቃት ማሳየት ቢችልም በዋናነት ግን የተከላካይ ክፍሉ ድክመት ዋጋ አስከፍሎታል። ይህንን ተከትሎ የውድድር ዓመቱ በተሻለ ደረጃ ለማጠናቀቅ የሚያደርገውን ጉዞ ለማሳካት የተጠቀሱትን ድክመቶች ማረም ይገባዋል። ተጋጣሚው በሊጉ ለመትረፍ የሞት ሽረት ትግል ማድረግ በሚጠበቅት ወቅት ላይ መገኘቱም ምናልባትም ጨዋታውን ፈታኝ ሊያደርግበት ይችላል ተብሎ ይገመታል።
ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በኩል ባሲሩ ኡማር ወደ ልምምድ ቢመለስም ለጨዋታ የመድረሱ ነገር አጠራጣሪ ከመሆኑ በስተቀር ሁሉም የቡድኑ ተጫዋቾች ለጨዋታው ዝግጁ ናቸው። በወላይታ ድቻ በኩል ከብስራት በቀለ ውጭ ሁሉም የቡድኑ አባለት ዝግጁ መሆናቸውን አውቀናል።
ሁለቱ ቡድኖች በሊጉ 11 ጊዜ የግንኙነት ታሪክ ያላቸው ሲሆን ሁለቱም በተመሳሳይ በ3 ጨዋታዎች ሲረቱ ቀሪዎቹ 5 ጨዋታዎች ደግሞ በአቻ ውጤት ተቋጭተዋል። ወላይታ ድቻ 11 ሲያስቆጥር ንግድ ባንክ በአንፃሩ 13 አስቆጥሯል።