ቅዱስ ጊዮርጊስ በዚህ የዝውውር መስኮት የውጪ ተጫዋች እንዳያስፈርም እግድ ቢጣልበትም ሁለት የውጪ ተጫዋቾችን ወደ ቡድናቸው ሊቀላቅሉ እንደሆነ ገልፀን የነበረ ሲሆን የሁለቱ ተጫዋቾችን ማንነት ደግሞ እንደሚከተለው ለማጣራት ሞክረናል።

ቅዱስ ጊዮርጊስ ስፖርት ክለብ ከደቂቃዎች በፊት ጋዜጣዊ መግለጫ እና የቡድን አባላት ትውውቅ መርሐ ግብር ያከናወነ ሲሆን በተለይ የቡድኑ አሠልጣኝ ሆነው በአምስት አመት ውል የተሾሙት ሚቾ ስለስብስባቸው ገለፃ ሲያደርጉ ሁለት የውጪ ተጫዋቾችን እንዳካተቱ ተስተውሎ በምን አግባብ ተጫዋቾቹ እንደሚመጡ ጥያቄ ቀርቦ የተጫዋቾቹን አመጣት በተመለከተ የተሰጠውን ማብራሪያ ዘገባ አቅርበን ነበር። አሁን ደግሞ ድህረ ገፃችን ሶከር ኢትዮጵያ የተጫዋቾቹን ማንነት ለማጣራት ሞክራ እነማን ፈረሰኞቹን እንደሚቀላቀሉ አደውቃለች።
ቀዳሚው ቡድኑን ይቀላቀላል ተብሎ የሚጠበቀው የ20 ዓመቱ ኮንጎዊ ተከላካይ ቫን ኢጎር ቡካካ ነው። ቦካካ ከዚህ ቀደም በሀገሩ ኢንተር ክለብ ብራዛቪል የተጫወተ የመሀል ተከላካዩ ሲሆን ሰኞ ወደ ሀገራችን መጥቶ ቡድኑን በይፋ እንደሚቀላቀል ይጠበቃል።
ሁለተኛው ተጫዋች ደግሞ የኮንጎ ብራዛቪል ተወላጅ የሆነው ክሪስት ቶሉንጋ ነው፡፡ ክሪስት የ20 ዓመት ወጣት የአጥቂ ስፍራ ተጨዋች ሲሆን ለሀገሩ ከ23 ዓመት በታች ብሄራዊ ቡድን እንዲሁም በክለብ ደረጃ በዲያብሌስ ኖይሪስና ለአልጄሪያው ፓራዱ ክለቦች ተጫውቷል፡፡ ይህ ተጫዋች ከወራት በፊት ፈረሰኞቹን ለመቀላቀል ወደ ኢትዮጵያ መጥቶ በእግድ ምክንያት ግልጋሎት ሳይሰጥ ተመልሶ መሄዱ የሚታወቅ ሲሆን አሁን ዳግም ፈረሰኞቹን ለማገልገል በቀጣዩ ሳምንት የመጀመሪያ ቀናት እንደሚመጣ አውቀናል።
የክለቡ የቦርድ አባል የሆኑት አቶ ቶፊቅ ሁለቱ ተጫዋቾች ከኦክቶበር 19 በኋላ መፈረም እና መጫወት እንደሚችሉ መግለፃቸውን ቀድመን ማስነበባችን ይታወቃል።

