የ35ኛው ሳምንት በሊጉ ለመቆየት 3 ነጥብ የሚያስፈልጉት ድሬዳዋ ከተማ መውረዱን ካረጋገጠው ስሑል ሽረ በሚያደርጉት የዕለቱ ብቸኛ ጨዋታ ይጠናቀቃል።
በአርባ ነጥብ 15ኛ ደረጃ ላይ የተቀመጡት ድሬዳዋ ከተማዎች በሊጉ የሚያቆያቸውን ወሳኝ ድል ለማስመዝገብ መውረዱን ካረጋገጠው ስሑል ሽረ ጋር ይፋለማሉ።
ሦስት ተከታታል ድሎች አስመዝግበው በሊጉ የመቆየት ተስፋቸው ካለመለሙ በኋላ በመጨረሻዎቹ ሁለት ጨዋታዎች አንድ ነጥብ ብቻ ማሳካት የቻሉት ብርቱካናማዎቹ በነገው ዕለት ዳግም ወደ ድል መንገድ የሚመለሱ ከሆነ ነጥባቸውን አርባ ሦስት በማድረስ በሊጉ የመቆየታቸውን ጉዳይ የሚያረጋግጡ ይሆናል። ከሲዳማ ቡና ጋር ነጥብ በተጋሩበት ጨዋታ ላይ ከተጋጣሚያቸው ተመጣጣኝ የሚባል እንቅስቃሴ ያደረጉት ድሬዎች በተለይም የተሻለ ብልጫ በወሰዱበት የመጀመርያው አጋማሽ ላይ ጉልህ የሆነ ዕድሎችን የመፍጠር ድክመት ተስተውሎባቸዋል። በዕለቱ በርከት ያሉ የግብ አጋጣሚዎች የመፍጠር እንዲሁም የጨዋታውን ውጤት ቀያሪ የግብ ዕድሎች የመጨረስ ድክመት የተስተዋለበት ቡድኑ በነገው ዕለት በተጋጣሚ የግብ ክልል አከባቢ ያለበትን ውስንነት መቅረፍ ዋነኛ ዓላማው መሆን ይገባዋል። ብርቱካናማዎቹ በነገው ዕለት በሁለት መርሐ-ግብሮች ዘጠኝ ግቦች ያስተናገደ ቡድን እንደመግጠማቸው ከባድ ፈተና ይጠብቃቸዋል ተብሎ ባይገመትም በድምሩ አራት ግቦች አስቆጥረው ድል ባደረጉባቸው ከባህርዳር ከተማ እና የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በተደረጉ ጨዋታዎች የነበራቸው የማጥቃት ጥንካሬ እንዲሁም ብርቱ የማሸነፍ መንፈስ መመለስ ይኖርባቸዋል።
በሀያ ሁለት ነጥብ 17ኛ ደረጃ ላይ የተቀመጡትና በ32ኛው ሳምንት ላይ በቅዱስ ጊዮርጊስ ሽንፈት ካስተናገዱ በኋላ ወደ ከፍተኛ ሊጉ መውረዳቸውን ያረጋገጡት ስሑል ሽረዎች ደረጃቸውን የሚያሻሽሉበት ዕድል ዝግ ቢሆንም ብያንስ የውድድር ዓመቱን በተሻለ ነጥብ ለማገባደድ እና ለክብር ብርቱካናማዎቹን ይገጥማሉ።
በተከታታይ ስድስት መርሐ-ግብሮች ነጥብ ተጋርተው ከወጡ በኋላ በመጨረሻዎቹ አራት ጨዋታዎች በመደዳ ሽንፈት ያስተናገዱት ስሑል ሽረዎች ከምንም ነገር በላይ ባለፉት አራት ጨዋታዎች ደካማ የነበረውን የመከላከል አደረጃጀታቸውን ማስተካከል ይኖርባቸዋል። ባለፉት አራት ጨዋታዎች አስራ ሁለት ግቦች ያስተናገደው እና በውድድር ዓመቱ ከወልዋሎ እና አዳማ ከተማ በመቀጠል በርከት ያሉ ግቦች (39) የተቆጠሩበት ቡድኑ በነገው ዕለት በሊጉ ለመቆየት ወሳኝ ሦስት ነጥብ ይዞ ለመውጣት የሚያልመውን ድሬዳዋ ከተማ እንደመግጠሙ ሰሞነኛ የመከላከል ድክመቱን አርሞ መቅረብ ይኖርበታል።
በድሬዳዋ ከተማ በኩል ሱራፌል ጌታቸው በቤተሰብ ችግር ምክንያት ከነገው ጨዋታ ውጭ ቢሆንም ድልአዲስ ገብሬ እና አሕመድ ረሺድ ግን ቅጣታቸውን ጨርሰው ለጨዋታው ዝግጁ ሆነዋል። በስሑል ሽረ በኩል ሀብታሙ ገዛኸኝ፣ ፋሲል አስማማው፣ አላዛር አድማሱ እና ሄኖክ ተወልደ በጉዳት እንዲሁም ሞይስ ፖዎቴ፣ መሐመድ ዓብዱለጢፍ፣ አሌክስ ኪታታ እና ሱሌይማን መሐመድ ደግሞ ከደሞዝ ጋር በተያያዘ ባለፉት አራት ቀናት ልምምድ ያልሰሩ ሲሆን በነገው ጨዋታም የማይሳተፉ ይሆናል።
በ2011 ለመጀመርያ ጊዜ የተገናኙት ክለቦቹ ከተሰረዘው እና የአቻ ውጤት ከተመዘገበበት የ2012 ጨዋታ ውጭ 3 ጊዜ ተገናኝተው በሦስቱም ጨዋታዎች ነጥብ ተጋርተዋል፤ በግንኙነቱ ሁለቱም ክለቦች በእኩሌታ ሁለት ሁለት ግቦችን አስቆጥረዋል።