አብዮተኛው ሲታወሱ !

አብዮተኛው ሲታወሱ !

የኢትዮጵያ እግር ኳስ ሲነሳ በተለይ የአስልጣኞች ታሪክ ሲወሳ ከፊት መስመር ከሚሰለፉ ታላላቅ የእግር ሰዎች መካከል አንዱ ናቸው። ሥዩም አባተ! አዲስ ነገር ፈጣሪ፣ ታታሪ ተጫዋች፣ ሞገደኛ፣ የመሐል ሜዳ ሞተር፣ ባለ ንስር ዓይኑ ውጤታማ አሰልጣኝ .. ባለ ብዙ መልኮች የግማሽ ክፍለ ዘመን የእግር ኳስ ታሪክ ባለቤት የሆኑት ሥዩም አባተ ከዚህ ዓለም በሞት የተለዩት ልክ የዛሬ 7 ዓመት በዛሬዋ ቀን ጥቅምት 1 ቀን 2011 ዓ.ም ነበር። እኛም የታላቁን የኢትዮጵያ እግር ኳስ ባለውለታን በዚህ ቀን ለመዘከር ወደድን!

ሥዩም አባተ የተወለዱት በአዲስ አበባ ከተማ በ1943 ዓ/ም ነው። ከ1960ዎቹ ጀምሮ እስከ 1970ዎቹ አጋማሽ ድረስ በዘለቀው የተጫዋችነት ዘመናቸው አመዛኙን ጊዜ በቅዱስ ጊዮርጊስ ያሳለፉ ሲሆን በአማካይ ስፍራ ይበልጥ ቢታወቁም በሁለገብነት የቅዱስ ጊዮርጊስ ስኬታማ ዓመታት ላይ ጉልህ ሚና ተጫውተዋል። ከክለቡ ጋር የኢትዮጵያ ሻምፒዮና እና አራት ጊዜ የኢትዮጵያ ዋንጫ ድልም አሳክተዋል። በተለያዩ አጋጣሚዎችም የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድንን አገልግለዋል።

በ1972 የትግል ፍሬ ቡድን የተጫዋች-አሰልጣኝ በመሆን ወደ አሰልጣኝነቱ እንገደገቡ የሚነገረው ሥዩም አባተ ከ25 ዓመታት በላይ በዘለቀው የአሰልጣኝነት ህይወታቸው ቡድን የመገንባት፣ የራስን አስተሳሰብ የማስረጽ እና በቅጽበታዊ እይታ የተጫዋቾችን እምቅ አቅም የመረዳት ችሎታ የበራቸው ታሪክ ከማይረሳቸው ታላላቅ አሰልጣኞች መሐል ይመደባሉ።

የአሰልጣኝ ሥዩም አባተ የአሰልጣኝነት ጉዞ በኢትዮጵያ ቡና እና ኢትዮጵያ መድን ክለቦች ላይ ያጠነጠነ ነው። በ1976 ኢትዮጵያ ቡናን የተቀላቀሉት ሥዩም በአምስት የተለያዩ አጋጣሚዎች ክለቡን ያሰለጠኑ ሲሆን በተለይም ክለቡ በአዲስ መልክ ከተቋቋመ በኋላ የቡድን ግንባታ ላይ ትልቁን መሰረት እንደጣሉ ይነገርላቸዋል። በክለቡ ታሪክ የመጀመርያውን ትልቅ ዋንጫ በ1980 የኢትዮጵያ ዋንጫን በማንሳት እንዲያሳካ አድርገዋል። ኢትዮጵያ ቡና ድንቅ አጨዋወት እንዲኖረውና የበርካታ ደጋፊ ቀልብ እንዲይዝ የማይተካ ሚናም ነበራቸው።

በመቀጠል ወደ ኢትዮጵያ መድን በ1981 ያመሩት አሰልጣኝ ሥዩም እንደ ኢትዮጵያ ቡና ሁሉ ትልቅ መሠረት ከጣሉ የክለቡ አሰልጣኞች አንዱ ሆነው አልፈዋል። እስከ 1985 አጋማሽ በነበረው ቆይታቸው ድንቅ ቡድን የገነቡ ሲሆን ክለቡን በለቀቁ በጥቂት ወራት ክለቡ በካፍ ካፕ ውድድር እስከ ግማሽ ፍጻሜ በመድረስ ታሪክ መስራት ችሏል።

ከመድን ቆይታቸው በኋላ በኒያላ በሁለት አጋጣሚዎች በ1986 እና 1988 ቆይታ አድርገው ወደ ኢትዮጵያ ቡና በ1980ዎቹ መጨረሻ የተመለሱት አሰልጣኝ ሥዩም በድጋሚ የበርካቶችን ቀልብ የሳበ ድንቅ ቡድን የገነቡ ሲሆን የ1989 የኢትዮጵያ ሻሞፒዮና አሸናፊ ከመሆን አልፈው አሁንም ድረስ በታሪክ የሚወደሰውና አል አህሊን ከውድድር ያስወጣው የ1990 ቡድን አሰልጣኝ ነበሩ። በዚሁ ዓመት የኢትዮጵያ ዋንጫን እንዲያነሳም አድርገዋል።

ከ1990ዎቹ መጀመርያ በኋላ ባልተረጋጋው የአሰልጣኝነት ዘመናቸው በኢትዮጵያ ቡና እና ኢትዮጵያ መድን በተደጋጋሚ ተመላልሰው ሰርተዋል። በዚህም በ1991 መድንን ከመሩ በኋላ ቀጣዩን ዓመት በአየር መንገድ አሳልፈው ወደ ቡና ተመልሰዋል። ከአንድ ዓመት የቡና ቆይታ በኋላ ደግሞ በ1995 አዲስ አዳጊ በነበረው ብርሀንና ሰላም ስኬታማ ያልሆነ ጊዜን አሳልፈዋል።

የአሰልጣኝ ሥዩም ፈር ቀዳጅነት በሁለቱ ክለቦች የተገደበ አልነበረም። በ1996 የተረከቡት ባንኮችን በታሪኩ የመጀመርያ የሆነውን ትልቅ ዋንጫ የኢትዮጵያ ዋንጫን በማንሳት እንዲያሳካ አድርገዋል።

ከባንክ ቆይታቸው በኋላ በድጋሚ ወደ ቡና በአሰልጣኝነት እና ቴክኒክ አማካሪነት በመቀጠል ደግሞ ከ1999 እስከ ሚሌንየሙ መጀመርያ በመድን አሰልጣኝነት አሳልፈዋል።

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድንን ከ1985 – 1999 የታዳጊ፣ የወጣት፣ የኦሊምፒክ እና ዋና ብሔራዊ ቡድንን በተለያዩ ጊዜያት የመሩት ሥዩም አባተ በታዳጊ ቡድን ቆይታቸው በ1985 በሞሪሸስ በተካሄደው የወጣቶች የአፍሪካ ዋንጫ ግማሽ ፍጻሜ ድረስ መጓዝ የቻለ ቡድን ገንብተዋል። ይህ ወጣት ቡድን በወቅቱ ለዓለም ወጣቶች ዋንጫ ለመሳተፍ ጥቂት ቀርቶት (4ኛ ሆኖ በማጠናቀቁና ሦስት ቡድኖች ብቻ ያልፉ ስለነበር) ከውድድሩ ተመልሷል። በ1987 በሴካፋ ውድድር የታዳጊ ብሄራዊ ቡድኑን ይዘው ከኬንያ ጥሩ ውጤት ይዘውም ተመልሰዋል። በ1996 የመሩት ቡድን ለ2004 የአቴንስ ኦሊምፒክ ለማለፍ የመጨረሻ ምዕራፍ ደርሶ ነበር። በ1998 ዋናውን ብሔራዊ ቡድን ለአፍሪካ ዋንጫ ማጣርያ ከተረከቡ በኋላ የክለብ ልምድ የሌላቸው አዳዲስ ወጣት ተጫዋቾችን ያስተዋወቁበት መንገድም መነጋገርያ ሆኖ ነበር።

በትምህርት ዝግጅት ብቁ ከነበሩ አሰልጣኞች አንዱ የነበሩት ሥዩም በ1971 በጀርመን ከፍተኛ የአሰልጣኝነት ኮርስ ከወሰዱ ቀደምት አሰልጣኞችም አንዱ ናቸው። በ1988 የካፍ ኤሊት ኮርስ የወሰዱ ሲሆን በግብጽ – ካይሮ Intercontinental Elite Coach Seminar ተካፍለው በጊዜው የሀገሪቱን የእግርኳስ ኢንስትራክተሮች ቁጥር ወደ 3 ለማሳደግ መንገዱን ጀምረውም ነበር።

ከሚሌኒየሙ ወዲህ ከአሰልጣኝነት የራቁት ሥዩም ለረጅም ጊዜያት በሳንባ ምች ህመም በህክምና ሲረዱ ቆይተው ልክ በዛሬዋ ዕለት ጥቅምት 1 ቀን 2011 ከዚህ ዓለም በሞት ተለይተዋል። ሥርአተ ቀብራቸውም በሳሪስ አቡነ ገብረመንፈስ ቅዱስ ቤተክርስቲያን ጥቅምት 2/2011 ተፈጽሟል።

በተጫዋችነት እና በአሰልጣኝነት የሁለት ባላንጣ ክለቦች ታሪካዊ ሰው የነበሩት ሥዩም አባተ በይበልጥም የኢትዮጵያ እግርኳስን መልክ ከቀየሩ አብዮተኞች አንዱ ሆነው ታሪክ ሲዘክራቸው ይኖራል። ሆኖም በኢትዮጵያ እግርኳስ ጥለውት እንዳለፉት አሻራና ውለታ የሚገባቸው መታሰቢያ እንዳልተደረገላቸው ብዙዎቹ የሚስማሙበት ሀቅ ነው።