በሲቢኢ የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ የአዲስ አበባ ምደብ የመጀመሪያ ሳምንት የመጨረሻ ጨዋታዎች የጣና ሞገዶቹ ነብሮቹን ሲያሸንፉ የዓምናው ቻምፒዮን ኢትዮጵያ መድን ከአዳማ ከተማ ያለ ጎል አቻ ተለያይተዋል።
አዳማ ከተማ 0-0 ኢትዮጵያ መድን
7፡00 ሲል በዋና ዳኛ በሪሶ በላንጎ መሪነት የተጀመረው ጨዋታ የተጠበቀውን ያህል ፉክክር ያልተደረገበት ሲሆን የመጀመሪያው ለግብ የቀረበ ሙከራም 17ኛው ደቂቃ ላይ ተደርጓል። ረመዳን የሱፍ ከግራ መስመር የተሻገረለትን ኳስ ተጠቅሞ ያደረገው ሙከራ የግቡን የግራ ቋሚ ገጭቶ ተመልሶበታል።
ኃይል የተቀላቀለበት የጨዋታ መንገድ የተከተሉት ቡድኖቹ ያለቀላቸው የግብ ዕድሎችን አያስመልክቱን እንጂ በማጥቃት እንቅስቃሴው በኩል ግን አዳማዎች የተሻሉ ነበሩ። በተለይም 36ኛው ደቂቃ ላይ አህመድ ሁሴን እንዲሁም 38ኛው ደቂቃ ላይ ቢኒያም ዐይተን ያባከኗቸው ኳሶችም ተጠቃሽ ነበሩ።
ከዕረፍት መልስ ጨዋታው በተመሳሳይ ሂደት ሲቀጥል በ50 እና 51ኛው ደቂቃ በዳዋ ሆቴሳ አማካኝነት ከቅጣት ምት ሙከራዎችን ማድረግ የቻሉት አዳማዎች 58ኛው ደቂቃ ላይ ግብ ለማስቆጠር ተቃርበው አህመድ ሁሴን ለማሻማት በሚመስል መልኩ ከቀኝ መስመር ያሻገረው ኳስ አቅጣጫውን ቀይሮ መረቡ ላይ ሊያርፍ ሲል ግብ ጠባቂው ፋሲል ገብረሚካኤል አስወጥቶበታል።
ጨዋታው ቶሎ ቶሎ በሚነጠቁ ቅብብሎች እና በተደጋጋሚ በሚሰሙ የዳኛ ፊሽካዎች አሰልቺ እየሆነ ሲሄድ አዳማዎች 61ኛው ደቂቃ ላይ ዳዋ ሆቴሳ ከረጅም ርቀት ባደረገው ሙከራ እና 66ኛው ደቂቃ ላይ ነቢል ኑሪ ተቀይሮ በገባበት ቅጽበት ሳይጠቀምበት በቀረው ኳስ አዳማዎች የተጋጣሚያቸውን ሳጥን ቢፈትሹም ከዚህ ሙከራ በኋላ ግን ማስቀጠል አልቻሉም።
ባለፈው ዓመት ከመድን ጋር ቻምፒዮን የሆነው እና አሁን በአዳማ ከተማ በአንበልነት ቡድኑን እየመራ የሚገኘው ሀይደር ሸረፋ የቀድሞ የቡድን አጋሮቹ ወገኔ ገዛኸኝ እና በረከት ካሌብ ላይ በሁለት ደቂቃዎች ልዩነት በሠራቸው ጥፋቶች በሁለት ቢጫ ከሜዳ ወጥቷል። መድኖችም ያገኙትን የቁጥር ብልጫ ተጠቅመው በተረጋጋ እንቅስቃሴ ጎል ለማስቆጠር አጥቅተው ለመጫወት ቢሞክሩም ውጤታማ ሳይሆኑ ቀርተው ጨዋታው ያለ ግብ 0ለ0 ተጠናቋል።
ባሕር ዳር ከተማ 3-1 ሀዲያ ሆሳዕና
10፡00 ሲል በዋና ዳኛ መለሠ ንጉሤ መሪነት በአዲስ አበባ የተደረገው የመጀመሪያ ሳምንት የመጨረሻ ጨዋታ ገና በ7ኛው ደቂቃ የጣና ሞገዶቹን ጎል ያስመለከተን ነበር። ፍቅረሚካኤል ዓለሙ ከዮሐንስ ደረጄ ተቀብሎ ያደረገውን ሙከራ ግብ ጠባቂው ያሬድ በቀለ ሲያስወጣበት ያንኑ ኳስ ከማዕዘን ሲሻማ ያገኘው የመሃል ተከላካዩ ክንዱ ባየልኝ ኳሱን በግንባሩ በመግጨት መረቡ ላይ አሳርፎታል።
ነብሮቹ የአቻነት ግብ ፍለጋ ቶሎ ቶሎ ወደ ተጋጣሚ ሳጥን የመድረስ ፍላጎት ቢያሳዩም ተመስገን ብርሃኑ ካደረጋቸው ኃይልየለሽ ሙከራዎች ውጪ ግን የግብ ዕድሎችን ለመፍጠር ሲቸገሩ በአንጻሩ ባሕር ዳሮች በሄኖክ ይበልጣል አማካኝነት ጥሩ ሙከራ አድርገው በግብ ጠባቂው ያሬድ በቀለ ተመልሶበታል።
ከዕረፍት መልስ እንደመጀመሪያው አጋማሽ ሁሉ ፈጣን አጀማመር ያደረጉት የጣና ሞገዶቹ 47ኛው ደቂቃ ላይ ሁለተኛ ጎል አስቆጥረዋል። በቀኝ መስመር በጥሩ ቅብብል የወሰዱትን ኳስ በመጨረሻም ወንድወሰን በለጠ ወደ ውስጥ ሲቀንሰው ግብ ጠባቂው ያሬድ በቀለ በቀላሉ ኳሱን በመልቀቁ ያገኘው አማኑኤል ገብረሚካኤል ስጦታውን ተቀብሎ ኳሱን መረቡ ላይ አሳርፎታል።
ሀዲያዎች በሁለት ጎል እየተመሩ ባለበት ሰዓት 53ኛው ደቂቃ ላይ በእንቅርት ላይ ጆሮ ደግፍ የሆነ አጋጣሚ ተፈጥሮባቸዋል። ኤልያስ አህመድ ክንዱ ባየልኝ ላይ በሠራው አደገኛ ጥፋት በቀጥታ ቀይ ካርድ ከሜዳ ወጥቷል።
ባህር ዳር ከተማዎች ወደፊት ተጭነው መጫወታቸውን ቀጥለው 57ኛው ደቂቃ ላይ በፍቅረሚካኤል ዓለሙ አማካኝነት ከሳጥኑ ጠርዝ ላይ ጥሩ ሙከራ ሲያደርጉ ከአራት ደቂቃዎች በኋላ ግን ጎል አስተናግደዋል። ተመስገን ብርሃኑ መትቶት ግብ ጠባቂው ፔፔ ሰይዶ የመለሰውን ኳስ ከጨዋታ ውጪ አቋቋም ላይ የነበረው ጫላ ተሺታ ጎል አስቆጥሮት ቡድኑን ማነቃቃት ችሏል።
የጣና ሞገዶቹ ጫና ቢበረታባቸውም 80ኛው ደቂቃ ላይ ግን እፎይታ የሰጣቸውን ጎል አስቆጥረዋል። ተቀይሮ የገባው ሰቲ ኦሴ ከሳጥን ጠርዝ እጅግ አስደናቂ በሆነ ሁኔታ የመታው ኳስ የግቡን የቀኝ ቋሚ ገጭቶ ጎል ሆኗል። በቀሪ ደቂቃዎችም ተመጣጣኝ እንቅስቃሴ ያስመለከተን ጨዋታ በመጨረሻም በባሕር ዳር ከተማ 3ለ1 አሸናፊነት ተጠናቋል።