በሲቢኢ የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ የምድብ ለ የሳምንቱ መጨረሻ ጨዋታ ሽረ ምድረ ገነት በዳንኤል ዳርጌ ግሩም ግብ ድል አደረገ።
ሁለቱም ቡድኖች እየተፈራረቁ ብልጫ በወሰዱበት የመጀመርያው አጋማሽ ጥቂት የግብ ሙከራዎች የተደሩበት ነበር። ሆኖም ሽረ ምድረገነቶች ሙከራ በማድረግ የተሻሉ ነበሩ፤ ስንታየሁ ዋለጬ ከቅጣት ምት አክርሮ መቷት የግቡን አግዳሚ የመለሳት ኳስ እንዲሁም ተካልኝ ደጀኔ ከመዓዝን ምት በቀጥታ ያደረጋት ሙከራም ይጠቀሳሉ። በ38 ደቂቃ ግን ሽመክት ጉግሳ ወደ ሳጥን አሻግሯት ዳንኤል ዳርጌ በመቀስ ምት ባስቆጠራት ግሩም ግብ ሽረዎች መሪ መሆን ችለዋል።
የመቐለ 70 እንደርታ ብልጫ የታየበት ሁለተኛው አጋማሽ በጥፋቶች እንዲሁም በተደጋጋሚ ፊሽካዎች ታጅቦ የተካሄደ ነበር። ምዓም አናብስት ብርሀኑ አዳሙ በመቀስ ምት በሞከራት ኳስ እንዲሁም ተቀይሮ በገባው ስንታየሁ መንግስቱ ሙከራዎች ማድረግ ቢችሉም የአቻነቷን ግብ ማስቆጠር አልቻሉም። ፍፁም ዓለሙ ከቅጣት ምት የሞከራት እንዲሁም በድጋሚ ከግቡ አፋፍ መቷት ግብ ጠባቂው ያወጣት ሙከራዎችም ቡድኑን አቻ ለማድረግ የተቃረቡ ሙከራዎች ነበሩ። ጥቂት ሙከራዎች የተደረጉበት ጨዋታም በሽረ ምድረ ገነት አሸናፊነት ተጠናቋል።