ኢትዮጵያ መድን ወሳኙን የሜዳ ላይ ጨዋታውን በሌላ ሀገር ያደርጋል

ኢትዮጵያ መድን ወሳኙን የሜዳ ላይ ጨዋታውን በሌላ ሀገር ያደርጋል

በካፍ ቻምፒየንስ ሊግ የሁለተኛ ዙር የማጣሪያ ጨዋታ የግብፁን ፒራሚድስ የሚገጥመው መድን በሜዳው የሚያደርገውን ጨዋታ በሌላ ሀገር እንዲከውን ውሳኔ ተላለፈ።

የወቅቱ የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ሻምፒዮኑ ኢትዮጵያ መድን በአፍሪካ ቻምፒየንስ ሊግ ሀገራችንን እየወከለ የሚገኝ ሲሆን በመጀመሪያው ዙርም የዛንዚባሩን ምላዴግ ገጥሞ በድምር ውጤት በማሸነፍ ወደ ሁለተኛ ዙር ማለፉ ይታወቃል። በሁለተኛው ዙር የግብፁን ሀያል ክለብ ፒራሚድስ የሚገጥመው ቡድኑ ከኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ጨዋታው ጎን ለጎን ለወሳኙ ፍልሚያ ዝግጅቱን እያከናወነ ይገኛል።

ሶከር ኢትዮጵያ አሁን ባገኘችው መረጃ መሠረት መድን የሜዳ ላይ ጨዋታውን ለማድረግ መጀመሪያ አበበ ቢቂላ ስታዲየምን ከዛም የድሬዳዋ ስታዲየምን ለማስመዝገብ ጥረቶችን ቢያደርግም ካፍ እንዳልተቀበለው ታውቋል። በተለይ የአበበ ቢቂላ ስታዲየም ምንም እንኳን የመጀመሪያውን ዙር ጨዋታ ቢያስተናግድም በካፍ ገምጋሚዎች ታይቶ ለሁለተኛ ዙር ጨዋታዎች ብቁ እንዳልሆነ መገለፁ ተመላክቷል።

በዚህን መሠረት ኢትዮጵያ መድን ሀገሩ ላይ የሚያደርገው ጨዋታ ወደ ሩዋንዳ መዘዋወሩ ታውቋል። በዚህም የፊታችን እሁድ ጥቅምት 16 የመጀመሪያ ጨዋታውን መድን ኪጋሊ ላይ ሲያደርግ የመልሱን ጨዋታ ደግሞ ጥቅምት 22 ካይሮ ላይ የሚያከናውን ይሆናል።

ከኢትዮጵያ መድን ጋር በተያያዘ ቡድኑ አህጉራዊ ጨዋታዎች ስላሉበት በኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ በሁለተኛ፣ ሦስተኛ እና አራተኛ ሳምንት የሚያከናውናቸው ጨዋታዎች ወደ ሌላ ጊዜ እንደሚዘዋወሩ ይጠበቃል።