ሪፖርት | ኢትዮጵያ ቡና ተከታታይ ድል አስመዝግቧል

ሪፖርት | ኢትዮጵያ ቡና ተከታታይ ድል አስመዝግቧል

ቡናማዎቹ አቡበከር አዳሙ ባስቆጠረው ብቸኛ የፍፁም ምት ግብ ሀዲያ ሆሳዕናን አሸንፈዋል።

ተመሳሳይ ነጥብ በመሰብሰብ ጨዋታቸውን ያደረጉት ሁለቱ ቡድኖች በኳስ ቁጥጥሩ ተሽለው ወደ ተጋጣሚ የግብ ክልል መድረስ የቻሉት ኢትዮጵያ ቡናዎች 11ኛው ደቂቃ ላይ የሀዲያ ተጫዋች ከራሳቸው የግብ ሳጥን ውስጥ ኳስ በእጅ መንካታቸውን ተከትሎ ያገኙትን የፍፁም ቅጣት ምት አቡበከር አዳሙ ድንቅ በሆነ መንገድ ወደ ግብነት ቀይሮ ቡናማዎችን መሪ ማድረግ ችሏል።

በሀዲያ ሆሳዕና በኩል 20ኛው ደቂቃ ላይ ከሜዳው የግራ መስመር የተሻገረውን ኳስ ቃለአብ ውብሸት በእግሩ ጨርፎ የሞከረው ኳስ ለጥቂት በግቡ ቋሚ በኩል ወጥቶበታል።

ከዕረፍት መልስ 55ኛው ደቂቃ ላይ አቡበከር አዳሙ መሀል ለመሀል የሰነጠቀልትን ኳስ በጥሩ ሩጫ ያገኘው በፍቃዱ አለማየሁ ወደ ግብ ቢሞክረውም ግብጠባቂው ኦውሱ እንድሪውስ ወደ ውጭ አውጥቶታል።

የአቻነት ግባቸውን ለማግኘት ጫና ፈጥረው ለመጫወት የሞከሩት ሀድያ ሆሳዕናዎች 74ኛው ደቂቃ ላይ ናትናኤል ሞገስ ከቅጣት ምት ጥሩ ሙከራ ማድረግ ቢችልም ግብጠባቂው ዳንላድ ኢብራሂም ጨርፎ አውጥቶታል።ይህንንም ተከትሎ በአቡበከር አዳሙ ብቸኛ ግብ ቡናማዎቹ 1-0 ማሸነፍ ችለዋል።