የምኞት ደበበ ቅጣት ጉዳይ?

የምኞት ደበበ ቅጣት ጉዳይ?

መነጋገሪያ የሆነው የፋሲል ከነማው ተከላካይ ምኞት ደበበ ቀይ ካርድ ጉዳይ እና የአራት ጨዋታዎች ቅጣትን በተመለከተ ያለውን የህግ ማዕቀፍ ለማጣራት ሞክረናል።

የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ የ10ኛ ሳምንት ጨዋታዎች ከዓርብ እስከ እሁድ የተደረጉ ሲሆን በጨዋታ ሳምንቱ ሁለተኛ ቀን የተደረገው የፋሲል ከነማ እና ነገሌ አርሲ ጨዋታ በስፖርት ቤተሰቡ ዘንድ ከፍተኛ የመነጋገሪያ ርዕስ ይዞ ብቅ ብሏል። በጨዋታው ድል የቀናው ፋሲል ከነማ በ79ኛው ደቂቃ አምበሉ ምኞት ደበበን በቀይ ካርድ ያጣበት ሁነት በተለይ ምስሉን በቴሌቪዥን ምልሰት ለተመለከተ የስፖርት ቤተሰብ ከውሳኔው በተቃራኒ እንዲቆም አስችሎታል። ታዲያ ጨዋታው ከተጠናቀቀ በኋላ የቡድኑ ዋና አሠልጣኝ ዮሐንስ ሳህሌን ጨምሮ ብዙዎች ተጫዋቹን በቀጥታ ቀይ ካርድ ያስወጡት አልቢትር ሔኖክ አበበ ውሳኔ እንደሚቀለበስ በማሰብ አስተያየታቸውን ሲሰጡ የነበረ ቢሆንም የሊጉ የውድድር እና ሥነ-ስርዓት ኮሚቴ ከሰዓታት በፊት ባወጣው የዲሲፕሊን ውሳኔዎች ዝርዝር ምኞት በጨዋታው ባየው ቀይ ካርድ ምክንያት የአራት ጨዋታዎች ቅጣት ፀንቶበታል።

አብዛኛው የስፖርት ቤተሰብ ምኞት በጨዋታው ያየው ቀይ ካርድ እንደሚነሳለት በማሰብ ሀሳቦች ሲንሸራሸሩ ቢቆዩም የሜዳው ላይ ውሳኔ መፅናቱ የተወሰነ ግርታን ፈጥሯል። ሶከር ኢትዮጵያም የዳኛውን የሜዳ ላይ ውሳኔ እንዲሁም ከውሳኔው በኋላ ተጫዋቹ የተላለፈበት ቅጣት ተግባራዊ እንዲደረግ የሆነበትን የህግ ማዕቀፍ ከፌዴሬሽኑ የዳኞች ኮሚቴ እንዲሁም ከፕሪምየር ሊግ አክሲዮን ማኅበር በኩል ለማጣራት ሞክራለች።

ምኞት ያየው ቀይ ካርድ በዕለቱ ዳኛ እይታ እና የህግ አተረጓጎም የተከናወነ ቢሆንም ከሜዳ ላይ ውሳኔው በኋላ በገሀድ ከታየው “የውሳኔ ስህተት” በኋላ የተጫዋቹ የአራት ጨዋታዎች ቅጣት ለምን ተግባራዊ ተደረገ የሚለውን በተመለከተ ብሔራዊ የዳኞች ኮሚቴ በሜዳ ላይ በዳኞች የሚወሠኑትን የካርድ ውሳኔዎች በተመለከተ ውሳኔዎችን የመቀልበስ ምንም አይነት ሥልጣን እንደሌለው ገልፀው በሌሎች ሀገሮች እንደሚደረገው ግን የካርድ ውሳኔዎቹ ስህተት መሆናቸውን የሚያሳይ ትክክለኛ የቴሌቪዥ ምስል ከተገኘ ግን ስህተቶቹን ለማረም የሚያስችል አሠራር በውድድር ደንባችን ማካተት ብንችል የሚል ምክረ ሀሳብ ለኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ አክስዮን ማሕበር ቦርድ ማቅረባቸውን ነግረውናል።

የፌዴሬሽኑ የዲሲፕሊን መመሪያ ምዕራፍ አንድ አንቀፅ 73 ቁጥር 5 ላይ “ማንኛውም የፌዴሬሽን የስራ አስፈፃሚ አባል፣ የቋሚ ኮሚቴ አባላት፣ የፍትህ አካላት (ከተሰጣቸው ስልጣንና ኃላፊነት በስተቀር) የውድድርና የጨዋታ አመራሮች ጭምር አንድ ጨዋታ ከመጀመሩ በፊት ጨዋታው እየተካሄደና ጨዋታው ከተጠናቀቀ በኋላ የጨዋታ አመራሩ በቃልም ሆነ በካርድ ጨዋታ እንዳይካፈሉ ያገዳቸውን ተጫዋቾችና የቡድን አመራሮች በውሳኔ ማንሳት፣ መሰረዝ፣ መቀየርም ሆነ መሻር አይችሉም፡፡” በሚል የተቀመጠውን ህግ እንደ ዳኞች ኮሚቴ ሁሉ የሊጉ የበላይ አካል የሆነው አክሲዮን ማኅበሩም ውሳኔውን መሻር እንደማይችል በግልፅ አትቷል።

ይህንን መነሻ በማድረግ ምኞት ደበበ ያየው ካርድ በዳኞች ኮሚቴም ሆነ በአክሲዮን ማኅበሩ መሻር እንደማይችልና ሁለቱም አካላት የዳኛውን የሜዳ ላይ ውሳኔ መቀየር የሚችሉበት ስልጣን እንደሌላቸው ለማወቅ ተችሏል።