የግል አስተያየት| «ጨለማው» ሰንጠረዥ

የግል አስተያየት| «ጨለማው» ሰንጠረዥ

ሳሙኤል ስለሺ

 

ከቀናት በፊት ታዋቂው የዲጂታል ሰው አይሾው ስፒድ የብሄራዊ ቡድናችንን መለያ ለብሶ ኢትዮጵያ በተገኘበት እለት ብሄራዊ ቡድናችንን የሚመለከት ዜና ከወደ ሞሮኮ ተሰምቶ ነበር። ምንም እንኳን ይህ ዩቲበር እና ሌሎች ኢትዮጵያውያን የዲጂታል ሚዲያ ወጣቶች ይህንን የብሄራዊ ቡድን መለያ አጊጠውበት እና ተውበውበት በደስታ እና ፍሰሀ ቢናኙበትም ብሄራዊ ቡድናችንን በተመለከተ ከሞሮኮ የተሰማው ዜና ግን የሚያስቆዝም እና ብዙ ትንታኔ የሚያስፈልገው ነው። አዎ ኢትዮጵያ ከአፍሪካ የመጨረሻዎቹ 12 ሀገራት መሀከል ተደልድላ፥ ከደካሞች 6 የምስራቅ አፍሪካ ጎራ ተቀምጣ የአፍሪካ ዋንጫ የማጣሪያ ማጣሪያ እንድታደርግ ድልድል ወጥቷል። ይህ ለኢትዮጵያ እግር ኳስ አዲስ ነገር ባይሆንም «አዲስ» ስላልሆነ ተብሎ ግን እንዲህ በቀላሉ የሚታለፍ ሊሆን አይገባም። ኢትዮጵያ በፊፋ ያላት ደረጃ ለወትሮው የሚታወቅ ቢሆንም በዚህ መልኩ በሰንጠረዥ ሲቀርብ እና በፖለቲካ፣ በኢኮኖሚ፣ በታሪክ፣ በጂኦግራፊ በህዝብ ብዛት፣ በስነልቦና እና በሌሎች መለኪያዎች ከማንወዳደራቸው ሀገራት ጋር ስንደለደል «ለምን» ብሎ መሞገት የሚጠበቅ ነው።

ለእግር ኳስ ወዳድ ኢትዮጵያዊ፣ ለባለሞያው፣ ለተጨዋቹ፣ ለአሰልጣኞች እንዲሁም ለአመራሮች የኢትዮጵያን ስም እዚህ ሰንጠረዥ ውስጥ እንደማየት የሚያም ነገር ሊኖር አይችልም፤ ምን አልባትም ሀገሪቷን እንደ ሐገር ህዝቦቿንም እንደ ህዝብ የሚጠላ ካልሆነ በስተቀር። ይህ ሰንጠረዥ የኢትዮጵያ ስፖርትን ለሚመሩ፣ የኢትዮጵያ እግር ኳስን ለሚያስተዳድሩ፣ በአንድም ይሁን በሌላ መልኩ በኳሱ ዙሪያ ለሚገኙ ሰዎች ማነቃቂያ ፖስተር ነው።

ኢትዮጵያ በዚህ ደረጃ ስትገኝ የመጀመሪያዋ ባይሆንም የመጨረሻዋ ላይሆን እንደሚችል ማሰቡ ደግሞ የበለጠ ያማል። ነፃነቷን ጠብቃ ዘመናትን የቆየች ሀገር ትላንት የአለም ካርታን ከተቀላቀሉ ሀገራት ጋር ልትሰለፍ በቅታለች። እንኳን ሀገራችን ክለቦቻችን በእድሜ የሚበልጧቸው ሀገራት ዛሬ ምስጋና ለእግር ኳሳችን ይግባና እኩል አድርጎናል። እግር ኳሳችን ነፃ ሀገርነት ያወረሰንን «ትልቅነት» አጨናግፎ ከጦርነት እና ከእርስ በእርስ እልቂት በኋላ ከተወለዱ ሀገራት ጋር እኩል እንደሆንን ተምሳሌት ሆኖ ቀርቧል። በትላንትናዋ የጄኖሳይድ እልቂት የምትባንነው እና እንቅልፍ የማይወስዳት ቡሩንዲ’ጦርነት ያዋለዳት እና እስካሁንም እትብቷ የሚደማው ደቡብ ሱዳን የኢትዮጵያ አቻ ሆነው በአንድ ሰንጠረዥ ተቀምጠዋል። ምስጋና ለእግር ኳሳችን ይግባና። ማዕከላዊ መንግስት የተዳከመባት እና «ፌይልድ ስቴት» የሚል ስያሜ የተሰጣት ሶማሊያ የመንግስት ስርዓት ፀንቶ የቆየባትን ኢትዮጵያ ትከሻ ለትከሻ ለመለካካት እንደ እግር ኳስ የምትናፍቀው አለም አቀፍ መድረክ የለም።

ስፖርትን ከሚያወግዘው አሊሸባብ ጋር እየታገሉ አስራ አንድ ውሀ ሰማያዊ መለያ የለበሱ ተጨዋቾችን ማሰለፍ መቻላቸው ብቻ እንደ ስኬት ይቆጠርላቸዋል። በአምባገነን መንግስት ስር የምትተዳደር፤ ምርጫ አድርጋ የማታውቅ ሀገር ብለን የምናብጠለጥላት ኤርትራ በእግር ኳስ የኢትዮጵያ አቻ ለመሆን ዴሞክራሲያዊ እና ህብረ ብሄራዊ መንግስት አላስፈለጋትም። ተጨዋቾቿ ባገኙት አጋጣሚዎች ሁሉ የሚኮበልሉባት ኤርትራ ፕሮፌሽናል ኮንትራት ቀርቦላቸው’ቁርስ፣ ምሳ፣ እራት ተዘጋጅቶላቸው ከመሚጫወቱት ኢትዮጵያውያን ጋር «አቻ ናችሁ» ተብለው በአንድ ማዕድ ቀርበዋል። «ማዕዱን ይቋደሳሉ ወይስ መንግስታቸው እንደሚፈራው ከኤይርፖርት ይጠፋሉ?» የሚለው ጥያቄ መጋቢት ላይ የምናየው ይሆናል።

እነዚህ የህዝብ ብዛታቸው ተደምሮ የኢትዮጵያን የማያህል ሀገራት ከኢትዮጵያ ጋር አቻ ሆነው መሰለፋቸው «ህዝብ ቁጥር እንጂ የተለየ ትርጉም የለውም» ለሚሉ ተከራካሪዎች ትልቅ ማስረጃ ሆኖ መቅረብ ይችላል። «ህዝብ ሆድ ብቻ አይደለም እጅና እግር ይዞ ነው የሚወለደው» የሚሉ ተከራካሪዎችን አንገት አስደፍቷል። ከኢትዮጵያ አንፃር የተቀሩት 11 ሀገራት የአዲስ አበባን ሰፈሮች የሚያህል ህዝብ ቁጥር እንኳን የላቸውም። 107ሺህ የሚያህል የህዝብ ቁጥር ያላት ሲሸልስ ከኢትዮጵያ ጋር ሳይሆን ከአራዳ አልያም ከቂርቆስ ክፍለ ከተማ ጋር ለመመጣጠን የምትችገር ሀገር ናት። ሳኦቶሜም ብትሆን በ230ሺህ የህዝብ ብዛት ታክስ ሰብስባ፣ ስቴዲየም ሰርታ፣ ብሄራዊ ቡድን ገንብታ 130ሚሊየን የኢትዮጵያ ህዝብን ልትገጥም ከደጃፋችን ቆማለች።

እዚህ ደረጃ መገኘታችን የሚመዘምዝ ቁስልን በትኩስ ቢላ እንደ መብጣት ነው። 1950 ዎቹ እና 60ዎቹ ካፍን የመሰረተች፣ አፍሪካ ዋንጫን ያዘጋጀች እና የወሰደች ሀገር ምስጋና እጅ እና እግር ሳይሆን ሆድ ብቻ ይዘው ለተፈጠሩ የልጅ ልጆቿ ይግባና ከግብፅ፣ ናይጄሪያ፣ ሞሮኮ እና ሴኔጋል እኩል የአፍሪካ ዋንጫ ግማሽ ፍፃሜ ከመፋለም ወርዳ ወርዳ ከታናናሾቿ ጋር የማጣሪያ ማጣሪያ ለማድረግ ተገዳለች። በጊዜው ዋንጫ ያነሳችበት አዲስ አበባ ስቴዲየም አሁን ብሄራዊ ቡድኑን ካስተናገደ ድፍን አምስት አመታት አልፎታል። ስቴዲየሙ ሊጉን ወደ ማስተናገዱ ቢመለስም መረቦች «የጎል ፆም» የያዙ ይመስል እምብዛም ኳስ ሲቀማምሱ አይስተዋልም።

የባህር በር ጥቅምን በታሪኳ እና በተፈጥሯዊ አቀማመጧ የምታውቅ፤ ነገን ለማግኘት የምትሻ ሐገር መጨረሻዋ ከቻድ ጋር በአዛምድ የእግር ኳስ ሰንጠረዥ መገናኘት ሆኗል። ቻድ እንደ ዛሬዋ ኢትዮጵያ ሁሉ የባህር በር የሌላት ሀገር ብትሆንም የእርሷ ማጣት ግን ከኢትዮጵያም የከፋ የሚያደርገው የባህር በር በሌላቸው ሀገራት መከበቧ ነው (landlocked by landlocked countries)። ከሰሜን የሰሀራ በረሀ በሀሩሩ እና በአሸዋ ብናኞቹ ታዳጊ ኳስ ተጨዋቾቿን ያውካቸዋል፤ ከደቡብ የሳህል በረሀ እና ቀውስ ልጆቿን ይረብሽባታል። ውሀ ከወርቅ በላይ ዋጋ ያለባት ቻድ የአፍሪካ የውሀ ማማ ከሆነችው ኢትዮጵያ ጋር በአንድ ለመታየት በቅታለች፤ ይቺ በሁለት በረሀ መሀከል ተገኝታ በተፈጥሮ የምትጠበስ ሀገር የ13 ወር ፀጋ ከተላበሰችዋ ኢትዮጵያ፣ ለልጆቿ ምቹ እና ተስማሚ የአየር ሁኔታ ካቀረበችው ኢትዮጵያ ጋር ከመደልደል ያገዳት የተፈጥሮም ሆነ ሰው ሰራሽ ሀይል የለም።

የኢኮኖሚ ንፅፅሩ ከተነሳ ኢትዮጵያ መሸሸጊያ አይኖራትም። የእነዚህ 11 ሐገራት ጂዲፒ ተደምሮ የኢትዮጵያን አያህልም። 156ቢሊየን ዶላር ኖሚናል ጂዲፒ ያላትን ኢትዮጵያ የምትከተለው ሀገር 13 ቢሊየን ዶላር ያላት ሞሪሸስ እንደሆነች በማሳየት ንፅፅሩን ማቆም ይቻላል። መሰረተ ድንጋይ የተቀመጠለት አዲሱ አየር ማረፊያ በጀት የሁሉም ሀገራት አመታዊ በጀት ተደምሮ ትንሽ ቢያንስ ነው። በንፅፅር በዚህ ደረጃ ሀብታም የሆነችው ኢትዮጵያ ልዩ የሚያደርጋት የእግር ኳስ መሰረተ ልማት እና የእድገት ፕላን የላትም። አሁንም ክለቦቿ በፕሮፌሽናል ጋዜጣ የጠቀለሉ የለየለት አማተሮች ናቸው፥ አሁንም ሊጓ እንኳን የውጭ ገበያ የሀገር ውስጥ ሰው የራቀው የማይሸጥ እና የማይገዛ ሆኗል። ስልጠና ቦታ ከማይሰጣቸው የእለት ተእለት ደራሽ ስራ እና ለሪፖርት ብቻ ከሚደረጉ ተግባራት መሀከል ተመድቧል። ሳይንስ፣ ዘመናዊነት፣ እውቀት በገንዘብ ተሸፍነው ማንነት እና ማንአለብኝነት አገንግነው ወተዋል።

እነዚህ 11 ሀገራት እግር ኳሳቸው እዚህ ደረጃ ለመገኘቱ ሰበብ አላቸው። እነርሱ ከተፈጥሮ እርግማን ጋር ጉሮሮ ለጉሮሮ እየተናነቁ እኛ በምርቃቷ ላይ እንመፃደቃለን። እነርሱ የአየር ሁኔታን፣ ቅኝ ግዛትን፣ የህዝብ ብዛትን፣ ጂኦግራፊን፣ ታሪክን እንደሰበብ መደርደር ይችላሉ። ከማፈር ውጭ ይህ ግን ለኢትዮጵያ የሚሰራ አይደለም። ኢትዮጵያ ልዑላዊነቷን ጠብቃ ለዓመታት የቆየች ሀገር፣ የስፖርት ሚኒስትሪ ከእነ በጀቱ ያላት ሀገር፣ ፌዴሬሽን፣ ኮሚቴ ያደራጀች ሀገር፣ ዋና ከተማዋ የዲፕሎማቲክ መናኀሪያ፣ የአፍሪካ ህብረት መቀመጫ፣ ያለምንም እንከን የአፍሪካ ህብረት ጉባኤን በፀጥታ እና ያለምንም የደህንነት ችግር የምታከናውን ሀገር ናት። አብዛኞቹ ጋር ይሄ አይታሰብም፤ በነዳጅ የሰከሩ የቻድ አማፅያን ዋና ከተማዋ መቼ ገብተው መቼ እንደሚወጡ አይታወቅም፤ የሶማሊያ ፓይሬትሶች ለመሰል ዲፕሎማሲያዊ ግኑኝነቶች መሰናክል ናቸው።
ከሰሜን እስከ ደቡብ ከምስራቅ እስከ ምዕራብ በቀን ለ24 ሰዓት ዓመቱን ሙሉ ኳስን ለመጫወት የሚያስችል የአየር ሁኔታ፣ አንገትን ቀና አድርጎ የሚያስኬድ ታሪክ፣ ሰፊ የእግር ኳስ ባህል፣ ትልቅ የእግር ኳስ ባጀት ያለባት ሐገር እንዴት እዚህ ሰንጠረዥ ውስጥ እራሷን ለማግኘት በቃች? ማንስ እዚህ አረንቋ ውስጥ ከተታት? በኢትዮጵያ እግር ኳስ እየሆነ ያለው ሁሉ ለማፈር እንጂ ለእፍርት የማይመች ሆኗል።

«ስፖርት ገር ሀይል ነው» ከተባለ ገራገርነቱ ሁለት መልክ አለው። ሀገራት በስፖርት ውጤታማነታቸው እና ስኬታቸው ምክንያት በሌሎች ሀገራት፣ ህዝቦች እና መንግስታት ላይ መንፈሳዊ ቅናትን በማሳደር በጎ ጫናን በማስተላለፍ ምስልን ለመገንባት፣ እሴትን ለመሸጥ እና ግኑኝነትን ለማቀላጠፍ ያስችላል። ይህ አዎንታዊው የስፖርት ዲፕሎማሲ መልክ ሲሆን ሌላኛው እና አሉታዊው ስለት ደግሞ ከጀርባው ይገኛል። አለመቻልን፣ ደካማነትን፣ አይረቤነትን ለሌሎች ይናገራል… ያሳብቃል። ለማህበረሰብ የተሸናፊነትን ስነልቦና ያሻግራል፣ ለትውልድ አቅመ ቢስነትን ያወርሳል፣ ለሌሎች ሀገራት መጥፎ የአእምሮ አሻራን ያስቀምጣል። የስፖርት ገራገርነት በበጎነት ብቻ ሳይሆን በአሉታዊውም መልኩ ሊገለፅ ይችላል። ሀገራት በምንተክላቸው ችግኞች ብዛት እንደሚያውቁን በገነባነው ግድብ እንደሚያስታውሱን ባስዋብናቸው ከተሞች እንደሚያደንቁን ሁሉ በእግር ኳስ ደረጃችንም ይታዘቡናል። በተለይ እንዲህ ገመናን ግልጥልጥ አድርጎ በሚያሳይ ሰንጠረዥ ውስጥ ሲያገኙን በቀላሉ አቅማችንን እና ችሎታችንን ለመጠራጠር እድል ያገኛሉ። ሱፍ ለብሰው ወዲያ ወዲህ የሚሉ ልጆችዋ፤ አዳራሽ ውስጥ ማይክ ሲቀባበሉ የሚውሉ አመራሮቿ፤ በጥናት እና ምርምር የቆዘሙት ሙህራን እንዲሁም ለመግለፅ የሚከብደው አስነዋሪ የክለብ ስርዓቷ በዚህ የኢትዮጵያ ኪሳራ ላይ አንድም መጥፎ ስራ በመስራት አልያም ደግሞ የሚጠበቅባቸውን ሞያዊም ሆነ ሀገራዊ ግዴታ ባለመወጣት ተጠያቂ ከመሆን አይድኑም፤ አንድንም።

በታሪክ አጋጣሚ ከኢትዮጵያ መንግስት እጅ የገንዘብ ሽልማት እንደተቀበለ አበባ ጉንጉን እንዳጠለቀ እና በክብር እንደተስተናገደ ባለሙያ የመንግስትን ጠንካራ ጎኖች የምዘነጋ እና ውለታውን የምረሳ አይደለሁም፤ እንደ ውለታ ከተቆጠረ። ደረጃቸውን በጠበቀ መልኩ እየተጠናቀቁ ያሉ ሁለት ግዙፍ ስቴዲየሞች፤ ከከተማ ልማት ጋር አብረው የተሰሩ የአካባቢ ሜዳዎች፤ አጠቃላይ የስፖርት ባህል ለማስረፅ የተፈጠሩ ምቹ ሁኔታዎች እየፀደቁ ያሉ የስፖርት ፖሊሲዎች እና የህግ ማዕቀፎች እንዲሁም ያልተቋረጠ የክለቦች ድጋፍ የመንግስትን ፍላጎት እና አቅም የሚያሳይ ነው። ይህቺ ትልቅ የእግር ኳስ ሐገር አንዳንዴ በሚጠሏት፤ ሌላ ጊዜም ፍፁም እውቀት በሌላቸው፤ አለፍ ሲልም እጅግ የግል ጥቅማቸውን በሚያስቀድሙ ሰዎች እየተመራች እዚህ ደርሳለች። አሸልቧት ነው ከአለም ዋንጫ የራቀችው ስትባል ጭራሽ ጥልቅ እንቅልፍ ወስዷት እዚህ «ጨለማ» ሰንጠረዥ ውስጥ እራሷን አገኘችው። የእግር ኳስ ልማትን የተጠየፉ ክለቦችን «ወልዳ… ወልዳ…አሳድጋ… አጎርምሳ…» ያረጠች እስኪመስል ድረስ አንድ እንኳን አርአያ ሆኖ መውጣት የሚችል ክለብ ሳይኖራት የወላድ መካን ሆና ካሸለበችበት የሚቀሰቅሳት አጥታለች። ዛሬ የሀገርነት ተማፅኖን እያቀረበች ያለችው እና የመጀመሪያ እውቅናዋን በእስራኤል ያገኘችው ሱማሌ ላንድ ነገ እድል ገጥሟት ሀገር ከሆነች ፌዴሬሽን መስርታ’ብሄራዊ ቡድን አቋቁማ ከኢትዮጵያ ጋር ላለመመደቧ የጀመርነው ስትራቴጂክ የእድገት ፕላን የለም እና ማረጋገጫ ለማቅረብ አይቻልም።

 

ስለፀሐፊው

ፀሐፊው ሳሙኤል ስለሺ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የስፖርት ሳይንስ ት/ክፍል የእግር ኳስ እና የስፖርት ስነልቦና መምህር ሲሆኑ ሁለተኛ ዲግሪ ትምህርታቸውን በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ፣ በስዊድኑ ሉንድ ዩኒቨርሲቲ እና በጀርመኑ ሊያፕዚግ ዩኒቨርሲቲ ተከታትለዋል። በአሁኑ ሰዓትም በጀርመን ስፖርት ዩኒቨርሲቲ የአለም አቀፍ ስፖርት ልማት እና ፖለቲካ የሁለተኛ ዲግሪ ተማሪ ናቸው።