ቅድመ ጨዋታ መረጃዎች| የ16ኛ ሳምንት የመጀመሪያ ቀን ጨዋታዎች

ቅድመ ጨዋታ መረጃዎች| የ16ኛ ሳምንት የመጀመሪያ ቀን ጨዋታዎች

16ኛው ሳምንት የሲቢኢ የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ  በአዳማ በሚካሄዱ ሁለት ጨዋታዎች ጅማሮውን ያደርጋል። ጨዋታዎቹን የተመለከቱ መረጃዎችንም እንደሚከተለው አሰናድተናል።

 

ወላይታ ድቻ ከ ባህር ዳር ከተማ

ቀስ በቀስ ወደ ውጤት ማጣት ቀውስ ውስጥ እየገቡ የሚገኙት ወላይታ ድቻዎች ባለፈው ሳምንት ከነጌሌ አርሲ ጋር በተደረገው እና ጠንካራ ሆነው በቀረቡበት ጨዋታ በመጨረሻ ደቂቃ ባስቆጠሩት የፍጹም ቅጣት ምት ግብ ነጥብ ተጋርተው መውጣት ቢችሉም በጨዋታው የፈጠሯቸው ያለቀላቸው የግብ ዕድሎችን ግን ድል ለማሳካት በቂ ነበሩ። ቡድኑ አጨራረስ ላይ የሚታይበት ችግር እንዳለ ሆኖ በሊጉ ካደረጓቸው 15 ጨዋታዎች በ14ቱ ግብ ማስተናገዳቸው ትልቁ ራስ ምታታቸው ነው። አሰልጣኝ መሳይ ከዚህ በፊት ይታወቁበት የነበረውን የጨዋታ መንገድ መነሻ በማድረግ የመከላከል አደረጃጀቱ ለውጥ እንደሚታይበት ታምኖበት የነበር ቢሆንም እንደተጠበቀው አለመሆኑ ካለፉት አምስት ጨዋታዎች ሦስት ነጥቦችን ብቻ እንዲሰበስቡ አድርጓቸዋል።

ከወሳኙ የመቻል ጨዋታ ድል በኋላ ባለፈው ሳምንት ከመቐለ 70 እንደርታ ጋር ያለ ግብ የተለያዩት የጣና ሞገዶቹ የመከላከል አደረጃጀታቸው ጠንካራነት ትኩረትን የሚስብ ነው። ካለፉት 6 ጨዋታዎች አንድ ግብ ብቻ የተቆጠረበት ክፍሉ የቡድኑ የጀርባ አጥንት ቢሆንም የማጥቃት ኃይሉ ግን አሁንም ለአሰልጣኝ ደግአረገ ይግዛው አሳሳቢ ነው። ከተጠቀሱት 6 ጨዋታዎች በአንዱ ጨዋታ ብቻ ግብ ማስቆጠር የቻለው ቡድኑ ባለፉት 9 ጨዋታዎች ያስቆጠራቸው 4 ግቦች የተገኙትም ከአማካይ እና ከተከላካይ መስመር ተጫዋቾች ነው። በመሆኑም ከግብ በራቁ ቁጥር በራስ መተማመናቸውን እያጡ የመጡት የአጥቂ ስፍራ ተጫዋቾች ቶሎ ወደ ግብ አስቆጣሪነት በመመለስ የራሳቸውንም የቡድናቸውንም ረጅም ጉዞ መስመር ማስያዝ የግድ ይላቸዋል።

ባህር ዳር ከተማ አማኑኤል ገብረሚካኤልን በጉዳት ወንድሜነህ ደረጄ እና አንበሉ በረከት ጥጋቡን ደግሞ በቅጣት ሲያጣ ያለፉትን ሁለት ሳምንታት ያልነበረው መሳይ አገኘሁ ግን ከጉዳቱ በማገገሙ ለጨዋታው ዝግጁ እንደሆነ ተጠቁሟል። በወላይታ ድቻ በኩል ሙሉቀን አዲሱ እና ኬኔዲ ከበደ በጉዳት ምክንያት አይኖሩም።

ሁለቱ ቡድኖች ከዚህ ቀደም በሊጉ 12 ጊዜ ተገናኝተው ባህርዳር ከተማ 4 ፣ ወላይታ ድቻ 1 ጊዜ አሸንፈው 7 ግንኙነታቸው በአቻ ውጤት ተጠናቋል። የጣና ሞገዶቹ 11 ፣ የጦና ንቦቹ በበኩላቸው 5 ጎሎችን አስቆጥረዋል።

 

መቐለ 70 እንደርታ ከ ኢትዮ ኤሌክትሪክ

 

ባለፉት አምስት ጨዋታዎች ከሽንፈት የራቁት መቐለ 70 እንደርታዎች በእነዚህ ጨዋታዎች አንድ ግብ ብቻ ማስተናገዳቸው በርካታ ግቦች ሲቆጠሩበት የነበረው የመከላከል አደረጃጀት ያመጣውን ትልቅ ለውጥ የሚጠቁም ነው። አሰልጣኝ ጸጋይ ኪዳነማርያም ቡድኑን ከተረከቡ በኋላ ሦስተኛ ድላቸውን ለማሳካት ከጠንካራው ኢትዮ ኤሌክትሪክ ጋር ብርቱ ፉክክር የሚያደርጉበትን የቡድን ውቅር ይዘው መቅረብ ይጠበቅባቸዋል። ምዓም አናብስት ዛሬ ድል የሚያደርጉ ከሆነ በጊዜያዊነትም ቢሆን ከወራጅ ቀጠናው ተላቀው 16ኛ ደረጃ ላይ የሚቀመጡበትን ዕድል ያገኛሉ።

ከአንድ ሽንፈት እና ከሁለት የአቻ ውጤቶች በኋላ ባለፈው ሳምንት ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ላይ የ2ለ1 ድል የተቀዳጁት ኢትዮ ኤሌክትሪኮች በተለይም በዚህ ጨዋታ ላይ የነበራቸው ከፍተኛ የማሸነፍ ወኔ አስገራሚ ነበር። ዕረፍት የለሽ እንቅስቃሴ በማድረግ የሚታወቀው ቡድኑ ከመሪው ሲዳማ በአምስት ነጥቦች ዝቅ ብሎ አምስተኛ ደረጃ ላይ የሚገኝ ሲሆን ከፋሲል ከነማ (5) ቀጥሎ ዝቅተኛውን የግብ መጠን (6) ያስተናገደ ጠንካራ የመከላከል አደረጃጀት አለው። ሆኖም ግን በነገው ዕለት ከወራጅ ቀጠና ለመውጣት ከሚታትር ቡድን ጋር ጨዋታውን እንደማድረጉ ከፍተኛ ጥንቃቄ ይሻል።

መቐለ 70 እንደርታዎች በዛሬው ጨዋታ ጉዳት ላይ ከሰነበቱት ሱሌይማን ሐሚድ፣ ቦና ዓሊ፣ ዘርኢሰናይ ብርሀነ፣ አማኑኤል ልዑል እና ዮሐንስ ዓፈራ በተጨማሪ በመጨረሻው ጨዋታ ጉዳት አስተናግዶ ከሜዳ የወጣውን ተመስገን ተስፋየ ግልጋሎት አያገኙም። ከዚህ በተጨማሪ በቤተሰብ ጉዳይ ከቡድኑ ጋር ያልነበረው መሐሪ አመሀ ከዛሬው ጨዋታ ውጭ ነው። በመጨረሻው ጨዋታ በዓይኑ አከባቢ ጉዳት ገጥሞት ተቀይሮ ለመውጣት የተገደደው ጊት ጋትኮች ግን ከሕመሙ ሙሉ ለሙሉ ባያገግምም ለጨዋታው ዝግጁ እንደሆነ ታውቋል። በኢትዮ ኤሌክትሪክ በኩል በዛብህ መለዮ አሁንም በዚህ ጨዋታ የማይኖር መሆኑ ሲታወቅ ተከላካዩ በረከት ወልደዮሐንስ ግን ከጉዳት መልስ ልምምድ ቢጀምርም በጨዋታው ለቡድኑ አገልግሎት ይሰጣል የሚለው ነገር አጠራጣሪ ነው።

ሁለቱ ቡድኖች ከዚህ ቀደም 4 ጊዜ ተገናኝተው መቐለ 3 ኤሌክትሪክ ደግሞ 1 ጊዜ ሲያሸንፉ በጨዋታዎቹ መቐለ 4 በአንጻሩ ኤሌክትሪክ 2 ግቦችን ከመረብ አሳርፈዋል።