ከአንድ ዓመት ከዘጠኝ ወር የአሜሪካ ቆይታ በኋላ ወደ ሀገር ቤት የተመለሰው አማካይ ወደ ሊጉ ተመልሷል።

በአዳማ ከተማ ጀምሮ በኋላም በፋሲል ከነማ ድንቅ ዓመታትን በማሳለፍ ወደ አሜሪካ በማቅናት ለሀያ አንድ ወራት ለሎዶን ዩናይትድ በመጫወት ላይ የቆየው ኢትዮጵያዊው አማካይ ሱራፌል ዳኛቸው ከአሜሪካው ክለቡ ጋር በመለያየት ወደ ሀገሩ ከተመለሰ ሦስት ወራት አስቆጥሯል።
ወደ ሀገር ቤት ከተመለሰ በኋላ በዕረፍት ላይ የቆየው ሱራፌል የአጋማሹ የተጫዋቾች ዝውውር መከፈቱን ተከትሎ ተጫዋቹን ለማስፈረም ሸገር ከተማ እንቅስቃሴ ቢያደርግም ማረፊያው የሊጉ መሪ ሲዳማ ቡና ሊሆን ተቃርቧል።
የሲዳማ ቡና ከፍተኛ አመራሮች ከትናንት በስቲያ ሱራፌልን ወደ አዳማ ከተማ በመምጣት አናግረውት ድርድሩ በስኬት የተጠናቀቀ ሲሆን ዛሬ የህክምና ምርመራውን አድርጎ አጠናቋል። ነገ በይፋ ፊርማውን የሚያኖር ይሆናል።
በመተሀራ መርቲ የእግርኳስ ህይወቱን የጀመረው ሱራፌል በአዳማ ከተማ ከታዳጊ ቡድን እስከ ዋናው ቡድን ከተጫወተ በኋላ በእግርኳስ ሕይወቱ ወደ ነገሰበት ፋሲል ከነማ በማምራት የሊጉን ዋንጫ ማንሳቱ ሲታወቅ ከአንድ አመት ከመንፈቅ የአሜሪካ ቆይታ በኋላ ዳግም ወደ ሊጉ በመመለስ ለሲዳማ ቡና ፊርማውን የሚያኖር ሲሆን ቡናማዎቹ ወደ ዋንጫው ለሚያደርጉት ጉዞ የሱራፌል መፈረም ትልቅ አስተዋፆኦ ያደርጋል ተብሎ ይጠበቃል።

