ሀዋሳ ላይ በተደረጉ ጨዋታዎች ቡናማዎች ጣና ሞገዶችን 2-0 ሲያሸንፉ ኢትዮ ኤሌክትሪኮች አርባ ምንጭ ከተማን 4 -1 በሆነ ሰፊ ውጤት አሸንፈዋል

ኢትዮጵያ ቡና ከ ባህር ዳር ከተማ
በኳስ እንቅስቃሴ ረገድ በሁለቱም ቡድኖች መካከል ተመጣጣኝ ብልጫን ባስመለከተን አጋማሽ ላይ 14ኛው ደቂቃ ኢትዮጵያ ቡናዎች መሪ መሆን የቻሉበትን ግብ ማስቆጠር ችለዋል።
አዲሱ ፈራሚ ቢኒያም ጌታቸው መነሻውን ከቅጣት ምት ያደረገው እና በባህርዳር ከተማ ተጫዋች በግንባር ተጨርፎ ያገኘውን ኳስ በግንባሩ ገጭቶ በማስቆጠር አዲሱ ክለቡ የግብ ካዝናውን አሃዱ ብሎ ከፍቷል።
26ኛው ደቂቃ ላይም ባህርዳር ከተማዎች አማኑኤል ገብረሚካኤል ላይ የተሰራውን ጥፋት ተከትሎ ያገኙትን ፍጹም ቅጣት ምት ግርማ ዲሳሳ ቢመታውም በግብ ጠባቂው ዳንላንድ ኢብራሂም ጥረት ተመልሷል። ወደ ጨዋታ መመለስ የሚችሉበትን የግብ እድል ያባከኑት ባህርዳር ከተማዎች 35ኛው ደቂቃ ላይ በዮሐንስ ደረጀ አማካኝነት በድጋሚ ግብ ለማስቆጠር ያደረጉት ጥረትም በግብ ጠባቂው ጥረት ሳይሳካ ቀርቷል።
ከዕረፍት መልስ በጥሩ ሁኔታ መንቀሳቀስ የቻሉት ኢትዮጵያ ቡናዎች 56ኛው ደቂቃ ላይ ሁለተኛ ግባቸውን ማስቆጠር ችለዋል። በጥሩ ቅብብል ወደ ተጋጣሚ የግብ ክልል ይዘው የገቡትን እና ዲቫይን ዋቹኩዋ ያቀበለውን ኳስ ለዘላለም አባተ ወደ ግብነት ቀይሮ ቡድኑን በሁለት ግብ ብልጫ መሪ ማድረግ ችሏል። ከግቦቹ መቆጠር በኋላ ባህርዳር ከተማዎች ጫናዎችን ፈጥረው መጫወት ቢችሉም፣ ግብ ማስቆጠር ተስኗቸው ጨዋታው በቡናማዎቹ ሁለት ለዜሮ አሸናፊነት ተጠናቋል።
አርባ ምንጭ ከተማ ከ ኢትዮ ኤሌክትሪክ
ኢትዮ ኤሌክትሪኮች ፍጹም ብልጫ በወሰዱበት በመጀመሪያው አጋማሽ ገና በአራተኛው ደቂቃ የአርባ ምንጭ ከተማ ተከላካዮች ኳሱን በአግባቡ አለማራቃቸውን ተከትሎ ያገኘውን ኳስ ፓትሪክ ሲቦማኔ ከሳጥን ውጭ አክርሮ ድንቅ ጎል በማስቆጠር ቡድኑን መሪ ማድረግ ችሏል። ከግቡ መቆጠር በኋላ አርባ ምንጭ ከተማዎች በመሃል በመልሶ ማጥቃት በጄሮም ፍሊፕ ቡጣቃ ሽመና ሙከሬዎች እጅግ ለግብ ቢቀርቡ ነገር ግን 16ኛው ደቂቃ ላይ የአርባ ምንጩ ግብ ጠባቂ ኢድሪሱ ኦጎዶጆ በሰራው ስህተት ተከትሎ አቤል ሀብታም ኳሷን ወደ ግብነት በመቀየር ኢትዮ ኤሌክትሪክን በሁለት ግብ ልዩነት መሪ አድርጓል።

የአጋማሹ መደበኛ የጨዋታ ሰዓት ሊጠናቀቅ ሁለት ደቂቃዎች ሲቀሩትም ፓትሪክ ሲቦማኔ በጥሩ እይታ አመቻችቶ ያቀበለውን ኳስ አንዋር በድሩ ወደ ግብነት በመቀየር ኢትዮ ኤሌክትሪኮች ጨዋታውን ከዕረፍት በፊት መግደል የቻሉበትን ግብ ማስቆጠር ችሏል።
በመጀመሪያው አጋማሽ በሦስት ግቦች ሲመሩ የነበሩት ኢትዮ ኤሌክትሪኮች በሁለተኛው አጋማሽ መጀመሪያ ላይ ብልጫቸውን ወደ አራት ግቦች አሳድገዋል። በ48ኛው ደቂቃ ሀሰን ሁሴን ያሻገረለትን ኳስ አቤል ሀብታሙ ከመረብ ጋር በማገናኘት በጨዋታው ለራሱ ሁለተኛ ለቡድኑ ደግሞ አራተኛ ግብ አስቆጥሯል። አርባ ምንጭ ከተማዎች በበኩላቸው ልዩነቱን ለማጥበብ ጥረት ያደረጉ ሲሆን በተለይ በፍቅር ግዛቸው በ54ኛው ደቂቃ ያባከናት ወርቃማ የግብ ዕድል የሚቆጭ ነበረች።
ከአራተኛው ግብ በኋላ የጨዋታው ግለት ቀዝቀዝ ብሎ ቢቆይም አዞዎቹ ተስፋ ሳይቆርጡ ወደ ተቃራኒ የግብ ክልል መድረሳቸውን ቀጥለዋል። ጨዋታው ወደ መጠናቀቂያው ደቂቃዎች ባመራበት ወቅትም አብነት ወደ ሳጥን ያሻገረለትን ኳስ ይገዙ ቦጋለ በግንባሩ በመግጨት አርባ ምንጭን ከተማን በባዶ ከመሸነፍ ያዳነች ግብ አስቆጥሮ ጨዋታው ተጠናቋል።

