«መስኮቱ»

«መስኮቱ»

ሳሙኤል ስለሺ

በኢትዮጵያ ስነ ቃል «መስኮት» እንደ አገባቡ ሁለት ፅንፍ ትርጓሜዎች አሉት። አንድም የጠዋት ብርሀን መፈንጠቂያ፥ የፀሀይ ብርሀን ድቅድቅ ጨለማን አሸንፎ የትላንት «ነገ» ላይ እንደደረስን ማብሰሪያ ነው። መስኮት ማናፈሻ፥ ንፁህ አየር ማስገቢያ ዋንኛ የቤት ቁመና አካል ነው። «መስኮት» እቤት ውስጥ ለተቀመጠ አንድ ሰው አርቆ ማያ፥ አሻግሮ መመልከቻ መነፅር ነው። በተቃራኒው «መስኮት» የሌባ ትልቁ መሳሪያ ነው፥ «በመስኮት ገብቶ በመስኮት ነው የወጣው» የሚሉ የምስክር ሐረጎችን በየፖሊስ ጣቢያው መዝገብ ፈልጎ ማግኘት የሚከብድ አይመስልም። እቤት ውስጥ እንዲገቡ የማይፈቀድላቸው ነገሮች በሙሉ ከዛፍም፥ ከጓሮም መተው የሚገቡት በመስኮት ነው።

ይህንን ያነሳሁት አዲስ የመስኮት አሰራር ለማስተዋወቅ ግድ ብሎኝ ሳይሆን የኢትዮጵያ እግር ኳስ የውድድር አመቱ አጋማሽ የዝውውር መስኮት ትላንት መዘጋቱን ተከትሎ ተያያዥ ሐሳቦችን ለመግለፅ እና ከወደፊት የትውልድ ተጠያቂነት እራስን ለማዳን ነው። ምንተስኖት አዳነ ከሰባተኛ ፖድካስት ጋር ያደረገውን «ዘግናኝ» ቆይታ አጣጥሜ ሳልጨርስ፥ የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን «የፀደቁ ውሎች የካቲት 27/2018ዓ.ም» በማለት በማህበራዊ ትስስር ገፁ የለቀቃቸውን ዝውውሮች ስመለከት በኢትዮጵያ እግር ኳስ እንደመታከትም፥ እንደመሰላቸትም አይነት ስሜት ተሰማኝ።

ፌዴሬሽኑ ምንም እንኳን እንደከዚህ ቀደሙ የዝውውር ሒሳቡን ለምን እንደሆነ በማላውቀው ነገር ግን በምገምተው ምክንያት ይፋ ባለማድረግ የግልፀኝነትን ጉዳይ ቢነሳበትም በተከታታይ የሚያቀርባቸው እና ሰንዶ የሚይዛቸው መሰል ሰነዶች በእጅጉ ሊደነቁ የሚገባቸው እንደሆኑ እመሰክራለሁ። ቀደም ባሉት ጊዜያት «መቼ ምን ተደረገ» የሚለውን ነገር እንዳናውቅ ሆነ ተብሎ መረጃ የሚታፈንበትን ስርአት አስተካክሎ መሰል መረጃዎች ማቅረቡን ሳላደንቅ አላልፍም። ለወደፊት ጥናትና ምርምር እንዲሁም ሲፈርሙ እና ሲያስፈርሙ የነበሩ ሰዎችን ለማሞገስም ይሁን ለመጠየቅ ሰፊ በር የሚከፍት እና ለመሸላለምም ሆነ ለመወቃቀስ የሚመች አሰራር ሆኖ አግኝቼዋለሁ… በርቱ!

በኢትዮጵያ እግር ኳስ ውስጥ ያለው የተጨዋቾች ዝውውር ተጨዋቾችን የሚያጠፋ፥ ክለቦችን የሚያቆረቁዝ፥ የኢትዮጵያ እግር ኳስን ወደ ኋላ የሚጎትት፥ ገንዘብ-ጎጥ-ፖለቲካ-ወንጀል የሚስተዋልበት፥ ከምንም በላይ ደግሞ በኢትዮጵያ ህዝብ ሞራል የሚቀልድ እና የኢትዮጵያ ህዝብ ገንዘብን አለአግባብ የሚያድፋፋ የጥፋት መስኮት ነው የሚል እምነት አለኝ። በዚህ ዙሪያ የተወሰነ ትምህርት እንዳለውና አካዳሚክ ጥናቶችን እንዳጠና፥ የፌዴራል ስፖርት ሪፎርም እና የእግር ኳስ ፌዴሬሽኑ የተለያዩ ጥናቶች ላይ እንደተሳተፈ ባለሙያ፥ ሚዲያ ላይ የሚቀርቡ የግል እና የቡድን ውይይቶችን እንደሚከታተል እና ከሁነኛ መረጃ ሰጪዎች (Key- Informants) ጋር የመገናኘት እድሉ እንዳለው ሰው አስተያየት የመስጠት ሐገራዊም ሆነ ሙያዊ ግዴታ አለብኝ ብዬ ስለማምን ይሄንን እና መሰል ፅሁፎችን አጋርቼያለሁ።

ከአምስት አመታት በፊት በ«ልዩ ስፖርት» ድረ ገፅ ላይ ሶስት ተከታታይ ፅሁፎችን (የተጨዋቾች ዝውውር እና ያለ ባህሪው የተያዘው የኢትዮጵያ እግር ኳስ – ክፍል አንድ፥ የተጨዋቾች ዝውውር እና ያልተረጋጋው የኢትዮጵያ እግር ኳስ- ክፍል ሁለት፥ የተጨዋቾች ዝውውር በኢትዮጵያ እግር ኳስ: የተቀየረው ገንዘብ ባልተቀየረው አሰራር – ክፍል ሶስት) በሚሉ ርዕሶች ያቀረብኳቸውን ፅሁፎች ማንበብ ይቻላል። ሆኖም ግን ምንም የተለየ ነገር ሳይፈጠር እኔ «ውሻው» መጮሄን እነሱ «ግመሎቹ»ም መጓዛቸውን ቀጥለናል።

ወደ ቀደመ ነገሬ ስመለስ ይህ የካቲት 27/2018ዓ.ም በተዘጋው መስኮት 32 ተጨዋቾች ወደ 15 ክለቦች የተዘዋወሩ ሲሆን የተፈራረሙበትም የጊዜ ገደብ እስካልተቀመጠው የውሰት ውል ጀምሮ እስከ አንድ አመት ከግማሽ ድረስ ይዘልቃል። ጠቅለል ባለ አገላለፅ እና ባለው የኢትዮጵያ እግር ኳስ ልማድ መሰረት እነዚህ ሁሉ ተጨዋቾች በሚቀጥለው አመት አጋማሽ 100% ወደ ሌላ ክለብ ይዘዋወራሉ ማለት ነው። የግማሽ አመት የውድድር «መስኮት» የቡድንን ጉልበት ለመጨመር፥ ክፍተትን ለመሙላት እና አዲስ ብርሀን ለመፈንጠቅ አስፈላጊ ነው ብዬ ባምንም በጥቅሉ የኢትዮጵያ እግር ኳስ «መስኮት» የእግር ኳሳችን አንዱ የጥፋት እና የነውር መከናወኛ መድረክ እንደሆነ ግን በዙሪያው ጥናትና ምርምር እንደሚያደርግ እንዲሁም የተለያዩ የስፖርት አካላትን የሚዲያ ኢንተርቪው እንደሚሰማ ባለሙያ በርግጠኝነት መናገር እችላለሁ።

ጥር 30 የተከፈተው መስኮት ተጨዋቾችን፥ ክለቦችን እና ሐገሪቷን ለመሰል ጥፋት ዳርጎ የካቲት 27 ተዘግቷል። የፋይናንስ ተጠየቅነትን ጉዳይ ሳላነሳ ዝውውሩ እግር ኳሳዊ በሆኑ አመክንዮች ብቻ መሞገት ይቻላል፤ በአራት አመት ውስጥ ለሶስት ክለብ የሚፈርም፥ ዋንጫ ባገኘባቸው ተጨዋቾች እራሱን ለማጠናከር ከመሞከር ይልቅ አዳዲስ ዝውውሮች ላይ የሚተጋ ክለብ፥ የቡድን ግንባታ እና የተጨዋች እድገት «በስክነት» ይመጣል ብለው የማያምኑ፥ ትላንት የቀጠሩትን ዛሬ የሚሸኙ፥ ዛሬ የቀጠሩትን ለነገ ለማላቅ የማይተጉ፥ ያለምንም ስካውቲንግ ሪፖርት «ልጄ ይወድሀል» (ዶናልድ ትራምፕ ስታይል) በሚል ተጨዋች የሚያስፈርም አመራር እና ባለሙያ በመስኮቱ ሲንሸራሸሩ ከርመዋል።

ሰው ልጅ የተከራየበትን ቤት ሲቀይር እንኳን ወደ ቀልቡ ለመመለስ እና በስራው ውጤታማ ለመሆን ጊዜ ይወስድበታል። ከጎረቤት ለመግባባት፥ ታማኝ ባለሱቅ ለመምረጥ እና ደንበኛ ለመያዝ፥ ውሀ የምትመጣበትን እና የምትሄድበትን ሰዓት ፓተርን ለማጥናት፥ ታክሲው የት ይያዛል፥ ስንት ሰዓት ላይ ሰልፉ ቀለል ይላል በማለት ስትራቴጂ ለመንደፍ እና ሙሉ ትኩረቱን ስራው ላይ ለማድረግ ጊዜ እንደሚወስድበት ሁሉ አንድ ተጨዋችም ከተማ ቀይሮ፥ ክለብ ቀይሮ፥ አሰልጣኝ ቀይሮ፥ ከጎኑ የሚጫወቱ ተጨዋቾችን ቀይሮ፥ የደጋፊውን ድባብ ቀይሮ እንዲህ ባለ የአጭር ጊዜ ውል የአቅሙን እና የችሎታውን አውጥቶ ለማሳየት ይቸገራል። የኢትዮጵያ ክለቦች ግን ይሄ ደንታቸው አደለም፥ ስለ Roster turnover ስለ Club Stability ፅንሰ ሀሳቡን አለመረዳታቸው ብቻ ሳይሆን ለመረዳት አለመፈለጋቸው እና ቢፈልጉም አለመቻላቸው እንዳዝንላቸውም እንዳልፈርድባቸውም ያደርገኛል። (ለዚህ ነው ቢገባቸው በከርታታ ተከራይ መስዬ ፅንሰ ሀሳቡን ያስቀመጥኩላቸው)።

አስረጂዎች

የቀድሞው የኢትዮጵያ ቡና አሰልጣኝ የነበረው አሰልጣኝ አብይ ከ15 ቀናት በፊት ኢቢሲ «ስለ ስፖርት» ፕሮግራም ላይ ቀርቦ «የሊጉ እንጂ የክለብ ሲኒየር» የለም ያለው አባባል ትልቅ መፅሀፍ ይወጣዋል። ጥቅሙን እና ውሉን አስከብሮ አንድ ክለብ ላይ ተረጋግቶ የሚጫወት ተጨዋች ማግኘት እጅግ አዳጋች ነው። ሊጉ ላይ 10 አመት ተጫውቻለሁ የሚል ተጨዋች ምን አልባትም አንድ ክለብ ቢበዛ ከ2 እና 3 አመት በላይ ሳይቆይ ከ4-5 የሚደርሱ ክለቦችን ሊጠቅስልህ ይችላል። ያልተረጋጋ ስርዓት የተረጋጋ ክለብን አይፈጥርም፥ ያልተረጋጋ ክለብ የተረጋጉ ተጨዋቾች አይኖሩትም። በክለቦቻችን አለመረጋጋት እና አለመስከን ሳቢያ የኢትዮጵያ እግር ኳስ ድክመት በኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን እየተመካኘ «ከደሙ ንፁህ ነን» የሚሉ ክለቦችን መመልከት የተለመደ ሆኗል። ኢትዮጵያ የሳኦቶሜ አቻ እንድትሆን ያደረጋት፥ ደካማ የእግር ኳስ ሀገር ያሰኛት – እግር ኳስን ያለማሉ ተብለው የተቋቋሙ ክለቦች ከልማት «በር» ይልቅ የዝውውር «መስኮት» መምረጣቸው ነው።

በወርሀ መስከረም ከመደበኛው የ2018ዓ.ም የዝውውር መስኮት መጠናቀቅን ተከትሎ በፕሪሚየር ሊጉ ከተመዘገቡ ተጨዋቾች መሀከል የ450 ተጨዋቾች መረጃን ለማየት እድሉ ገጥሞኝ ነበር። እንደመረጃው ከሆነ የኢትዮጵያ እግር ኳስ ክለቦች እና ተጨዋቾች አለመረጋጋት ፍንትው አድርጎ ያሳያል። ከተዘረዘሩት 450 ተጨዋቾች መሀከል «ነባሮቹ» ማለትም ከ2017 ዓ.ም የቀጠሉት 218 ብቻ ሲሆኑ በ2018 «መስኮት» የገቡት ደግሞ 232 ናቸው። የተሟላ መረጃ ቢገኝ ቁጥሩ ከዚህም ላቅ እንደሚል ታሳቢ በማድረግ ጠቅለል ባለ መልኩ ወደ መቶኛ ሲቀየር «በአማካኝ የአንድ ቡድን የቀድሞ መረጋጋት ጥቋሜ (Past Stability Index) 48.4% ብቻ ነው።» ይሄም ማለት በአማካኝ እያንዳንዱ ክለብ ከግማሽ በላይ የሚሆኑትን ተጨዋቾች «በመስኮቱ» ሸኝቶ አዳዲስ ተጨዋቾችን «በመስኮቱ» ቀላቅሏል ማለት ነው። ከአዳዲሶቹ ተጨዋቾች ምን ያህሉ- ምን ያህል ተጫወቱ? ምንስ ጠቀሙ? የሚለው ሌላ ሰፊ ትንተና የሚፈልግ የጥናት ሐሳብ በመሆኑ እዚህ ጋር ማንሳት አልወደድኩም።
በሰነዱ ይሄንን የሚደግፍ ሌላም መረጃ ፍንትው ብሎ ተቀምጧል፥ ከተዘረዘሩት 450 ተጨዋቾች መሀከል 201 ያህሉ በ2018 ዓ.ም መገባደጃ ላይ የውል ጊዜያቸውን የሚጨርሱ ሲሆን ሌሎች 194 ደግሞ በ2019 ዓ.ም ላይ ያገባድዳሉ። ይህም ማለት የክለቦች የወደፊት የመረጋጋት ጥቋሜ (Future Stability Index) በ2018 ዓ.ም መጨረሻ ላይ 55.3% እንዲሁም በ2019 ዓ.ም መደምደሚያ ላይ ደግሞ 12.2% ነው። ቁጥር እና መቶኛ ለሚገባው እንዲሁም የእግር ኳስ ፅንሰ ሀሳብን ለሚረዳ ሰው የዚህ አኀዝ ትርጉም የጎላ ነው። በአጭር ቋንቋ «በ2018 በአንድ ክለብ መለያ ከተጫወቱ 11 ተሰላፊዎች መሀከል፥ በ2020 ማልያውን ለብሶ ሜዳ ላይ የሚቀረው በማጠጋጋት አንድ ተጨዋች ብቻ ነው፥ አስሩ እንደ ርችት ይበተናሉ» የሚል ይሆናል። ይሄ «የርችት» ተርጓሜ ታይተው ወዲያው የሚጠፉ፥ ሳይጠገቡ የሚከስሙ፥ ውስጣቸው ያለውን ብርሀን እና ጥበብ ከሽርፍራፊ አመታት ውጭ ማሳየት የማይችሉ፥ ዘመንን የማይሻገሩ እላይ ተምዘግዝገው መሬት ለማረፍ ጊዜ የማይወስድባቸው አይነት ክለቦችን እና ተጨዋቾችን ይወክላል።

ያለመስከን ነፀብራቅ የሆነው ሊግ

የሊጉን ውጤታማነት እና የክለቦችን አሀዝ በማየት ባልተረጋጋ ዝውውር የጎደለብን እንጂ የሞላልን ነገር እንደሌለ ሊጉ ላይ ጠለቅ ያለ ትንተና ሳላደርግ እንደ ማሳያ ብቻ ላይ ላዩን ማቅረብ ይቻላል። የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግን ከሁለት ጨዋታ አራት ነጥብ በማግኘት (አንድ ማሸነፍ አንድ አቻ በመውጣት) ሻንፒዮን የሚኮንበት አይነት ሊግ መልክ ይዟል። ሊጉ ውስጥ ካሉ 20 ክለቦች መሀከል በአንድ ጨዋታ በአማካኝ አንድ ጎል ማስቆጠር የማይችሉ ክለቦች ብዛት 13 ነው፥ ለአንድ ሐገር ሊግ ይሄ ሁሉ ክለብ የትዬለሌ ነው- «አንድ ሳምንት ሙሉ በልቼ፥ ጠጥቼ፥ ሆቴል ተኝቼ፥ ሰልጥኜ፥ አሰልጥኜ ለደጋፊዬ አንድ ጎል መስጠት ካልቻልኩ ምን ትርጉም አለኝ?» የሚል ግለ ሂስ አዕምሮው ውስጥ የማይመላለስበት ሰው ካለ ስለጤንነቱ ሊጠነቀቅ ይገባዋል። በአማካኝ በሁለት ጨዋታ 3 ጎል ማስቆጠር የሚችል ክለብ ደግሞ ሊጉ ውስጥ አለመኖሩ ደግሞ ሌላው የዚህ ድክመት አስረጂ ነው- በአማካኝ በ2 ጨዋታ 3 ጎል የሚያስቆጥር ክለብ የለም።

ሊጉ ላይ ጎል አይቆጠርም ለሚለው ጥያቄ መከራከሪያ ሆኖ የሚቀርበው «ጥንቃቄ ስለሚበዛ ነው» የሚል ሀሳብ ነው። ይህ ማለት የሌላው አለም አሰልጣኞች ስለማይጠነቀቁ ነው ሊጋቸውን በጎል ያንበሸበሹት ወደሚል መደምደሚያ እንዳይወስደን እፈራለሁ። እንኳን 38 ሳምንት የሚቆይ የሊግ ጨዋታ ቀርቶ እንደ አለም ዋንጫ እና ቻምፒየንስ ሊግ ያሉ የጥሎ ማለፍ ጨዋታዎች እንኳን ጎሎችን ሲያመርቱ ደጋፊን ቁጭ ብድግ ሲያደርጉ ይስተዋላል። (በዚህ ሳምንት አትሌቲኮ ማድሪድ ያንን ሁሉ ተጠንቅቆ እንኳን በባርሴሎና 3 ጎሎችን ከማስተናገድ ያዳነው የለም)። እንደ እኔ ግን የዚህ ሁሉ ምክንያት «መስኮቱ» ነው፤ በዚህ መስኮት ምክንያት ተጨዋቾች «ገባ ወጣ» ክለቦች ደግሞ «የፈጠነ» ሆነዋል። በ«ገባ ወጣ» እና በ«ፈጠነ» የተቃኘ ስብስብ ደግሞ ለመዋሀድ፥ ለመናበብ እና ለመፍጠር ይቸገራል። ማጥቃት ደግሞ ከፈጠራ ጋር የተያያዘ፥ በአይን መናበብን የሚጠይቅ (Eye to Eye Knowing) እና የተጨዋቾችን የአእምሮ መግባባትን (Telepathic Connection) የሚፈልግ ነው። ተጨዋቾች በዚህ ደረጃ እንዲግባቡ እና እንዲፈጥሩ ደግሞ አብሮ መቆየት የነገሮች ሁሉ መጀመሪያ ነው፥ በ«መስኮት» በሚዘወር ክለብ ፈጠራን መጠበቅ ቂልነት ነው።

ይህ ጤናማ ያልሆነ እና ፍፁም ከእግር ኳስ መርህ ያፈነገጠ ኢ-እግር ኳሳዊ ዝውውር ተጨዋቾች ከአቅማቸው ይልቅ ኔትዎርካቸውን እንዲተማመኑ፥ ከስልጠና ይልቅ ብሄራቸው ላይ ተስፋ እንዲጥሉ፥ ከላባቸው ይልቅ ኪሳቸው ላይ ጥገኛ እንዲሆኑ እያደረጋቸው ከቦሌ አየር ማረፊያ በኋላ ተፈላጊ እንዳይሆኑ አድርጓቸዋል። አሰልጣኞችም ተሰሚነት የሌላቸው የሚሉት የማይደመጥ የማይናገሩት የማይሰማ፥ እንኳን ታክቲካቸው- ታሪካቸው እራሱ የሚያጠያይቅ እየሆነ መጥቷል። በዚህም ክለቦች እና ብሄራዊ ቡድናችን ከስመው ማህበረሰብ ላይ ጥቁር ጠባሳ የሚጥሉ፥ ተሸናፊነትን እና ተንበርካኪነትን ለትውልድ የሚያስተላልፉ፥ ለመፋቅ እጅግ ከባድ የሆነ መጥፎ አሻራ እያስቀመጡ ይገኛሉ።

ከትሪቡን እስከ ሜዳ

ትልቁ ጥያቄ ይሄ ስርአት እግር ኳሳዊ ካልሆነ እና ለተጨዋቾችም ሆነ ለክለቦች፥ እንዲሁም ለሀሪቷ እግር ኳስም የሚጠቅም ካልሆነ «ከየት መጣ?»፥ «እንዴት መጣ?»፥ «ማን አመጣው?»፥ «ለምን መጣ? «ማንስ አስቀጠለው?» የሚሉና መሰል ጥያቄዎችን ማንሳትና መሞገት ያስፈልጋል። ይህንን ስርዓት የተከሉልን ሰዎች እና ለእኛ ያወረሱን «ታላላቆች» አሁንም ሱፍና ከረባት አድርገው በፀሀይ መነፅራቸው አይነ ውሀቸውን ከልለው ትሪቡኑ ዙሪያ ታድመው ክለብ እና እግር ኳስ እየመሩ ነው፤ ተጠያቂ ሆነው የሚቀርቡት አሰልጣኞችም ቢሆኑ ቱታቸውን ለብሰው ፊሽካቸውን ጎርሰው ከመስኩ ቆመው ድራማቸውን መተወን ቀጥለዋል። ስርአት በመትከል ረገድ ተጨዋችን መውቀስ ይኑርብኝ አይኑርብኝ ባላውቅም እነሱ በተፈጠረ ስርዓት ጥቅማቸውን አስከብረው እና ተባባሪ ሆነው መቆየትን ይፈልጋሉ እንጂ የአስተዳደር እና የአመራር እንዲሁም የአሰራር ስርዓት በማነፅ እና በማስተካከል ረገድ ስራቸውም ሆነ አቅማቸው ነው ብዬ አላምንም፥ ጫማ ሲሰቅሉ እግር ኳሱን ለመታደግ ከመረባረብ ውጭ።

ዛሬ በአደባባይ እና በጎዳና ኳስ ሰፍተው በመሸጥ ቤተሰብ ለማስተዳደር የሚጥሩ እናት ባሉባት ሐገር፥ ኳስን አልምተው፥ ክለብን አቃንተው- ለታዳጊዎች፥ ለአካባቢ እና ለሀገር መትረፍ የሚገባቸው ክለቦች ግን «በመስኮት» መግባትና መውጣትን ስራቸው አድርገውት ዝውውር ላይ ቢዚ ሆነዋል። የዚህ ኢ- እግርኳሳዊ መስኮት ጥንስስ ግን «ገንዘብ፥ ጥቅም፥ ሌብነት፥ ወንጀል፥ ኃጢያት (መዘርዘር እችላለሁ)» እንደሆነ መደምደም እችላለሁ። «ወጪ ከሌለ ገቢ የለም» በሚል አስተሳሰብ «ባየ በሰማ» የተደራጁ ኮሚቴዎችና ባለሙያዎች፤ የግብር ከፋዩን ገንዘብ «የተጨዋቾች ዝውውር» በሚል የባጀት ኮድ አማካኝነት እንቀራመት በሚሉና «በመስኮት መግባት እና መውጣትን» ስልታቸው ያደረጉ የእግር ኳሱ ዙሪያ ገባዎች የፈጠሩት ስልት ነው። ከውሀ፥ ከሩዝ እና ከፓስታ የሚቀሸብ ገንዘብ ከተጨዋቾች ዝውውር ከሚቀሸበው አንፃር እዚህ ግባ የሚባል ባለመሆኑ ይህ በአመት ሁለቴ የሚከፈተው «መስኮት» የብዙዎች መንጠላጠያ፥ የኢትዮጵያ እግር ኳስ የስርቆሽ በር እንደሆነ ብዙ ተጨዋቾች በተለያዩ ሚዲያዎች እማኝ ሆነው ቀርበው አስረድተዋል፤ በተለያዩ ጥናታዊ ፅሁፎችም ጉዳዩ ትኩረት እንዲሰጠው እና ተራ የተጨዋቾች ዝውውር ጉዳይ ብቻ ሳይሆን ከፍተኛ ወንጀል የሚሰራበት እንደሆነ ለመንግስት ለማሳየት ተሞክሯል። መንግስት «የኔው ሰዎች ናቸው፤ ይጠቀሙ» የሚል ፈቃድ የሰጠ እስኪመስል ድረስ ዝም ማለቱ የሚያስተዛዝብ ሆኖ በግለሰቦች የሚሰረዙ እና የሚደለዙ ህጎችን ከማርቀቅ ውጭ ለኢትዮጵያ ክብር የሚመጥን ሐብቷንም ሆነ እግር ኳሷን ማዳን የሚችል ስራ ለመስራት ግን እስካሁን አልተቻለም።

 

ስለፀሐፊው

ፀሐፊው ሳሙኤል ስለሺ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የስፖርት ሳይንስ ት/ክፍል የእግር ኳስ እና የስፖርት ስነልቦና መምህር ሲሆኑ ሁለተኛ ዲግሪ ትምህርታቸውን በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ፣ በስዊድኑ ሉንድ ዩኒቨርሲቲ እና በጀርመኑ ሊያፕዚግ ዩኒቨርሲቲ ተከታትለዋል። በአሁኑ ሰዓትም በጀርመን ስፖርት ዩኒቨርሲቲ የአለም አቀፍ ስፖርት ልማት እና ፖለቲካ የሁለተኛ ዲግሪ ተማሪ ናቸው።