በድሬዳዋ ዓለም አቀፍ ስታዲየም የወዳጅነት ጨዋታ ለማድረግ ቀጠሮ በያዘው የዋልያዎቹ ዝግጅት ዙሪያ የተጠናከረ ወቅታዊ መረጃ እናድርሳችሁ።

የፊፋን ካላንደር መሠረት በማድረግ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ከማላዊ አቻው ጋር ግንቦት 29 እና ሰኔ 2 ቀን በድሬዳዋ ስታዲየም የወዳጅነት የሚያደርግ ይሆናል። ይህን ተከትሎ በቡድኑ ወቅታዊ ሁኔታ አዳዲስ መረጃዎችን እናድርሳችሁ
– በአሁን ሰዓት ጥሪ የተደረገላቸው ተጫዋቾች ጨዋታቸውን ካደረጉበት ማግስት ጀምሮ ካዛንቺስ በሚገኘው ጁፒተር ሆቴል በመገኘት ሪፖርት ያደረጉ ሲሆን ትናንት ጨዋታ የነበረባቸው ተጫዋቾች ዛሬ ቡድኑን እንደተቀላቀሉ አውቀናል።
– ከሰሞኑ በአዳማ ከተማ የተካሄዱትን 34ኛ ሳምንት ጨዋታዎች በጠቅላላ በአካል በመገኘት የተከታተሉት አሰልጣኝ ዮሐንስ ሳሕሌ የ34ኛ ሳምንት የፕሪሚየር ሊግ ጨዋታዎችን መሠረት በማድረግ ከተጠቀሰው ዝርዝር ላይ ለውጥ ሊኖር እንደሚችል ቢገለፅም ይህን መረጃ እስካደረስናችሁ ድረስ በመስመር አጥቂው መስፍን ታፈሰ ምትክም ሆነ ሌላ አዲስ ጥሪ የተደረገለት ተጫዋች የለም።
– ለጥቂት ቀናት በአዲስ አበባ ልምምድ እየሠራ የሚቆየው ብሔራዊ ቡድኑ ጨዋታውን ወደ ሚያደርግበት ድሬዳዋ ከተማ የፊታችን ሐሙስ ወይም ዓርብ እንደሚጓዝ ይጠበቃል።
– ብሔራዊ ቡድኑ የመጀመሪያ ልምምዱን ዛሬ እንደሚጀምር ቢጠበቅም ለጊዜው ምክንያቱ ባልታወቀ ሁኔታ ዛሬ የመጀመሪያ ልምምዱን አንደማይሠራ አውቀናል። ከነገ ጀምሮ የሚኖሩ ልምምዶችን እንደተለመደው ሶከር ኢትዮጵያ በቦታው በመገኘት ፈጣን መረጃዎችን የምታደርሳችሁ ይሆናል።
– የማላዊ ብሔራዊ ቡድን አሰልጣኝ ካሊስቶ ፓሱዋ ለ23 ተጫዋቾች ጥሪ ባደረጉት መሠረት በብላንታየር ከተሰበሰቡ በኋላ ወደ ኢትዮጵያ በረራ በማድረግ በእነዚህ ሁለት ቀናት ውስጥ ወደ አዲስ አበባ የሚመጡ ይሆናል።
– ጨዋታው በፊፋ የተመዘገበ (ዕውቅና) ያለው ከሆነ ከውጭ በመጡ ኢንተርናሽናል ዳኞች የሚከናወን ሲሆን ሆኖም በኢትዮጵያ ግብዣነት ብቻ የታሰበ ከሆነ ግን ኢትዮጵያውያን ኢንተርናሽናል ዳኞች ሊመሩት እንደሚችሉ ያገኘነው መረጃ ያመላክታል።
– በጊዜያዊ አሰልጣኝ ኢንስትራክተር ዳንኤል ገብረማርያም እየተመራ የነበረው ኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ከሁለት ዓመት በፊት በአፍሪካ ዋንጫ ማጣሪያ ከማላዊ ጋር ተጋጥሞ ጨዋታው ያለ ጎል የተጠናቀቀበት ጨዋታ የቅርብ ጊዜ ትውስታ ነው።

