ለወትሮም ቢሆን ከሀገሬው ማህበረሰብ አይንና ልብ እየራቀ ለመጣው ብሔራዊ ቡድናችን የሚዲያዎች ሽፋን ክልከላው ነገሮችን አያባብሳቸውምን?
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ባለፉት አምስት ዓመታት የካፍን ዝቅተኛ መስፈርት የሚያሟሉ ስታዲየሞች ባለመኖራቸው ሳቢያ በስደት በኪራይ ስታዲየሞች ሲንከራተት ሰንብቷል ፤ ይህ አሳዛኝ የታሪክ አጋጣሚ ብሔራዊ ፌደሬሽኑን አለፍ ሲል ሀገርን ለከፍተኛ ወጪ ከመዳረጉ ባለፈ በብሔራዊ ቡድናች ዙርያ በሚሊንየሙ ጅማሮ ከ31 ዓመታት በኃላ ወደ አፍሪካ ዋንጫ መመለሱን ተከትሎ የተፈጠረውን ከፍተኛ መነቃቃትን በሂደት እንዲያጣ ምክንያት ሆኗል።
ይህ መቀዛቀዝ ከሜዳ ላይ ውጤት ባለፈ ለብሔራዊ ቡድኑ በሀገሬው ዘንድ የሚሰጠው ትኩረት እንዲያሽቆለቁል አድርጓል ፤ ከጥቂት ወራት በፊት ብሔራዊ ቡድናችን በአፍሪካ ዋንጫ ቅድመ ማጣርያ ሳኦቶሜና ፕሪንሲፔን ሲገጥም በጨዋታዎቹ ቀናት ቡድኑ ጨዋታ እንደነበረው የሚያቀው ሰው መጠን በጣም አስደንጋጭ ነበር ፤ በጨዋታው ወቅትም በዲጂታል አማራጮች ጨዋታው በሚተላለፍባቸው አማራጮች የነበረው ዝቅተኛ የተመልካች ቁጥርም ለዚህ አይነተኛ ማሳያ ነበር።
ይህ ጉዳይ የሀገሪቱን እግርኳስ በበላይነት ለሚመራው ብሔራዊ ፌደሬሽኑ ሆነ ለሀገሪቱ እግር ኳስ ግድ ለሚሰጠው አንድ ዜጋ በጣም አስደንጋጭ ነው ፤ ሀገርን የሚወክል ብሔራዊ ቡድን ጨዋታ ኖሮት በተባራሪ “እንዴ ዛሬ አላቸው እንዴ?” ተብሎ ሲጠየቅ መስማት ልብን ያደማል። ይህ የትኩረት ማነስ የብዙ ምክንያቶች ድምር ውጤቶ መሆኑ ቢታመንም በብሔራዊ ቡድኑ እና በሰፊው ህዝብ መካከል ያለ መስተጋብር መላላት ግን ከዓበይት ምክንያቶቹ አንዱ ነው።
የሀገሪው ሚዲያ ከሀገር ቤት እግር ኳሳዊ ሁነቶች ይልቅ የብሩኖ ፈርናንዴዝ የዓመቱ ምርጥነት ፣ የአርሰናል የፕሪምየር ሊግ ዋንጫ ዓይነ ጥላ መገፈፈ አብዝቶ ሲያስጨንቀው ይውላል ታድያ ይህን ምዕራባዊያን ዘመም አካሄድ ሰብረው ጥቂቶች ለብሔራዊ ቡድኑ ድምፅ ለመሆን የሚጥሩ ሚድያዎች ስለሀገሪቱ እግር ኳስ እና ብሔራዊ ቡድናችን መዘገባቸው አልቀረም።
ለዚህም አሰልጣኝ ዮሀንስ ሳህሌ ሳኦቶሜን ሞሮኮ ላይ ከመግጠማቸው አስቀድሞ በነበረው ጋዜጣዊ መግለጫ ላይ በብሔራዊ ቡድኑ ዝግጅት ወቅት በልምምድ ሜዳዎች እየተገኙ ሽፋን ለሰጡና መረጃዎችን ለህብረተሰቡ ሲያደርሱ ለነበሩ የመገናኛ ብዙሃን አባላት እውቅና በመስጠት ምስጋና ማቅረባቸው አይዘነጋም።
ይህ ከሆነ ከወራት በኃላ ፌደሬሽኑ ዛሬ ማለዳ ደግሞ በማህበራዊ ትስስር ገፁ ትላንት ልምምድ የጀመረውና ከቀናት በኃላ በወዳጅነት ጨዋታ ማላዊን የሚገጥመው ቡድኑ በዕለተ ዕሮብ ከሚከውነው ልምምድ ውጭ ልምምዶቹ ለሚድያ ዝግ መሆናቸውን ይፋ አድርጓል።

ይህ ውሳኔ ፌደሬሽኑ ባለፉት ጥቂት ወራት ይከተለው ከነበረው ዓለምአቀፋዊ አሰራር ማለትም የብሔራዊ ቡድኑ የመጀመሪያ 15 ደቂቃዎች ልምምድ ለሚዲያ ክፍት ይሆናሉ ከሚለው እሳቤ ጋር የሚፃረር ሲሆን ለወትሮውም በጣት ከሚቆጠሩ ትኩረታቸውን በሀገር ቤት እግር ኳስ ላይ ካደረጉ መገናኛ ብዙሃን ባለፈ የሚዲያ ሽፋን ድርቅ ለሚመታው የብሔራዊ ቡድናችን ዝግጅት በብዙ መስዋዕትነት ዋጋ ከፍለው ልምምዱን ለመዘገብ የሚጥሩ አካላትን ሞራል የሚነካው ይህ ውሳኔ ከጥቅሙ ይልቅ ጉዳቱ ያመዘነ ይመስላል።
ይህ የፌደሬሽኑ አካሄድ እጅግ ኃላቀርነት የተላበሰ ከዓለም አቀፍ ተሞክሮዎችም ጭምር የተፃረረ ነው ፤ ለአብነት ትላንት ለ2026ቱ ዓለም ዋንጫው ወደ ማያሚ ያቀናው የእንግሊዝ ብሔራዊ ቡድን ወደ ፓልም ቢች ኢንተርናሽናል ኤርፓርት ጉዞ ሲጀምር እና ሲደርስ በሃገሪቱ ታላላቅ ሚዲያዎች ጭምር ሽፋን ሲያገኝ ለተመለከተ እያንዳንዷ የህዝብ ግንኙነት ስራ ስላላት ዋጋ ለመረዳት አይቸገርም።
የወቅቱ ብሔራዊ ቡድን አሰልጣኝ ዮሀንስ ሳህሌ ከዚህ ቀደምም በዋልያዎቹ አለቃነት በሃላፊነት በቆዩባቸው ዓመታት በሜዳ ላይ ካስመዘገቧቸው ስኬቶች ይልቅ የሚታወሱት ከሚድያ አካላት ጋር በሚፈጥሩት ሰጣ ገባ ነበር ፤ አሁንም ዳግም ከዓመታት በኃላ ወደ ኃላፊነት ሲመለሱ ገና ከመጀመሪያው ጋዜጣዊ መግለጫ አንስቶ ከሚድያ አካላት ጋር የተለመደውን ውዝግብ የጀመሩ ሲሆን አሰልጣኙ ይህን ሁሉም ነገር ከእኛ በተቃራኒ ነው የሚለው የስጋት እሳቤን (Siege Mentality) ቡድኑን ወደ ውጤት ለመምራት ይጠቀሙበት ይሆን የሚለው ጉዳይ ይጠበቃል።
በመጨረሻም ብሔራዊ ቡድኑ ከ130 ሚልየን በላይ የምንሆን ኢትዮጵያዊያን የጋራ መገለጫ እንጂ የተወሰኑ ቡድኖች ወይንም ግለሰቦች የግል መጠቀሚያ አይደለም ፤ ለወትሮው የሚድያ ሽፋንን ለተጠማው ብሔራዊ ቡድናችን የተሻለ የተግባቦት(Communication) እና የህዝብ ግንኙነት ስራዎች እንጂ በድብቅ የሚሰሩ የትኛውም ስራዎች አለባብሰው ቢያርሱ እንዲሉ መጨረሻቸው በአደባባይ የሚታይ ነው ከዚህ ባለፈም ብሔራዊ ፌደሬሽኑ እንደማንኛውም መንግስታዊ ተቋም ህዝቡን ለማገልገል የተቋቋመ እንደመሆኑ መረጃን ለህብረተሰቡ ተደራሽ የማድረግ ግዴታውን ሊወጣ ይገባል።

