የግብ ዘቡ ከብሔራዊ ቡድኑ ጋር ልምምድ አልሰራም

የግብ ዘቡ ከብሔራዊ ቡድኑ ጋር ልምምድ አልሰራም

ለሚዲያ ዝግ በተደረገው የዛሬው የብሔራዊ ቡድን ልምምድ የግብ ዘቡ ተሳትፎ እንዳላደረገ ሶከር ኢትዮጵያ አውቃለች።

ከማላዊ አቻው ጋር ሁለት የወዳጅነት ጨዋታዎች ያሉበት የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ትናንት የመጀመርያ ልምምዱን በኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ሜዳ የሰራ ሲሆን ዛሬ ደግሞ ባልተለመደ ሁኔታ ለሚዲያ ዝግ የነበረውን ሁለተኛ ልምምዱን በአበበ ቢቂላ ስታዲየም ሰርቷል።

ረፋድ ላይ በአበበ ቢቂላ ስታዲየም በነበረው ልምምድ ወቅት 21 ተጫዋቾች የተሳተፉ ሲሆን የግብ ዘቡ አቡበከር ኑራ አለመኖሩን ሶከር ኢትዮጵያ ከምንጮቿ አረጋግጣለች። ምክንያቱ ምን እንደሆነ ባደረግነው ማጣራት በግል ጉዳይ ተጫዋቹ ፍቃድ ተሰጥቶት እንደሆነ አውቀናል። ተጫዋቹም የግል ጉዳዮን ጨርሶ ቡድኑን ይቀላቀላል ተብሎ ይጠበቃል።

በሌላ ዜና ብሔራዊ ቡድኑ በአጥቂ መስመር ከጠራቸው ስድስት ተጫዋቾች መካከል መስፍን ታፈሰ እና አዲስ ግደይ ከስብስቡ ውጭ መሆናቸው ተከትሎ ዋና አሰልጣኙ በጎደሉት አጥቂዎች ምትክ አዲስ ጥሪ ያደርጋሉ ተብሎ ቢጠበቅም እስካሁን ምንም ተጫዋች አልጠሩም።