በአዲስ አበባ ስታዲየም የተደረጉ ጨዋታዎች በአቻ ውጤት ሲጠናቀቁ ሲዳማ ቡና የ2018 የሲቢኢ የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ ቻምፒዮን መሆኑን አውጇል።

ኢትዮጵያ ቡና ከ ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ
ዝናባማ በሆነ የአየር ሁኔታ በጀመረው የሁለቱ ቡድኖች ጨዋታ የጣለው ከባድ ዝናብ በሜዳው ላይ ውሃ እንዲቋጠር በማድረጉ ለተጫዋቾች ምቹ አልነበረም። በእንደዚህ ዓይነት አስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥም ኢትዮጵያ ቡናዎች በመጀመሪያው አጋማሽ በኳስ ቁጥጥር ረገድ ብልጫ መውሰድ የቻሉ ቢሆንም ወደ ተጋጣሚ የግብ ክልል በመድረስና ቀጥተኛ የግብ ሙከራዎችን በማድረግ ረገድ ግን የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ተጫዋቾች የተሻለ ብልጫ አሳይተዋል።

በዚህም ከማዕዘን ምት የተሻገረውን ኳስ ዘላለም አበበ በግንባሩ ገጭቶ የግቡ ቋሚ የመለሰበት እንዲሁም የተመለሰውን ኳስ ሁዜይፋ ሻፊ አግኝቶ ወደ ግብ መትቶት የቡናው ግብ ጠባቂ ታምራት ቅባቱ ያዳነበት አጋጣሚዎች በአጋማሹ ተጠቃሽ ሙከራዎች ነበሩ።

ከእረፍት መልስ በሁለተኛው አጋማሽ የኢትዮጵያ ቡና ተጫዋቾች የተለመደውን አጭርና ፈጣን የኳስ ቅብብሎሽ በመጠቀም ወደ ተጋጣሚ የግብ ክልል ለመድረስ የሞከሩ ሲሆን በአንጻሩ የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ስብስብ ደግሞ በፈጣን የጎንዮሽ መስመር ጥቃቶች ግብ ለማግኘት ብርቱ ጥረት አድርገዋል። ይሁን እንጂ የሁለቱም ቡድኖች ስልትና ጥቃት እንዲሁም ሁለቱ ቡድኖች ሶስተኛው የሜዳ ክፍል ላይ ባሳዩት ድክመት እና በተከላካዮች ጥንካሬ ምክንያት ሳይሳካ በመቅረቱ ጨዋታው ያለ ምንም ግብ 0ለ0 በሆነ አቻ ውጤት ፍጻሜውን አግኝቷል።
ሲዳማ ቡና ከ ነገሌ አርሲ
በርካታ ደጋፊዎች ህብረዜማ ታጅቦ የተጀመረው ተጠባቂው ጨዋታ በመጀመሪያው አጋማሽ ሲዳማ ቡናዎች በኳስ ቁጥጥርና ወደ ተጋጣሚ ክልል በመጠጋት የተሻለ ብልጫ ያሳዩበት ነበር።

ጨዋታው በ17ኛው ደቂቃ ላይ ግን ሁነቱን የቀየረ ክስተት ተፈጥሯል፤ የነገሌ አርሲው ቦና ቦካ በብርሃኑ በቀለ ላይ በሰራው ጥፋት ምክንያት በዋና ዳኛ ሃይማኖት አዳነ ውሳኔ ሰጪነት በሁለተኛ ቢጫ ካርድ ከሜዳ ተሰናብቷል። ይሁንና የቁጥር መጉደሉ ይበልጥ ያበረታቸው ነገሌዎች ጥቃታቸውን በመቀጠል በ33ኛው ደቂቃ ላይ ኪቲካ ጅማ ሞክሮ ለጥቂት በቋሚው በኩል የወጣችበትን አደገኛ ሙከራ ማድረግ ችለዋል።

በበርካታ ጥፋቶች ምክንያት በተደጋጋሚ ይቆራረጠ የነበረው የመጀመሪያው አጋማሽ የተሰጡት ጭማሪ ደቂቃዎች ተጠናቀው የዳኛው ፊሽካ በሚጠበቅበት ሰዓት የሲዳማ ቡና ደጋፊዎችን “ሮሪ ሲዳማ” እያሉ ያዜሙበት እና በደስታ የተናወጡበት ግብ ተቆጥሯል። 45+5 ላይ ከቀኝ ክፍል የተሻማውን የቅጣት ምት ደስታ ደሙ በግንባሩ ገጭቶ ያመቻቸለትን ኳስ ብርሃኑ በቀለ ወደ ግብነት ቀይሮ ቡድኑን መሪ አድርጓል። ይህች ግብም ሲዳማ ቡናን 1ለ0 በሆነ መሪነት ወደ እረፍት አሽጋግራለች።
ከእረፍት መልስ በሁለተኛው አጋማሽ ነገሌ አርሲዎች የተጫዋቾች ቅያሪ በማድረግና የአጥቂ መስመሩን በማጠናከር ወደ ተጋጣሚ የግብ ክልል በተደጋጋሚ ሲደርሱ የነበረ ሲሆን በሜዳ ላይ በቁጥር አንሰውም ቢሆን ያሳዩት ብርቱ ፉክክርና አልበገር ባይነት በመጨረሻም ፍሬ አፍርቶ በ76ኛው ደቂቃ ላይ የፍጹም ቅጣት ምት ለማግኘት አስችሏቸዋል። የሲዳማ ቡናው መላኩ አሰፋ በሳጥን ውስጥ ኳስ በእጁ መንካቱን ተከትሎ የተሰጠውን ይህንን የፍጹም ቅጣት ምት በረከት ወልዴ ወደ ግብነት በመቀየር የነገሌ አርሲን አቻነት ያበሰረበት ሲሆን ጨዋታውም ይበልጥ ተስፋና ግለት ታክሎበት ቀጥሏል።

ከግቧ መቆጠር በኋላ ሁለቱም ቡድኖች ድልን ፍለጋ እልህ አስጨራሽ ፍልሚያ ቢያደርጉም ተጨማሪ ግብ ሳይመዘገብ ጨዋታው 1ለ1 በሆነ የአቻ ውጤት ተጠናቋል። በዚህም መነሻነት ሲዳማ ቡና ለሻምፒዮንነት የሚያበቃውን ነጥብ በማረጋገጥ የ2018 የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ ባለድል መሆኑን በይፋ ያወጀበት አጋጣሚ ሆኖ አልፏል።

