በአሰልጣኝ በፀሎት ልዑልሰገድ የሚመሩት ኢትዮጵያ ንግድ ባንኮች ሴራሊዮናዊው የተከላካይ አማካይ ለማስፈረም ከስምምነት ደርሰዋል

በለቀቁባቸው ወሳኝ ተጫዋቾች ምትክ በክረምቱ የዝውውር መስኮት ተሳትፎ በማድረግ ቡድናቸውን በማጠናከር ላይ የሚገኙት ኢትዮጵያ ንግድ ባንኮች ሴራሎንያዊውን ሰይዱ ባህ ካማራ ለማስፈረም ከስምምነት ደርሰዋል።
ባለፉት አራት ዓመታት በአምበልነት ያገለገለበትን የሀገሩ ክለብ ቦ ሬንጀርስ እንዲሁም በሴራልዮን ብሔራዊ ቡድን መጫወት የቻለው ይህ የ24 ዓመቱ ተጫዋቹምች በቅርቡ በ2026 የምዕራብ አፍሪካ የስፖርት ሽልማት ላይ በምርጥ ተከላካይ አማካይነት ዘርፍ ኮከብ ተጫዋች ተብሎ የተሸለመ ሲሆን በ2025 የዓለም ዋንጫ ማጣሪያ ጨዋታ ላይ ሀገሩን ወክሎ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድንን መግጠሙ ይታወሳል።
ከዓመታት በፊት የሴራልዮን ፕሪምየር ሊግ ምርጥ ወጣት ተጫዋች ሽልማትን ያገኘው እንዲሁም በተጠናቀቀው የውድድር ዓመት በሊጉ ምርጥ 11 ውስጥ የተካተተው አማካዩ አሁን ደግሞ ለዓመታት ከተጫወተበት ቦ ሬንጀርስን በመልቀቅ የኢትዮጵያ ንግድ ባንክን ለመቀላቀል ከስምምነት ደርሷል። በአሁኑ ወቅት በቀድሞ የኢትዮጵያ ቡና አሰልጣኝ ፈረንሳዊው ዲድየር ጎሜስ ዳሮሳ ከሚመራው የሴራሊዮን ብሔራዊ ቡድን ስብስብ ጋር ያለው ተጫዋቹ የሀገር ግዴታውን ከተወጣ በኋላ ወደ ኢትዮጵያ በመምጣት ፌርማውን ያኖራል ተብሎ ይጠበቃል።

