ሎዛ አበራ የዋሽንግተን ዲሲው ክለብ ወሳኝ ተጫዋች መሆንዋን በማስመስከር ላይ ትገኛለች

ከውድድር ዓመቱ ጅማሮ በፊት ከክለቧ ዲሲ ፓወር ጋር ያላትን ውል ያራዘመችው አጥቂዋ ሎዛ አበራ አዲሱ የውድድር ዓመት በድንቅ ብቃት ጀምራዋለች። በተጠናቀቀው ወር ከብሩክሊን እና ሌክሲንግተን ጋር ባደረገቻቸው ጨዋታዎች ሦስት ግቦችን ማስቆጠር የቻለችው ሎዛ ከስኬታማው ወር በኋላ የጌይንብሪጅ ሱፐር ሊግ የወሩ ምርጥ 11 ውስጥ ተካታለች።
ባለፈው የውድድር ዓመት አፕሪል ወር ላይ በተመሳሳይ የሊጉ ምርጥ 11 ስብስብ ውስጥ መካተት ችላ የነበረችው ሎዛ በመጨረሻዎቹ ሁለት ጨዋታዎች ላይ ሦስት ግቦች በማስቆጠር የዋሽንግተን ዲሲው ክለብ ወሳኝ ተጫዋች መሆንዋን በማስመስከር ላይ ትገኛለች። በአዲሱ የውድድር ዓመት በተደረጉ ሦስት ጨዋታዎች ስድስት ነጥብ መሰብሰብ የቻለው ዲሲ ፓወር በሦስተኛ ደረጃ ላይ መቀመጥ የቻለ ሲሆን በአራተኛው ሳምንትም ከሦስት ቀናት በኋላ ከስፖርቲንግ ጋር የሚጫወት ይሆናል።

