ሜዳም ላይ ከሜዳም ውጪ መዋቅራዊ ለውጥ እያደረገ የሚገኘው ቅዱስ ጊዮርጊስ በቀጣዩ ሳምንት አጋማሽ ከሀገር ውጪ ጉዞ ሊያደርግ ነው።

የቀድሞ አለቃውን ሰርዲዮቪን ሚሉቲን ሚቾ ዳግም በመንበሩ የቀጠረው ቅዱስ ጊዮርጊስ ያለፉትን ወራት ከአስተዳደራዊ እስከ ሜዳ ድረስ የተለያዩ ለውጦችን እያደረገ ክለቡን እንደ አዲስ እያደራጀ የሚገኝ ሲሆን በክረምቱ የዝውውር መስኮትም በርከት ያሉ አዳዲስ ተጫዋቾችን ይጠቅሙኛል ካላቸው ነባር ተጫዋቾች ጋር አቀላቅሎ ለቀጣዩ የውድድር ዓመት ዝግጅቱን ቀጥሏል። ቡድኑ የቅድመ ውድድር ዝግጅቱን መቀመጫውን በክቡር ይድነቃቸው ተሰማ አካዳሚ አድርጎ እያከናወነ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድንን ጨማሮ ከሌሎች የሀገር ውስጥ ቡድኖች ጋር የአቋም መፈተሻ ጨዋታ ያከናወነ ሲሆን በቀጣዩ ሳምንት ደግሞ ወደ ታንዛኒያ አምርቶ ሁለት የአቋም መፈተሻ ጨዋታዎችን እንደሚያደርግ ሶከር ኢትዮጵያ አውቃለች።
ክለቡ በይፋ እስካሁን ስለጉዞው ያለው ነገር ባይኖርም የዝግጅት ክፍላችን እንዳገኘችው መረጃ ከሆነ ቡድኑ የፊታችን ረቡዕ ወደ ታንዛኒያ ዳሬሰላም የሚያቀና ሲሆን በሀገሪቱ ታላቅ ስም ካላቸው አዛም እና ያንጋ አፍሪካንስ ጋር ተከታታይ ሁለት የአቋም መፈተሻ ጨዋታዎችን የሚያደርግ ይሆናል።
ከዚሁ ጋር በተያያዘ የቀድሞ የቡድኑ የቪዲዮ ተንታኝ እና ምክትል አሠልጣኝ የነበረው አዲስ ወርቁ በአሁኑ ሰዓት በአዛም ቤት የፍሎረንት ኢቤንጌ ምክትል አሰልጣኝ ሲሆን በአቋም መፈተሻ ጨዋታውም የቀድሞ ክለቡን በተቃራኒ የሚገጥም ይሆናል።

