የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ከሀዋሳ ወደ አዲስ አበባ አድካሚ የመኪና ላይ ጉዞ በኋላ አመሻሽ ላይ ልምምዱን ሠርቷል።

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ለ2027 በአፍሪካ ዋንጫ ከሴኔጋል፣ ሞዛምፒክ እና ከሱዳን አቻው ጋር መደልደሉ ይታወሳል። ለእነዚህ ጨዋታዎች ይረዳው ዘንድ ለአርባ ተጫዋቾች ጥሪ በማድረግ ያለፉትን ሳምንታት ዝግጅቱን ሲያደርግ ቆይቷል።
– ከቅዱስ ጊዮርጊስ ፣ ከ20 ዓመት በታች የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን እና ከሀዋሳ ከተማ ጋር የአቋም መለኪያ ጨዋታ አድርጓል።
– ሄኖክ አዱኛ እና ግሩም ሀጎስን በጉዳት ሲያጣ ዘጠኝ ተጫዋቾችን ደግሞ ከስብስቡ ቀንሷል።
– በአዲስ አበባ ከጀመረው ዝግጅት በኋላ ወደ ሀዋሳ በማቅናት ሲዘጋጅ የቆየው ብሔራዊ ቡድኑ ዛሬ አድካሚ የመኪና ላይ ጉዞ ካደረገ በኋላ 08:30 አዲስ አበባ የደረሰ ሲሆን ማረፊያውን ጁፒተር ሆቴል አድርጓል።
– አሰልጣኝ ዮሐንስ ሳሕሌ ብሔራዊ ቡድኑ ነገ ወደ ደቡብ ሱዳን ከማቅናቱ በፊት ዘጠኝ ሰዓት ላይ ለመገናኛ ብዙሃን ጋዜጣዊ መግለጫ ከሰጡ በኋላ አስራ አንድ ሰዓት ላይ በአደይ አበባ ስታዲየም ልምምዳቸውን ሠርተዋል።
– በቡድኑ ውስጥ ምንም ዓይነት የጉዳት ዜና የሌለ ሲሆን 23 ተጫዋቾች በመልካም ጤንነት ላይ እንደሚገኙ አውቀናል።
– ብሔራዊ ቡድኑ ነገ ከሰዓት ወደ ደቡብ ሱዳን ከማቅናቱ በፊት በአዲስ አበባ የመጨረሻ ልምምዱን እንደሚሠራ ተሰምቷል።
– ቡድኑ ከሱዳን ጋር ዓርብ ጨዋታውን አድርጎ ቅዳሜ ወደ አዲስ አበባ ከተመለሰ በኋላ ወደ ባህር ዳር የሚያቀናው ቡድኑ ባሉት ቀናቶች ዝግጅት የሚያደርግ ይሆናል።
– ዓርብ መስከረም 15 ቀን ከሱዳን እንዲሁም ማክሰኞ መስከረም 19 ቀን በባህር ዳር ዓለም አቀፍ ስታዲየም ከሴኔጋል ጋር ጨዋታውን የሚያደርግ ይሆናል።

