በአብዩ አረጋሽ
በሲቢኢ የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ የአራተኛ ሳምንት የሁለተኛ ቀን ጨዋታ ኢትዮ ኤሌክትሪክ ኢትዮጵያ ቡናን 1 ለ 0 በማሸነፍ ተከታታይ ድሉን አስመዝግቧል።

በጨዋታው የመጀመሪያ አጋማሽ ሁለቱም ክለቦች ብርቱ ፉክክር ያደረጉ ሲሆን በአጋማሹ የተሻለ እንቅስቃሴ ያሳየው ኢትዮ ኤሌክትሪክ በጭማሪ ደቂቃ መሪነቱን መያዝ ችሏላ። በ45ኛው ደቂቃ ላይ በተጨመሩት 2 ደቂቃዎች ላይ አሸናፊ ተገኝ ከግራ መስመር ወደ ሳጥን የላካትን ኳስ አቤል ሀብታሙ በግንባሩ በመግጨት ወደ ግብነት ቀይሮ ኢትዮ ኤሌክትሪክን መሪ አድርጓል።

በሁለተኛው አጋማሽ ኢትዮጵያ ቡና ወደ ጨዋታው ለመመለስና አቻ ለመሆን ጥረት ቢያደርግም የኢትዮ ኤሌክትሪክን መከላከል ሰብሮ ግብ ማስቆጠር አልቻለም። ኢትዮ ኤሌክትሪክም የአንድ ግብ መሪነቱን እስከ መጨረሻው በማስጠበቅ ሶስት ነጥቡን አስጠብቋል።
በዚህም ኢትዮጵያ ቡና በውድድር ዘመኑ ሶስተኛ ሽንፈቱን ሲያስተናግድ፣ ኢትዮ ኤሌክትሪክ በበኩሉ ተከታታይ ድሉን አስመዝግቧል።

