አቡበከር ናስር የሜዳ ላይ ልምምዱን ዛሬ ጀምሯል

አቡበከር ናስር የሜዳ ላይ ልምምዱን ዛሬ ጀምሯል

በኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ታሪክ በአንድ የውድድር ዘመን በርካታ ጎሎችን በማስቆጠር ባለሪከርድ የሆነው የመቻሉ ተጫዋች አቡበከር ናስር ከጉዳት መልስ ዛሬ ወደ ልምምድ ተመልሷል።

በኢትዮጵያ እግርኳስ ከታዩ ምርጥ አጥቂዎች መካከል አንዱ የሆነው አቡበከር ናስር እጅግ ስኬታማ ቆይታ ካሳለፈበት ኢትዮጵያ ቡና በመቀጠል ወደ ደቡብ አፍሪካው ኃያል ክለብ ማሜሎዲ ሰንዳውንስ ከዛም ወደ ሱፐር ስፖርት ዩናይትድ እና ወደ ፕሪቶሪየ ዩኒቨርስቲ ክለቦች አምርቶ የነበረ ቢሆንም ጉዳት በታሰበው ልክ አቅሙን አውጥቶ እንዳይጫወት እንዳደረገው ይታወቃል። ታዲያ ተጫዋቹ በክረምቱ ወደ ሀገር ቤት ሲመለስ በሁለት ዓመት ውል መቻልን መቀላቀሉ አይዘነጋም።

ከጉዳት ጋር ዘለግ ላለ ጊዜ የቆየው አቡበከር በጦር ኃይሎች ሆስፒታል የፊዚዮቴራፒ ህክምናውን እየተከታተለ በቀን ሁለት ጊዜ የጂም እንቅስቃሴዎችን ሲያደርግ የቆየ ሲሆን በዛሬው ዕለትም ከረዥም ጊዜ በኋላ ወደ ሜዳ ወጥቶ የሜዳ ላይ ልምምድ ማድረግ መጀመሩን ሶከር ኢትዮጵያ አውቃለች። በትናንትናው ዕለት የመቻልን ስብስብ በይፋ ሆቴል በመግባት የተቀላቀለው አቡበከር ዛሬ ረፋድ ቡድኑ በራሱ ሜዳ ልምምድ ሲሰራ በአብዛኛው ለብቻው አልፎ አልፎ ከአጋሮቹ ጋር ቀለል ያሉ እንቅስቃሴዎችን ሲያደርግ እንደነበረ አውቀናል።

አቡበከር በ2013 የውድድር ዘመን በ24 ጨዋታዎች 29 ጎሎችን በማስቆጠር በኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ታሪክ በአንድ የውድድር ዘመን በርካታ ጎል በማስቆጠር ሪከርድ በመያዝ የኮከቦች ሽልማትን ጠራርጎ በመውሰድ ባለ ታሪክ ተጫዋች መሆኑ ይታወሳል።

በተያያዘ ዜና የቡድኑ ወሳኝ ተጫዋቾች የሆኑት ግሩም ሀጎስ እና ዳዊት ማሞም እንደ አቡበከር በዛሬው ዕለት ወደ ልምምድ መመለሳቸውን ሰምተናል።