በኩዌት ሊግ እየተጫወቱ የሚገኙት የዋልያዎቹ ሁለት ተጫዋቾች ብሔራዊ ቡድኑን መቀላቀል ጀምረዋል።

ከቀጣይ ሳምንት ጀምሮ በአፍሪካ ዋንጫ ማጣሪያ የምድቡን 3ኛ እና 4ኛ ጨዋታዎቹን ከሞዛምቢክ ጋር የሚያከናውነው የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ዝግጅቱን ከጀመረ ቀናት አስቆጥሯል። አሰልጣኝ ዮሐንስ ሳሕሌ ከሀገር ውጭ ከሚጫወቱ ተጫዋቾች በኩዌት ሊግ የሚገኙት ጋቶች ፓኖም እና ከነዓን ማርክነህን መጥራታቸው ይታወሳል።
ለአል ፋሂሊን ክለብ የሚጫወተው ጋቶች ፓኖም ብሔራዊ ቡድኑን መቀላቀሉ ሲታወቅ ዛሬ ከሰዓት በንግድ ባንክ ሜዳ ብሔራዊ ቡድኑ በሚኖረው ልምምድ ላይ መሳተፍ የሚጀምር ይሆናል።
ትናንት ለክለቡ አል አረቢ ጨዋታውን ያደረገው ከነዓን ማርክነህ ዛሬ አዲስ አበባ እንደሚገባ የሚጠበቅ ሲሆን ምን አልባት እርሱም ከሰዓት በሚኖረው ልምምድ አልያም ነገ በሚኖረው ልምምድ እንደሚጀምር አውቀናል።
ከብሔራዊ ቡድኑ ጋር በተያያዘ ዜና መጠነኛ ሕመም ላይ ይገኙ የነበሩት ተከላካዩ በረከት ሳሙኤል እና የመስመር አጥቂው ቸርነት ጉግሳ ወደ ሙሉ ልምምድ መመለሳቸውን ሰምተናል።

