“በአስር አመት ካላወቁት በአንድ ጨዋታ ሊያውቁት አይችልም”
“የምንችለውን ሁላ አድርገን ውጤት ይዘን ለመውጣት ተዘጋጅተናል”
“የመከላከል ጨዋታ አይደለም የምንጫወተው ፤ ለማሸነፍ ነው የምንጫወተው”
“ጫና የለብንም ብንል ውሸት ይሆናል”
“አሁንም ቢሆን ምክትሎቹ ሊነሱ ይችላሉ እኔ አንዳንድ ጊዜ ልቀመጥ እችላለው ፤ እነሱ ተቀምጠው እኔም ልመራ እችላለው”
የ2027 የአፍሪካ ዋንጫ የምድብ የማጣሪ ጨዋታዎች ነገም ቀጥለው ሲደረጉ በምድብ 10 ዋልያዎቹ ከሞዛምቢክ ጋር ወሳኝ ጨዋታ ያደርጋሉ። ከጨዋታው አስቀድሞ በዋዜማው አሠልጣኝ ዩሐንስ ሳህሌ የቅድመ ጨዋታ አስተያየት ሰጥተዋል።

ስለዝግጅታቸው
የመጨረሻ ልምምዳችንን ዛሬ ሰርተናል። በዓርቡ ጨዋታ ያልተጫወቱ ሁለት ልጆች (ብርሃኑ እና ቸርነት) አሉን። ትናንትና እና ዛሬ ልምምድ ጀምረዋል። የእነሱን ሁኔታ በመጨረሻ ከዶክተሮች ውሳኔ እንሰማና ለነገው ጨዋታ እንዘጋጃለን። እንደሚታወቀው የነገው ጨዋታ ወሳኝ ጨዋታ ነው ለእኛ ፤ ለእነሱም ወሳኝ ጨዋታ ነው። የምንችለውን ሁላ አድርገን ውጤት ይዘን ለመውጣት ተዘጋጅተናል።
ስለነገው የጨዋታ አቀራረብ
የማሸነፍ ጨዋታ ስለሆነ ተከላክለን የምንጫወትበት አይደለም። እነሱም ከእኛ የሚፈልጉት ሦስት ነጥብ ነው ፤ እኛም ሦስት ነጥብ ነው። ህዝባችን ፊት ነው የምንጫወተው በየትኛውም መንገድ ማሸነፉ ለእኛ በጣም ይጠቅመናል። ስለዚህ የመከላከል ጨዋታ አይደለም የምንጫወተው ፤ ለማሸነፍ ነው የምንጫወተው።
ወደአፍሪካ ዋንጫ ስለማለፍ ዕድል
እኛ ለራሳችን የራሳችንን እድል መክፈት አለብን። በሌሎች ጥገኛ መሆን አንችልም። በምንችለው ሁሉ ህዝባችን ፊት ዘጠና ደቂቃ ተጫውተን አሸንፈን የራሳችንንም እድል ለማመቻቸት ነው የምንሞክረው።
ስለጫና
ጫና የለብንም ብንል ውሸት ይሆናል። ኃላፊነትም አለመቀበል ይሆናል። ከጫናው ይልቅ ግን የምናስበው እኛ በተቻለ መጠን አሸንፈን እንዴት አድርገን ነው ህዝባችንን የምናስደስተው ነው። ጫናውማ የግድ ነው። ከጫና የኢትዮጵያን ህዝብ የምናስደስትበት መንገድ የምናስበው። ክብሩን ነው ከፍ የምናደርገው እንጂ ጫና አለ።
ቡድናቸውን ቆሞ ስለመምራት ጉዳይ
በሴኔጋሉ ጨዋታ የነበሩን ተጫዋቾች በብዛት 9 እና 10 አመት በብሔራዊ ቡድን የተጫወቱ ናቸው። ስለዚህ ለእነዚህ ልጂች ሜዳ ላይ ብዙ የምትነግረው ነገር የለም። ለምን? በአስር አመት ካላወቁት በአንድ ጨዋታ ሊያውቁት አይችልም። ስለዚህ ልምዱ አላቸው ፤ ተነጋግረናል መተግበር ነው። በተጨማሪም በ48 ሺ ህዝብ መሀል ምኑንስ ነው የምትለው? ላይሰማም ይችላል። አሁን ደግሞ በብዛት አዲስ ልጆች ነው ያሉን። ባለፈው አምስት እና ስድስት ልጆች ነው የነበሩት። እነሱን መምራት አለብን። ምክንያቱም የእነሱን ትንሽ የእኛን ትንሽ አንድ ላይ አድርገን ነው የምናጫውተው። ጊዜው ስለሌለ እርዳታ ያስፈልጋል ፤ መምራት ያስፈልጋል። የአቋም መለኪያ ጨዋታዎች ስላላደረግን ልጆቹን አናውቃቸውም። የምናውቃቸው ሜዳው ላይ ነው። ሜዳው ላይ ስህተት ከመሰራቱ በፊት አንዳንድ ነገሮችን ብንረዳቸው ያ ይጠቅማል። እያንዳንዱ ጨዋታ የራሱ ሂደት አለው። ተጫዋቾችህ፣ የምትጫወትበት ቦታ ውጤቱ…። አሁንም ቢሆን ምክትሎቹ ሊነሱ ይችላሉ እኔ አንዳንድ ጊዜ ልቀመጥ እችላለው ፤ እነሱ ተቀምጠው እኔም ልመራ እችላለው። ስለዚህ የጨዋታው እና የተጫዋቾቹ ሁኔታ ይወስነዋል።

