ዋልያዎቹን የረቱት የሞዛምቢክ አሠልጣኝ ከጨዋታው በኋላ ምን አሉ !

ዋልያዎቹን የረቱት የሞዛምቢክ አሠልጣኝ ከጨዋታው በኋላ ምን አሉ !

👉 “ከሜዳ ውጪ ከማሸነፍ በሜዳ ማሸነፍ የተሻለ ይቀል ነበር”

👉 “እዚህ ማሸነፍ ግዴታ ነበር ፤ ምክንያቱም በሞዛምቢክ እና በኢትዮጵያ መካከል ያለውን የነጥብ ልዩነት ማስፋት ነበረብን”

👉 “…ኢትዮጵያ ሱዳንን ካሸነፈች ሞዛምቢክ በቀላሉ ወደ አፍሪካ ዋንጫው…”

👉 “ይሄ ድል በዓርቡ ሽንፈት ለተበሳጩ የሞዛምቢክ ደጋፊዎች እንዲሆንልን እፈልጋለው”

የ2027 የአፍሪካ ዋንጫ የማጣሪያ የምድብ አራተኛ ጨዋታ ዛሬ በባህር ዳር ስታዲየም ተከናውኖ እንግዳው ቡድን ሞዛምቢክ ኢትዮጵያን አንድ ለዜሮ በሆነ ውጤት አሸንፏል። ከጨዋታው በኋላም የሞዛምቢክ ብሔራዊ ቡድን አሠልጣኝ ቺሊኒሆ ኩንዴ በስፍራው ለተገኙ የመገናኛ ብዙሀን አባላት የድህረ ጨዋታ ጋዜጣዊ መግለጫ ሰጥተዋል።

ስለ ጨዋታው

ጨዋታው ለሁለቱም ቡድኖች ጥሩ ነበር። ከአየር ሁኔታው ጋር በተያያዘ ተጫዋቾችን ላይ ተፅዕኖው ትንሽ ከበድ ይል ነበር። ነገር ግን ተጫዋቾቼ ባሳዩት ነገር እንኳን ደስ አላችሁ ማለት እፈልጋለው። በመጀመሪያው አጋማሽ አንድ እና ሁለት ግቦችን ማስቆጠር ነበረብን። በሁለተኛው አጋማሽ ወደ ራሳችን የግብ ክልል አፈግፍገን የተጋጣሚ ቡድንን ስህተት ተጠቅሞ በመልሶ ማጥቃት ለመጫወት ነበር የሞከርነው። በዚሁ አጋጣሚ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ተጫዋቾችን ማድነቅ እፈልጋለው። እስከመጨረሻው ደቂቃ ድረስ ለማሸነፍ የነበራቸው ተጋድሎ የሚደነቅ ነበር።

ስለ ድሉ

ድሉ ደስ ይላል። ሁሌ ማሸነፍ ደስ ይላል ፤ ግን ዓርብ በሜዳችን ሳይጠበቅ ተሸንፈን ነበር። ቡድኑ ግን ለዚህ ምላሽ መስጠት እንደሚችል አምኖ ነበር። ከሽንፈቱ በኋላ ስለዓርቡ ሽንፈት በሚዲያዎች መነጋገሪያ ሆነን ነበር። ሽንፈቱም ከቡድኑ ወደ አሠልጣኙ የዞረ ነበር።

ከአየር ሁኔታው ጋር በተያያዘ ጨዋታው ላይ ትንሽ ከብዶናል። ከዚህ በተጨማሪም የተወሰኑ ልምድ ያላቸውን ከወጣቶቹ ጋር አቀላቅለን ነበር የተጫወትነው። ከሜዳ ውጪ ከማሸነፍ በሜዳ ማሸነፍ የተሻለ ይቀል ነበር። በአጠቃላይ ይሄ ድል በዓርቡ ሽንፈት ለተበሳጩ የሞዛምቢክ ደጋፊዎች እንዲሆንልን እፈልጋለው።

ወደ አፍሪካ ዋንጫው ለማለፍ በምድቡ ስላለው ዕድል

እዚህ ማሸነፍ ግዴታ ነበር። ምክንያቱም በሞዛምቢክ እና በኢትዮጵያ መካከል ያለውን የነጥብ ልዩነት ማስፋት ነበረብን። በቀጣይ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን የሱዳን ብሔራዊ ቡድንን እንደምታሸንፍ አስባለው። ምክንያቱም ኢትዮጵያ ሱዳንን ካሸነፈች ሞዛምቢክ በቀላሉ ወደ አፍሪካ ዋንጫው ስለምታልፍ። በአጠቃላይ በማሸነፋችን ደስተኛ ብንሆንም አሁንም ወደ አፍሪካ ዋንጫው ለማለፍ የሚቀሩን የቤት ስራዎች አሉ።

ስለ ኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ጠንካራ እና ደካማ ጎን

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ጠንካራ ተጫዋቾች አሉት። ቀጥተኛ አጨዋወትም የሚጫወት ነው። ስለድክመቱ ግን ከክብር ጋር አሁን ምንም ማለት አልችልም። ነገር ግን እያደገ ሊመጣ የሚችል ቡድን እንደሆነ አስባለሁ።