👉 “ውድድሩ እስካላለቀ ድረስ ከውድድሩ ወጥተናል ማለት አንችልም”
👉 “ጨዋታውንም እንደ ጥሎ ማለፍ ውድድር ነው የተመለከትነው”
👉 “ማን ማለፍ አለበት ወይም መውደቅ አለበት ይለያል ብዬ የምገምተው የሚቀጥለው ጨዋታ ላይ ነው”
👉 “ጫና ምንጊዜም ቢሆን አለ”
ታንዛኒያ፣ ኬኒያ እና ዩጋንዳ በሚያስተናግዱት የ2027 የአፍሪካ ዋንጫ ለማለፍ የምድብ ማጣሪያ ጨዋታዎች እየተደረጉ እንደሚገኙ ይታወቃል። የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድንም በምድቡ አራተኛ ጨዋታዋን ዛሬ አድርጋ 1ለ0 በሆነ ውጤት በሜዳዋ በሞዛምቢክ ተሸንፋለች። የብሔራዊ ቡድኑ አሠልጣኝ ዩሐንስ ሳህሌም ከጨዋታው በኋላ ከጋዜጠኞች ጋር ያደረጉትን የድህረ ጨዋታ አስተያየት እንደሚከተለው ይዘን መጥተናል።
ስለጨዋታው
ከእረፍት በፊት ትንሽ እነሱ በኳስ ቁጥጥር በልጠውን ነበር። እኛም ጫና ለማድረግ ሞክረናል ፤ ነገር ግን በተፈጠረ አንድ ስህተት ግብ ተቆጥሮብናል ፤ ያገኙትን ዕድል ተጠቅመዋል። ከእረፍት በኋላ እኛም አጨዋወታችንን በመቀየር ሙሉ በሙሉ ጫና ፈጥረን ለመጫወት ሞክረናል። አንዳንድ የግብ ማስቆጠር እድሎችንም አግኝተን ነበር፤ እርሱንም አልተጠቀምንበትም። እንግዲህ ጨዋታው በእነሱ አንድ ለዜሮ አሸናፊነት አልቋል።
በውድድሩ ስላላቸው ተስፋ
ውድድሩ አላለቀም ፤ አሁን በሶስተኛ ደረጃ ላይ ነን ፤ ሁለት ጨዋታዎችም ይቀሩናል። ውድድሩ እስካላለቀ ድረስ ከውድድሩ ወጥተናል ማለት አንችልም ፤ ምክንያቱም ዕድሎች አሉን። ዛሬ ብናሸንፍ ግን የተሻለ እድል ይኖረን ነበር። ሁለት የቀሩ ጨዋታዎች አሉ ፤ እያንዳንዱን ጨዋታ እንደ ጨዋታው መመልከት ነው። ከውድድሩ ልንወጣ እንችላለን የምንለው በቀጣዩ ጨዋታ ነው። እኛም ማሸነፍ አለብን ፤ የሌላውንም ማየት አለብን። መጀመሪያ ግን እኛ ማሸነፍ አለብን። ካላሸነፍን ግን ሁሉ ነገር ያልቃል።
ውድድሩ አላለቀም ፤ ነገር ግን ከነበረን ዕድል ያነሰ ዕድል ነው ያለን። ዛሬ ብናሸንፍ ኖሮ ከፍ ያለ ዕድል ይኖረን ነበር። አሁንም ውድድሩ አላለቀም። በእኔ ግምት ማን ማለፍ አለበት ወይም መውደቅ አለበት ይለያል ብዬ የምገምተው የሚቀጥለው ጨዋታ ላይ ነው።
ጨዋታውን ለማሸነፍ ስለነበራቸው አቀራረብ
እንዳያችሁት በተለይ ሁለተኛው አጋማሽ ላይ በተቻለ መጠን በእነሱ ሜዳ ላይ ነው የተጫወትነው። ዕድሎችም አግኝተናል አልጨረስናቸውም እንጂ። ማንም እንዳየው እነሱ ተከላክለው ነው የተጫወቱት። ኳስ በማውጣት አንድ ሁለቴ በመልሶ ማጥቃት በመውጣት ለመጫወት ሞክረዋል። ከዛ ውጪ ግን ተጫዋቾቻችን የሚችሉትን ሁላ ለማጥቃት ሞክረዋል። በሁለተኛው አጋማሽ እኛ የበላይነት ነበረን ፤ መጨረሱ ላይ ነው እንጂ።

በጨዋታው ስላደረጉዋቸው የተጫዋች ለውጦች
በግራና በቀኝ በኩል ብዙ ክሮሶችን አድርገን ነበር ፤ ነገር ግን አልተሳካልንም። ስላልተሳካ የመሐል ሜዳ ተጫዋቾችን አስገብተን የሚገኙ ሁለተኛ ኳሶችን ወደ ጎል መሞከር የሚችሉ በረከት እና ወገኔን ነው ያስገባነው። ምክንያቱም በክሮሶቹ ላይ ተጋጣሚያችን በአየር ላይ በበላይነት እየበለጡን ስለነበር።
ስለተጫዋቾቹ ስሜት እና ሞራል
የተጫዋቾቹን ውስጣዊ ስሜት በትክክል ማወቅ አልችልም ፤ ነገር ግን መቶ በመቶ ልናረጋግጥ የምንችለው አንድ ነገር አለ። ለማሸነፍ የሚጠበቅብንን ሁሉ ለማድረግ ተነጋግረን ነበር። ጨዋታውንም እንደ ጥሎ ማለፍ ውድድር ነው የተመለከትነው። ከዚያ ውጪ እያንዳንዱ ተጫዋች በውስጡ ያለውን ስሜት እኔ ማወቅ አልችልም።
ማፑቶ ላይ ስለተመዘገበው ድል እና ስለዛሬው ሽንፈት
ማፑቶ በነበርንበት ሰዓት ያለን 100% አሸንፎ መውጣት የሚለው ብቻ ነው። ምንም አማራጭ የሌለው ነው። ዛሬ እንግዲህ ስንጫወት አቻ ብንወጣም ሊሆን ይችል ነበር። አሁን ከተሸነፍን በኋላ አሁንም አልወጣንም የሚለው አለ። ማፑቶ ባናሸንፍ ኖሮ ምንም ማውራት አንችልም ነበር። ጨርሰን ነበር።
በዛሬው ጨዋታ ቡድኑ ላይ ስለነበረ የማሸነፍ ጫና
ጫና ምንጊዜም ቢሆን አለ። ነገር ግን ከጫናው በላይ አሸንፈህ የምታገኘው ክብር ከፍተኛ ስለሆነ ትኩረቱ ማሸነፉ ላይ ነው እንጂ ልጆቹ ላይ ብንሸነፍ የሚል ነገር አላየሁም።
በመጨረሻ ጨዋታው ከተጠናቀቀ በኋላ በጋቶች ፓኖም እና ከነዓን ማርክነህ እንዲሁም በደጋፊዎች መካከል የተፈጠረውን ሁነት በተመለከተ ተጠይቀው አሠልጣኙ ስለጉዳዩ ምንም እንደማያውቁ መልሰዋል።

