አብዱልከሪም ወርቁ ዳግም በተመለሰበት ቤቱ በ45 ያክል ደቂቃዎች የሜዳ ላይ ቆይታው ለቡድኑ ወሳኝ ጥያቄ መልስ ሆኖ ብቅ ብሏል።

ኢትዮጵያ ቡና በአዲሱ የውድድር ዘመን በአሰልጣኝ ገብረመድህን ኃይሌ እየተመራ የትኛውም እንደ አዲስ እየተገነባ ያለ ቡድን እንደሚገጥመው አጀማመሩ በተጠበቀው ልክ አልሆነም ፤ በተለይ ቡድኑ በመከላከሉ ወቅት የሚስተዋሉ ተደጋጋሚ ግለሰባዊ ስህተቶች እንዲሁም በማጥቃቱ ደግሞ ዕድሎችን በብዛትና በጥራት ከመፍጠር ጋር ተያይዞ ቡድኑ በሚጠበቀው ደረጃ ላይ አለመድረሱን የመጀመሪያዎቹ አምሰት ጨዋታዎች ቁልጭ አድርገው ያሳዩት እውነታ ነበር።
በመከላከሉ ከጨዋታ ጨዋታ ቡድኑ የሚታዩ የመሻሻል ምልክቶችን ቢያሳይም በማጥቃቱ ረገድ ግን አመርቂ መሻሻል አልነበረም ፤ ሊጉ ለብሔራዊ ቡድኖች ውድድር ከመቋረጡ አስቀድሞ ኢትዮጵያ ቡና ባደረጋቸው አምስት የሊግ ጨዋታዎች (450 ደቂቃዎች) ያስቆጠረው የግብ መጠን ሁለት ብቻ ነበር ፤ ከግቦቹ መጠን ማነስ ባሻገር አንደኛዋ ግብ ከቆመ ኳስ የተገኘች ከመሆኗ ጋር ተዳምሮ ቡድን በክፍት ጨዋታ የሚፈጥራቸው ዕድሎች ደካማ ስለመሆናቸው አይነተኛ ማሳያ ነበሩ።
በመጀመሪያዎቹ አምስት የሊግ ጨዋታዎች ቡድኑ በጥቅሉ በ450 ደቂቃዎች 9 ኢላማቸውን የጠበቁ ሙከራዎችን ሲያደርግ ይህም በአማካይ በጨዋታ 1.8 ሙከራዎች እንደ ማለት ነው ይህ ቁጥር ከሙከራዎች ጥራት ጋር አጣምረን ከተመለከትን አንድ ለዋንጫ መጫወት ከሚፈልግ ቡድን የሚጠበቅ አልነበረም።
ሊጉ ለቀናት ለዕረፍት ሲቋረጥ ብዙሃኑ የቡና ደጋፊ ቡድኑ ዳግም ወደ ውድድር ሲመለስ ቡድኑ በሁለተንተናዊ መንገድ ተሻሽሎ እንዲመጣ ፍላጎት የነበረው ሲሆን በተለይ በፈጠራ ረገድ ያለበትን ክፍተት ቀርፎ እንዲመጣ መሻት ነበረው ፤ በዚህ መሀል ነበር ታድያ በክረምቱ መቻልና ኢትዮጵያ ቡናን ሲያነታርኩ ከቆዩት ዓለምብርሃን ይግዛውና አብዱልከሪም ወርቁ ሁለተኛው ለኢትዮጵያ ቡና እንዲጫወት በክለቦቹ መካከል በተደረገ መግባባት የተወሰነው።
በመጀመሪያዎቹ አምስት ጨዋታዎች በዲቫይን ዋኩቹኩዋ እንዲሁም በክረምቱ የዝውውር መስኮት ክለቡን በተቀላቀለው ጁኒዮር ምቤሌ ማቩንጉ እግሮች የጠበቀውን ያክል ግልጋሎት ላላገኘው ኢትዮጵያ ቡና ይህ ዜና ታላቅ ብስራት ነበር እርግጥ ጁኒዮር ምቤሌ አሰልጣኝ ገብረመድህን ኃይሌ ከወድድሩ ጅማሮ አስቀድሞ ከክለቡ ሬዲዮ ጋር በነበራቸው ቆይታ “የአስማተኛ ግራ እግር” ባለቤት ብለው ቢገልፁትም ከጨዋታ ዝግጁነት አንፃር የተወሰነ ጊዜ እንደሚፈልግ ተናግረው እንደነበር ልብ ይሏል።
አቡዱልከሪም ወርቁ በኢትዮጵያ ቡና መለያ ባደረገው የመጀመሪያ ጨዋታ ቡድኑ ወላይታ ድቻን ሲገጥም በሁለተኛ አጋማሽ ተቀይሮ በመግባት ሲያደርግ ተጫዋቹን ሲያመጡ ከአብዱልከሪም የጠበቁትን ነገር ለማግኘት ደቂቃ አልፈጀባቸውም። ከ12 ደቂቃዎች የሜዳ ላይ ቆይታ በኃላ አብዱልከሪም የግል ጥረቱን ተጠቅሞ ቡድኑን ቀዳሚ ያደረገች ግብ አመቻችቶ ሲያቀብል 45 ያክል ደቂቃዎች በዘለቀው የሜዳ ላይ ቆይታው ቡድኑ በጥቅል ባደረጋቸው አምስት ሙከራዎች ላይ በቀጥታም ይሁን በተዘዋዋሪ ተሳትፎ በማድረግ ድንቅ የሚባል እንቅስቃሴን እንዲሁ ማሳየት ችሏል።
ስለ ኢትዮጵያ ቡና ማጥቃት መሻሻል ለማውራት ጊዜው ገና ቢሆንም በወላይታ ድቻው ጨዋታ ግን ተስፋን ተመልክተናል በአብዱልከሪም ተቀይሮ መግባት የተነቃቃውን ማጥቃት ይበልጥ መዋቅራዊ ማድረግ የአሰልጣኝ ገብረመድህን ቀጣይ የቤት ስራ ነው።
እርግጥ አብዱልከሪም ወርቁ ኢትዮጵያ ቡናን ጠንቅቆ እንደማወቁ በቀጣይ የቡድኑ የውድድር ዘመኑ ጉዞ ላይ ከፍተኛ በጎ ተፅዕኖ እንደሚፈጥር የሚጠበቅ ሲሆን ተጫዋቹ ቡና አሁን ካሉት የአማካይ ስፍራ ተሰላፊ አማራጮች በተሻለ በፓሶች ብቻ ጨዋታን ከመወሰን ባሻገር በግሩም እንቅስቃሴ (Mobility) እንደመጫወቱ በቡና እንቅስቃሴ ውስጥ የማቀበያ አማራጮችን በመፍጠር ፣ በመስመሮች መካከል በመገኘት አለፍ ሲልም ወደ ሳጥን በመድረስ ማጥቃቱን እንደሚያሳድግ ይጠበቃል።

