ፕሪሚየር ሊግ ትኩረት 22 | እንደሚቻል ያሳየው ኦቢኤን

ፕሪሚየር ሊግ ትኩረት 22 | እንደሚቻል ያሳየው ኦቢኤን

በስድስተኛ ሳምንት የሲቢኢ የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ዘጠኙንም ጨዋታዎች ከአራት ከተሞች በቀጥታ ስርጭት ሽፋን የሰጠው ኦቢኤን የጨዋታ ሳምንቱ የሶከር ኢትዮጵያ የትኩረት ማዕከል ሆኗል።

​የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ በረጅም ዓመት ታሪኩ ውስጥ በርካታ ውጣ ውረዶችንና የለውጥ ሂደቶችን አልፏል። በተለይም ከቴሌቪዥን ስርጭት አንፃር ሊጉ ለዓመታት ሲታማበት የነበረው የተደራሽነት ውስንነት ቀደም ባሉት ጊዜያት በዲኤስ ቲቪ የነበረው የስርጭት ቆይታ ካለፈ በኋላ በኦሮሚያ ብሮድካስቲንግ ኔትወርክ (ኦቢኤን) አማካኝነት አዲስ እና ተስፋ ሰጪ ምዕራፍ ከፍቷል። ከ2018 ጀምሮ የሊጉን የቀጥታ ስርጭት መብት ይዞ እየሰራ የሚገኘው ኦቢኤን ዘንድሮ በሲቢኢ የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ የ6ኛ ሳምንት መርሐ-ግብር የሊጉን ሁሉንም ጨዋታዎች ከአራት የተለያዩ ከተሞች በቀጥታ ስርጭት ለተመልካች ማድረስ መቻሉ በዘርፉ ለሀገራችን እግርኳስ ታሪካዊ ስኬት እና የለውጥ አመላካች ተደርጎ የሚወሰድ ትልቅ እርምጃ በመሆኑ የጨዋታ ሳምንቱ የትኩረታችን ማዕከል አድርገነዋል።

​ከዚህ ቀደም በነበሩት የውድድር ዓመታት የሊጉ ጨዋታዎች በቀጥታ የሚተላለፉት በውስን ቁጥር ወይም በአንድ ከተማ ብቻ ተገድበው ነበር። ይህ ሁኔታ በርካታ ክለቦችንና ደጋፊዎቻቸውን ከቴሌቪዥን መስኮት ያራቀ ከመሆኑም በላይ የሊጉን ተወዳዳሪነት በአንድ ማዕከል ብቻ የተገደበ እንዲመስል አድርጎት ቆይቷል። ሆኖም የሊጉ የውድድር ቅርፅ ዘንድሮ በመጠኑ ከተቀየረ በኋላ ኦቢኤን በአንድ ሳምንት ውስጥ በአራት የተለያዩ ከተሞች የተደረጉትን ሁሉንም ጨዋታዎች በቀጥታ ማስተላለፍ መቻሉ በክለቦችና በደጋፊዎች መካከል የነበረውን የፍትሐዊነት ጥያቄ የመለሰ ታላቅ ስራ ነው። ዛሬ በየትኛውም የሀገሪቱ ጥግ የሚገኝ የእግርኳስ አፍቃሪ የሚወደውን ክለብ ጨዋታ በቀጥታ የመከታተል እድል በማግኘቱ ለሊጉ ያለው ፍቅርና ባለቤትነት ስሜት ይበልጥ እንዲጎለብት አድርጓል።

​ይህ የተደራሽነት መስፋት ከስፖርታዊ ፋይዳው ባለፈ ለሊጉ ኢኮኖሚያዊና የገበያ እድገት ያለው ሚና እጅግ ከፍተኛ ነው። በዘመናዊው እግርኳስ የቴሌቪዥን ስርጭት የክለቦችና የሊጎች ዋነኛ የገቢ ምንጭና የንግድ መሳቢያ ድልድይ ነው። ይህ ዕድል በሀገራችን ገና በተሟላ መልኩ ባይሳካም የኦቢኤን ጅምር በዚሁ ከቀጠለ የሀገራችንንም ክለቦች ከዚህ ዘመናዊ አካሄድ ተጠቃሚ እንደሚያደርጋቸው መናገር ይቻላል። በዚህም ሁሉም ጨዋታዎች በቀጥታ በተላለፉ ቁጥር የክለቦች ማልያዎች፣ በሜዳ ዙሪያ የሚቀመጡ ማስታወቂያዎች እና የስፖንሰሮች አርማዎች በሚሊዮኖች በሚቆጠሩ ተመልካቾች ፊት የመታየት እድላቸው ይሰፋል። ይህ ደግሞ ትላልቅ የንግድ ተቋማት በኢትዮጵያ እግርኳስ ላይ ኢንቨስት እንዲያደርጉና ክለቦችም ራሳቸውን በገንዘብ የሚደጉሙበት የስፖንሰርሺፕ ዕድል እንዲያገኙ ቀጥተኛ ግፊት ይፈጥራል።

​በሌላ በኩል ሁሉም ጨዋታዎች በካሜራ እይታ ውስጥ መግባታቸው በሜዳ ላይ ለሚታየው የውድድር ጥራት እና ፍትሐዊ ዳኝነት ትልቅ ዋስትና ይሰጣል። ከዚህ ቀደም በቴሌቪዥን የማይተላለፉ ጨዋታዎች ላይ በዳኝነት ውሳኔዎች ዙሪያ የሚነሱ ቅሬታዎች እና ከስፖርታዊ ጨዋነት ውጭ የሆኑ ድርጊቶች በስፋት ይስተዋሉ ነበር። አሁን ግን እያንዳንዱ እንቅስቃሴ በሚሊዮኖች ዐይን ስር መሆኑ ዳኞች ከፍተኛ ጥንቃቄ እንዲሁም ኃላፊነት እንዲሰማቸው የሚያደርግ ሲሆን ተጫዋቾችም ብቃታቸውን ለሀገር ውስጥ ብቻ ሳይሆን ለውጭ ሀገር መልማዮች (Scouts) ጭምር የሚያሳዩበትን ወርቃማ ዕድል ፈጥሮላቸዋል።

​ከሚዲያ አቅምና ከቴክኖሎጂ አጠቃቀም አንፃር ስንመለከተውም ኦቢኤን ያሳየው አፈፃፀም እጅግ የሚያስመሰግንና በቀላሉ የሚታይ አይደለም። በአንድ የጨዋታ ሳምንት በአራት የተለያዩ ከተሞች የቀጥታ ስርጭት መሳሪያዎችን፣ ካሜራዎችን፣ ባለሙያዎችንና የስርጭት ግንኙነቶችን አቀናጅቶ ያለመቆራረጥ ስርጭት ማድረግ ከፍተኛ የሎጂስቲክስ፣ የወጪ እና የቴክኒክ ብቃትን ይጠይቃል። ኦቢኤን ይህንን ከባድ ፈተና በብቃት በማለፍ የሀገር ውስጥ የስፖርት ሚዲያዎች በቂ ቁርጠኝነትና አቅም ካላቸው በዓለም አቀፍ ደረጃ የሚታዩ የስፖርት ስርጭት ደረጃዎችን መተግበር እንደሚችሉ በተግባር ያረጋገጠ ድንቅ አርአያ ሆኗል።

​በአጠቃላይ ኦቢኤን በ6ኛው ሳምንት የሲቢኢ የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ መርሐ-ግብር ያሳየው ይህ አስደናቂ ተግባር ለሀገራችን ስፖርት “ይቻላል” የሚል ትልቅ መልዕክት ያስተላለፈና ተቋሙን በእጅጉ የሚያስመሰግን ገድል ነው። ይህ ድንቅ ጅማሮ በአንድ ሳምንት ስኬት ብቻ ተገድቦ ሳይቀር በቀጣይ ሳምንታትም ተጠናክሮ መቀጠል ይኖርበታል። በተለይም የምስል ጥራቱን ይበልጥ በማሳደግ፣ የካሜራ አንግሎችን በማብዛትና የጨዋታ ትንታኔዎችን በማጠናከር ረገድ ቀጣይነት ያለው መሻሻል ከታከለበት ኦቢኤን የጀመረው ይህ መልካም ስራ የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግን ወደ ተሻለ ከፍታ እንደሚወስደው ያለመጠራጠር መናገር ይቻላል።