በአብዩ አረጋሽ
ዛሬ በተደረጉ የሲቢኢ ኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ የ6ኛ ሳምንት ጨዋታዎች ሸገር ከተማ፣ ኢትዮጵያ ቡና፣ ባህርዳር ከተማ እና ሲዳማ ቡና ባለ ድል ሆነዋል።

ሸገር ከተማ ከ ሀዋሳ ከተማ
በአዳማ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲ በተደረገው የ9፡00 ጨዋታ ሸገር ከተማ ሀዋሳ ከተማን 2-1 በማሸነፍ የውድድር ዘመኑን ሁለተኛ ድል አስመዝግቧል።
የመጀመሪያው አጋማሽ ሁለቱም ቡድኖች ጥሩ እንቅስቃሴ ያደረጉበት ቢሆንም ሁለቱም በተመሳሳይ ለግብ የቀረበ ሙከራ ሳያደርጉ አጋማሹ 0 – 0 ተጠናቋል። ከዕረፍት መልስ በ54ኛው ደቂቃ ካሌብ በየነ ከግራ መስመር ያሻገረውን ኳስ ኦዳ መሐመድ ወደ ግብነት በመቀየር ሸገርን መሪ አድርጓል። ከሦስት ደቂቃዎች በኋላም በ57ኛው ደቂቃ ቢንያም ፍቅሩ በሁለት የሀዋሳ ተከላካዮች መካከል አልፎ ባስቆጠረው ግብ የሸገርን መሪነት ወደ 2 ለ 0 አሳድጓል።

በ86ኛው ደቂቃ ተቀይሮ የገባው ጌታነህ ከበደ ለሀዋሳ ከተማ ግብ በማስቆጠር ውጤቱን 2-1 አድርጓል። ከግቡ በኋላ ሀዋሳ ከተማ ጫና ፈጥሮ ቢጫወትም አቻ የሚያደርግ ግብ ማስቆጠር አልቻለም። በጨዋታውም ሸገር ከተማ ያገኘውን የፍጹም ቅጣት ምት ቡልቻ ሹራ ሳይጠቀም ቀርቷል።
ኢትዮጵያ ቡና ከ ወላይታ ድቻ
በአዲስ አበባ ስታዲየም 9፡30 በጀመረው ጨዋታ ኢትዮጵያ ቡና ወላይታ ድቻን 2-1 በማሸነፍ ሦስት ነጥብ ወስዷል።
በመጀመሪያው አጋማሽ ወላይታ ድቻ በኩል መሳይ ሰለሞን ከግብ ጠባቂው ጋር ተገናኝቶ የመታው ኳስ የግቡን አግዳሚ በመምታት የተመለሰበት አጋጣሚ የሚጠቀስ ነበር። ኢትዮጵያ ቡና በኳስ ቁጥጥር የተሻለ ቢሆንም አደገኛ የግብ ሙከራ ሳያደርግ አጋማሹ ያለ ግብ ተጠናቋል።

በ58ኛው ደቂቃ ታይባ ምቦኑዩምዋኒ ከቀኝ መስመር በኩል አብዱልከሪም ወርቁ ያቀበለውን ኳስ ወደ ግብነት በመቀየር ቡናን መሪ አድርጓል። በ66ኛው ደቂቃ ደግሞ ታይባ ለዘላለም አባተ ለማቀበል የሞከረውን ኳስ ዩቪ ዮሴፍ በጉልበቱ ነክቶ በራሱ ግብ መረብ ላይ በማስቆጠር የቡናን መሪነት ወደ 2 ለ 0 ከፍ አድርጓል።
ወላይታ ድቻ በ68ኛው ደቂቃ ከማዕዘን ምት የተገኘውን ኳስ ኪሩቤል አበበ በግራ እግሩ ወደ ግብነት በመቀየር ውጤቱን 2-1 አድርጓል። በ90ኛው ደቂቃም ኪሩቤል አበበ ከሳጥን ውጭ በቮሊ ያደረገው ጠንካራ ሙከራ ግብ ጠባቂው አቡበከር ኑራ በግሩም ብቃት አድኖበታል። ጨዋታውም በኢትዮጵያ ቡና 2 ለ 1 አሸናፊነት ተጠናቋል።
ባህርዳር ከተማ ከ ኢትዮጵያ መድን
በባህርዳር አለምአቀፍ ስታዲየም 10፡00 የተደረገውን ጨዋታ ባህርዳር ከተማ ኢትዮጵያ መድንን 3 ለ 1 በማሸነፍ በዕለቱ ከተከናወኑ ጨዋታዎች በርካታ የጎል ብልጫ በመያዝ ጭምር ድል አስመዝግቧል።
ባህርዳር ከተማ በ10ኛው ደቂቃ ዮዳሄ ዳዊት ከቆመ ኳስ ከርቀት ባስቆጠረው ግብ መሪነቱን ወስዷል። በ39ኛው ደቂቃ ደግሞ ግብ ጠባቂው ሬችሞንድ አይ በኪቲካ ጁማ ላይ በሰራው ጥፋት የተገኘውን የፍጹም ቅጣት ምት አንተነህ ተፈራ ወደ ግብነት በመቀየር የቡድኑን መሪነት ወደ 2 ለ 0 ከፍ አድርጓል።

ከዕረፍት መልስ በ68ኛው ደቂቃ ግብ ጠባቂው ፔፔ ሰይዱ በአሸናፊ ሐፍቱ ላይ በሰራው ጥፋት የተገኘውን የፍጹም ቅጣት ምት ወገኔ ገዘኸኝ በማስቆጠር ኢትዮጵያ መድንን ወደ ጨዋታው መመለስ ችሏል።
ጨዋታው ወደ መጠናቀቂያው በደረሰበት 90+4 ደቂቃ ላይ ተቀይሮ የገባው ደሳለኝ አሻግሬ አንተነህ ተፈራ ከቆመ ኳስ ያቀበለውን ኳስ ወደ ግብነት በመቀየር የባህርዳርን ድል አረጋግጧል።
ሲዳማ ቡና ከ አዳማ ከተማ
በአዳማ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲ ስታድየም ምሽት 12፡00 የተጅመረው ጨዋታ ሲዳማ ቡና አዳማ ከተማን 2 ለ 1 በማሸነፍ የውድድር ዘመኑን የመጀመሪያ ድል አስመዝግቧል።
በሁለቱም ቡድኖች በኩል ጥሩ ፉክክር በተደረገበት የመጀመሪያው አጋማሽ አዳማ ከተማ በእንቅስቃሴ ረገድ የተሻለ ቢሆንም አደገኛ የግብ ሙከራ ማድረግ አልቻለም። ሲዳማ ቡናም ኢላማውን የጠበቀ ሙከራ ሳያደርግ አጋማሹ 0 ለ 0 ተጠናቋል።

ከዕረፍት መልስም አዳማ ከተማ የተሻለ እንቅስቃሴ እያደረገ በነበረበት ወቅት በ78ኛው ደቂቃ መስፍን ታፈሰ ለሲዳማ ቡና ግብ በማስቆጠር ቡድኑን መሪ አድርጓል። ይህች ግብ ለሲዳማ ቡና በውድድር ዘመኑ የመጀመሪያ ግብ ሆናም ተመዝግባለች።
በ88ኛው ደቂቃ ላይ እዮብ ማትያስ ከማዕዘን ምት የተገኘውን ኳስ በግንባሩ ወደ ግብነት በመቀየር አዳማ ከተማን አቻ ማድረግ ችሏል። ሆኖም በ90+5ኛው ደቂቃ አቤል ያለው ግብ ጠባቂው አላዛር የመለሰውን ኳስ ተጠቅሞ ወደ ግብነት በመቀየር ሲዳማ ቡናን ባለ ድል አድርጓል። በዚህም ሲዳማ ቡናዎች በመጨረሻ ደቂቃ ባስቆጠሩት ግብ የውድድር ዘመኑን የመጀመሪያ ድል አስመዝግበዋል።

