ከብሔራዊ ቡድኖች ዓለም አቀፍ ጨዋታዎች በኋላ የሲቢኢ የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ በ6ኛ ሳምንት ሁለት ጨዋታዎች ወደ ውድድር ተመልሷል። በተደረጉት ጨዋታዎችም ቅዱስ ጊዮርጊስ ሙሉ ሦስት ነጥብ ሲያገኝ፣ ወልዋሎ ዓዲግራትና መቻል ነጥብ ተጋርተዋል።
በዐቢዩ አረጋሽ

ቅዱስ ጊዮርጊስ 2-0 ሀዲያ ሆሳዕና
በአዲስ አበባ ስታዲየም ቀን 9:30 ላይ ቅዱስ ጊዮርጊስን ከሀዲያ ሆሳዕና ያገናኘው ጨዋታ በፈረሰኞቹ 2ለ0 አሸናፊነት ተጠናቋል።

ቅዱስ ጊዮርጊስ ከጨዋታው መጀመሪያ አንስቶ በኳስ ቁጥጥርና በጥቃት እንቅስቃሴ የተሻለ ብቃት በማሳየት ተጋጣሚውን ጫና ውስጥ መክተት ችሏል። በ9ኛው ደቂቃ ተመስገን ብርሃኑ ከቀኝ መስመር ያሻማውን ኳስ ዳግም ወንድሙ በግራ እግሩ ጨርፎ በራሱ ላይ በማስቆጠር ፈረሰኞቹን መሪ አድርጓል።
የመጀመሪያው አጋማሽ ሊጠናቀቅ አንድ ደቂቃ ሲቀረው በ44ኛው ደቂቃ ቢላል ገመዳ ወደ ቅጣት ሳጥን ይዞ የገባውን ኳስ ለአማኑኤል ኤርቦ አቀብሎት፣ አማኑኤልም በግራ እግሩ ወደ ግብነት በመቀየር የቡድኑን መሪነት ወደ 2ለ0 አሳድጓል። በዚህም የመጀመሪያው አጋማሽ በፈረሰኞቹ ሁለት ግቦች መሪነት ተጠናቋል።

በሁለተኛው አጋማሽ ቅዱስ ጊዮርጊስ በተጋጣሚው የመከላከል ስህተቶች የተፈጠሩ ተጨማሪ የግብ እድሎችን ቢያገኝም ወደ ግብነት መቀየር አልቻለም። ሀድያ ሆሳዕናም የጨዋታውን ውጤት ለመቀየር ቢጥርም የተሳካ የግብ ሙከራ ሳያደርግ ጨዋታውን በሽንፈት አጠናቋል።
በዚህ ውጤት ቅዱስ ጊዮርጊስ በሊጉ ተከታታይ ሁለተኛ ድሉን ሲያስመዘግብ፣ ሀድያ ሆሳዕና በተቃራኒው ተከታታይ ሁለተኛ ሽንፈት ገጥሞታል።
ወልዋሎ ዓ/ዩ 0-0 መቻል
በአዳማ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲ ስታዲየም ቀን 10:00 ላይ ወልዋሎ አዲግራት መቻልን ያስተናገደበት ጨዋታ ያለ ግብ 0ለ0 በሆነ ውጤት ተጠናቋል።
በመጀመሪያው አጋማሽ መቻል በኳስ ቁጥጥር የተሻለ ብቃት ቢያሳይም ወደ ግብ የተቃረቡ አደገኛ ሙከራዎችን ማድረግ አልቻለም። ወልዋሎም በተመሳሳይ ለተጋጣሚው መከላከያ ከባድ ፈተና የሚሆኑ የግብ ሙከራዎችን ሳያቀርብ የመጀመሪያው አጋማሽ ተጠናቋል።

በሁለተኛው አጋማሽ በ62ኛው ደቂቃ የመቻሉ ተጨዋች በረከት ካሌብ ሁለተኛ ቢጫ ካርድ በማየቱ በቀይ ካርድ ከሜዳ ተሰናብቷል። በዚህም መቻል የቀሩትን ደቂቃዎች በ10 ተጨዋቾች ለመቀጠል ተገዷል።
የተጨዋች ቁጥር ብልጫ ያገኘው ወልዋሎ ይህንን እድል ተጠቅሞ የድል ግብ ለማስቆጠር ጥረት ቢያደርግም የመቻሉን መከላከያ ሰብሮ መግባት አልቻለም። በመጨረሻም ጨዋታው ያለ ግብ በአቻ ውጤት ተጠናቋል።

ይህ ውጤት ወልዋሎ በሊጉ እስካሁን ያለ ድል ጉዞውን እንዲቀጥል ሲያደርግ፣ መቻል በተከታታይ ሁለተኛ ጨዋታው በቀይ ካርድ ተጨዋች ማጣቱ ሌላው የሚጠቀስ ክስተት ሆኗል። መቻልም በተከታታይ ሁለተኛ ጨዋታው ያለ ግብ አቻ ወጥቷል።

