የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ መሪው ቅዱስ ጊዮርጊስ ለወዳጅነት ጨዋታ በመጪው ማክሰኞ ወደ ሱዳን መዲና ካርቱም እንደሚጓዝ ሶከር ኢትዮጵያ ማወቅ ችላለች፡፡
ፈረሰኞቹ ሐሙስ ግንቦት 18 ከሱዳኑ ታላቅ ክለብ አል ሂላል ጋር ጨዋታቸውን ያደርጋሉ፡፡ በጉዳዩ ዙርያ ለሶከር ኢትዮጵያ አስተያየታቸውን የሰጡት የቅዱስ ጊዮርጊስ ስፖርት ማህበር ስራ አስኪያጅ አቶ ሰለሞን በቀለ የወዳጅነት ጨዋታው መኖሩን አረጋግጠው ጨዋታው የኢትዮ-ሱዳን ግንኙነት ለማጠናከር እና የግንቦት 20ን ለማድመቅ የታለመ ጨዋታ እንደሆነ አስረድተዋል፡፡
ቦዲቲ ላይ ዕሁድ በ21ኛ ሳምንት የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ጨዋታ ከወላይታ ድቻ የሚጫወተው ጊዮርጊስ ወደ ካርቱም ማክሰኞ እንደሚያቀና ዋና ስራ አስኪያጁ አስረድተዋል፡፡ የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን ከሌሴቶ ባለበት የአፍሪካ ዋንጫ ማጣሪያ ምክንያት የሚቋረጠው ፕሪምየር ሊጉ የወዳጅነት ጨዋታውን ለማድረግ አመቺ ሆኗል፡፡
ከካፍ ቻምፒየንስ ሊግ በአል አሃሊ ትሪፖሊ በአንደኛው ዙር ተሸንፎ የወደቀው የኦምዱሩማኑ ክለብ የሱዳንን ፕሪምየር ሊግ አንድ ቀሪ ጨዋታ እየቀረው በ40 ነጥብ እየመራ ይገኛል፡፡ የከተማ ተቀናቃኙ ኤል ሜሪክ ሁለት ጨዋታ እየቀረው በ33 ነጥብ ሁለተኛ ነው፡፡
ቅዱስ ጊዮርጊስ የተመሰረተበትን 80ኛው ዓመት ለማድመቅ በጥር ወር ከሱዳኑ ኤል ሜሪክ እና ከኬንያው ጎር ማሂያ የወዳጀነት ጨዋታ መጫወቱ ይታወሳል፡፡