የኢትዮጵያ ከፍተኛ ሊግ አዲሱ የውድድር ዘመን ህዳር 3 ይጀመራል

 ከፍተኛ ሊግ| 05-01-2009 


የኢትዮጵያ ከፍተኛ ሊግ የ2009 የውድድር ዘመን ህዳር 3 እንደሚጀመር ከኢትዮጵያ እግርኳስ ፌዴሬሽን ባገኘነው መረጃ ለማወቅ ተችሏል፡፡ የእጣ ማውጣት ስነስርአት እና የውድድር ደንብ ውይይቱ ደግሞ ውድድሩ ከመጀመሩ 1 ወር በፊት ጥቅምት 3 ቀን 2009 በኢትዮጵያ ሆቴል ይካሄዳል፡፡

ፌዴሬሽኑ ለተሳታፊዎቹ 32 ክለቦች በላከው ደብዳቤ መሰረት ከዛሬ መስከረም 5 ጀምሮ እስከ መስከረም 20 ቀን 2009 ድረስ የምዝገባ እና ፍቃድ ማውጫ ገደብ ያወጣ ሲሆን ለታዛቢዎች እና ዳኞች የሚከፈለውን አበል እስከ መስከረም 30 ድረስ እንዲያጠናቅቁ አሳስቧል፡፡ በቀነ ገደቡ ከፍለው የማይጨርሱ ክለቦችንም ከውድድር እንደሚሰርዝ ፌዴሬሽኑ አስታውቋል፡፡ የአምናው ውድድር በዳኞች እና ታዛቢዎች ክፍያ ለመጠናቀቅ ምክንያት የተጀመረበት ጊዜ መጓተቱ የሚታወስ ነው፡፡

የከፍተኛ ሊግ ክለቦች ውድድሩ እስከሚጀመርበት ህዳር 3 ቀን 2009 ድረስ ተጫዋቾች የማዘዋወር መብት የሚኖራቸው ሲሆን ከመስከረም 9 ጀምሮ ተጫዋቾቻቸውን ማስመዝገብ እንደሚችሉ ታውቋል፡፡

የ2009 የውድድር ዘን ከፍተኛ ሊግ በተባለበት ቀን የሚጀመር ከሆነ እስከ ሰኔ አጋማሽ እንደሚጠናቀቅ ይጠበቃል፡፡ ይህም በ2008 ከነበረው ውድድር በተሸለ በጊዜ ተጠናቆ ወደ ፐሪሚየር ሊግ ለሚያልፉ ክለቦች ፋታ የሚሰጥ ይሆናል፡፡ የ2008 የውድድር ዘመን በነሃሴ ወር አጋማሽ መጠናቀቁ የሚታወስ ነው፡፡

 

የውድድር መጀመርያ ወቅቶች

ፕሪሚየር ሊግ – ጥቅምት 20 ሲጀመር መስከረም 12 የውድድሩ ፕሮግራም ይወጣል

ከፍተኛ ሊግ – ህዳር 3 ሲጀመር ጥቅምት 3 የውድድሩ ፕሮግራም ይወጣል

ብሄራዊ ሊግ – የሚጀመርበት ቀን ያልተቆረጠ ሲሆን በቀጣዮቹ ቀናት ይታወቃል ተብሏል፡፡

 

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *