ሪፖርት ፡ የሳምንቱ ታላቅ ጨዋታ በቅዱስ ጊዮርጊስ አሸናፊነት ተጠናቋል

የዓምናው ቻምፒዮን ቅዱስ ጊዮርጊስ በሳምንቱ ታላቅ ጨዋታ ደደቢትን 2-0 አዲስ አበባ ስታዲየም ላይ ማሸነፍ ችሏል፡፡ ከጨዋታው በፊት ሁለቱም ክለቦች የመጀመሪያ ሳምንት ጨዋታቸውን በሶስት ግብ ብልጫ ማሸነፋቸው ጨዋታው ተጠባቂ ያደረገው ሲሆን ፈረሰኞቹ በመጀመሪያው አጋማሽ ያስቆጠሯቸው ሁለት ግቦች ሙሉ ሶስት ነጥብ ይዘው ለመውጣት ችለዋል፡፡ ጨዋታው በሳምንቱ በአሳዛኝ ሁኔታ ህይወቱ ላለፈው ለሃዋሳ ከተማው ግብ ጠባቂ ክብረአብ ዳዊት የአንድ ደቂቃ ህሊና ፀሎት በማድረግ የዕለቱ አርቢትር የፊፋ ኢንተርናሽናል ዳኛ ባምላክ ተሰማ አስጀምረውታል፡፡

በመጀመሪያው አጋማሽ ፈረሰኞቹ የደደቢትን የመስመር አጨዋወት መስበር ሲችሉ ሰማያዊዎቹ በሜዳ ክልላቸው የመቀባበያ አማራጭ እንዲያጡ በማድረግ ጫና ፈጥረው ሲጫወቱ ታይቷል፡፡ በ17ኛው ደቂቃ አዳነ ግርማ አቡበከር ሳኒ ያሻገረለትን ኳስ በአግባቡ መጠቀም ሳይችል ኳሷን በግቡ አናት ሰድዷታል፡፡

በ23ኛው ደቂቃ ምንተስኖት አዳነ በግንባሩ በመግጨት ፈረሰኞቹን መሪ ማድረግ ችሏል ችለዋል፡፡ ከዘጠኝ ደቂቃዎች በኃላ በቀኝ መስመር ጥሩ እንቅስቃሴ ሲያሳይ የነበረው አቡበከር ከመስመር የተሻገረለትን ጥሩ ኳስ ቢያገኝም ሳይጠቀምበት ወደ ውጪ ወጥቷል፡፡ በ38ኛው ደቂቃ ሰማያዊዎቹ በስዩም ተስፋዬ አማካኝነት አቻ ለመሆን ተቃርበው ነበር፡፡

የመጀመሪያው አጋማሽ ሊጠናቀቅ በተቃረበበት ሰዓት አዳነ የቅዱስ ጊዮርጊስን መሪነት ወደ ሁለት ያሰፋች ግብን በግንባሩ በመግጨት ከመረብ አሳርፏል፡፡ በጭማሪው ሰዓት ዩጋንዳዊው ኢንተርናሽናል ሮበርት ኦዶንካራ የጌታነህ ከበደን ቅጣት ምት በድንቅ ሁኔታ አምክኗል፡፡

በሁለተኛው አጋማሽ የደደቢት የእንቅስቃሴ እና የግብ ማግባት ሙከራ ብልጫ የታየ ሲሆን ፈረሰኞቹ ውጤታቸውን አስጠብቆ ለመውጣት ሲጥሩ አምሽተዋል፡፡ ሰማያዊዎቹ በጌታነህ፣ ዳዊት ፍቃዱ እና ተቀይሮ በገባው አቤል ያለው አማካኝነት ያልተሳኩ የግብ ሙከራዎችን አድርገዋል፡፡ ምንም እንኳን በሁለተኛው 45 ሰማያዊዎቹ የግብ ማግባት ሙከራ የበላይነት ቢኖራቸውም ኢላማውን የጠበቀ ሙከራ ማድረግ ሳይችሉ ቀርተዋል፡፡ ውጤቱ ቅዱስ ጊዮርጊስን በስድስት ነጥብ የሊጉ አናት ላይ እንዲቀመጥ አድርጓል፡፡

 

ከጨዋታ በኃላ የተሰጡ አስተያየቶች

“በራሳችን ስህተት ነው የተሸነፍነው ማለት እንችላለን” የደደቢት አሰልጣኝ ዩሃንስ ሳህሌ

“በራሳችን ስህተት ነው የተሸነፍነው ማለት እንችላለን፡፡ ሁለት ጥፋቶችን ሰጠን በሁለት የቆመ ኳስ ሁለት ግብ አገቡብን፡፡ እነኛን ሁለት ሙከራዎች ብቻ ነበር ያደረጉብን እና የራሳችን ስህተት ነው፡፡ የራሳችንን ስህተት አርመን መምጣት አለብን፡፡ መሃል ሜዳውን ሰጥተናቸዋል፡፡ አውቀን ነው የሰጠናቸው ምክንያቱም በመኃል ሜዳ አልነበረም እኛ የመጫወት ፍላጎታችን፡፡ ግን በዛ ተበልጠን አይደለም እራሳችን በሰራነው ጥፋት ነው ግቦች የተቆጠሩብን፡፡”

“ወደ ግብ የመሄድ ብዙ ዕድል አላገኘንም፡፡ የማግባት እድሎች አንድ ወይም ሁለት ነው ያጋጠሙን እነሱን መጨረስ አልቻልንም፡፡ ስለዚህም ማረም የሚገባንን ነገር አርመን እንመጣለን፡፡ በሁሉም ተጫዋቾች ደስተኛ ነኝ፡፡ 28 ጨዋታ ይቀረናል አንድ ጨዋታ ነው የተሸነፍነው፡፡”

 

“ተጫዋቾቻችን የሰጠናቸውን ስራ በሙሉ በአግባቡ እና በጥሩ መልኩ ሰርተዋል” የቅዱስ ጊዮርጊስ ረዳት አሰልጣኝ ዘሪሁን ሸንገ

“ጨዋታው በጣም ጥሩ ነው፡፡ ሁሉም ነገር የሰጠናቸው እና አርጉ ያልናቸው ነገር አርገው ውጤቱን ይዘን በመውጣታችን በጣም ደስተኞች ነኝ፡፡ የእያንዳንዱን ቡድ ጠንካራ እና ደካማ ጎን እናውቃለን፡፡ ለምን በዛላይ ሰርተን ስለምንመጣ ያንን አየተን የሰራነውን ስራ አግኝተንበታል፡፡”

“የተለየ ዝግጅት አላደረግንም፡፡ እነሱም እኛም አሸንፈን ነው የመጣነው፡፡ ደደቢት ጠንካራ ቡድን ነው፡፡ ሁለታችንም የሚጠብቀን ጠንካራ እና ከባድ ጨዋታ ነበር ይህንን በድል ተወጥተናል፡፡ የቡድናችን ጠንካራ እና ደካማ ጎኖች አሉ፡፡ በመስመር በኩል ያሉትን ክፍተቶች ተጠቅመን ማድረግ ያለብንን አድርገን ልጆቻችንን ውጤት ይዘው ወጥተዋል፡፡”

“ጉዳት ላይ እና በቅጣት የሌሉ ልጆች አሉ፡፡ አስቻለው (ታመነ) ጥሎ ማለፍ ላይ በቀይ ወጥቶ አራት ጨዋታ የለም፡፡ ራምኬል፣ ሳላዲን (ሰኢድ) እ ዘካሪያስ በጉዳት አልተጫወቱም፡፡ ስለዚህም ባሉን ተጫዋቾች ምን እንደምንፈልግ እና ማን የትኛው ቦታ ላይ ጥሩ ነው የሚለውን እያየንበት ስለሆነ ተጫዋቾቻችን የሰጠናቸውን ስራ በሙሉ በአግባቡ እና በጥሩ መልኩ ሰርተዋል፡፡”

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *